ፈልግ

የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፣ 

የአማዞን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ እምነት ከፍርሃት የበለጠ ሊሆን እንደሚገባ አስታወቀ።

 በቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 26/2012 ዓ. ም. ጀምሮ በመሰብሰብ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ልዩ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በስምንተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሃሳብ ላይ እምነት ከፍራቻ ሕይወት የበለጠ መሆኑን አስታወቀ። ሲኖዶሱ ይህን ያስታወቀው ጉባኤው በተጀመረ ሦስተኛ ሳምንት እና 166 የሲኖዶሱ አባቶች በተካፈሉበት ጉባኤ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአማዞን አካባቢ አገሮች በሚደረግ የወንጌል ምስክርነት “የኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳሚነት” በሚል ርዕስ ላይ ስምንተኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ባደረገው ውይይት፣ “በአማዞን አካባቢዎች ስለ ቅዱስ ወንጌል የሚያውቁ ስንት ናቸው”? በማለት ጥያቄን አንስቶ የተወያየ ሲሆን፣ የቅዱስ ወንጌል መልካም ዜና በአማዞን አካባቢ አገሮች ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በሙሉ መነገር ያለበት ቀዳሚ ምስክርነት ነው ብሏል። የወንጌል መልካም ዜና በአንድ ሰው ብቻ የሚከናወን አይደለም ያለው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ መጠነ ሰፊ ለሆኑት የሐዋርያዊ አገልግሎት ጥያቄዎች ተገቢ እና በቂ ምላሾችን ለመስጠት፣ የወንጌልን ደስታ ለመመስከር ብቁ የሆኑ አገልጋዮችን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያትም ለዚህ ነው ብለዋል።

በክህነታዊ ስልጣን ላይ የተደረገ አስተንትኖ፣

የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ በጠቅላላ ጉባኤ፣ው የጥሪ ማነስ በአማዞን አካባቢ አገሮች ብቻ አለመሆኑን አስገንዝቦ፣ በአማዞን አካባቢ አገሮች ውስጥ የሚታየውን የክህነት ጥሪ ማነስ ለማስወገድ የአካባቢው አገሮች ነባር ሕዝቦች ባሕልን መሠረት ያደረገ የክህነት ጥሪን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። የሲኖዶሱ አባቶች ከዚህ ጋር በማያያዝ አሁን የምንገኝበት ዓለም ለቤተክህነት የቅድስና ሕይወት የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ እንደሆነ፣ የዓለማዊነት ባህል ተጽዕኖን እያስከተለ እንደሚገኝ ከገለጹ በኋላ የክህነት የቅድስና ሕይወት እሴቶች እንዳይዘነጉ በጥንቃቄ ማሰብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በአማዞን አካባቢ አገሮች ውስጥ ለሚቀርብ የክህነት አገልግሎት፣ ቆሞሳት ከሌሎች ሩቅ አገሮች በእንግድነት ከመምጣት ይልቅ በቋሚነት የሚያገለግሉ የአካባቢው ተወላጆች ቢሆኑ መልካም ነው ብለው ለክህነት ጥሪ ማነስ ብቻ መልስ ለማግኘት ከመሞክር ይልቅ በአማዞን አካባቢ አገሮች የምትገኝ ቤተክርስቲያን የአካባቢውን ባሕል እና ማንነት የምትገልጽ መሆን ይኖርባታል ብለዋል። የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት በተጨማሪም ይህ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ያለን እምነት ለስሕተት ካለን ፍራቻ የሚበልጥ በመሆኑ አዳዲስ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ መሠረቶችን ለመጣል ያግዛል ብለዋል።   

ተጨማሪ ሴቶችን ለወንጌል አገልግሎት፣

በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የሴቶችን ሚና በድጋሚ የተመለከተው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ሴቶች ሐዋርያዊ ሃላፊነቶችን የሚውስዱ እና በውሳኔ አሰጣጥ ውጤታማ ተሳትፎ የሚያደርጉትን ሴቶችን ማዘጋጀት አስመልክቶ ውይይት አድርጓል። ሴት ምዕመናንን በአማዞን አካባቢ አገሮች በምትገኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ በአገልግሎት ለማሳተፍ ከሚያግዙ መንገዶች መካከል አንዱ የድቁና ሕይወት ነው ብለው ይህን ማዕረግ ለአማዞን አካባቢ አገሮች ሴቶች መስጠትን በተመለከተ ቤተክርስቲያን በጥበብ እና በማሰተዋል ማሰብ እንዳለባት የጉባኤው ተካፋዮች አሳስበዋል። በማሕበረሰብ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያስታወሰው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ሴቶች በአማዞን አካባቢ አገሮች ውስጥ ከሚያበረክቱት የትምህርተ ክርስቶስ እና የእናትነት አገልግሎት በተጨማሪ በሌሎች አዳዲስ የቤተክርስቲያን አገልግሎቶች መሳተፍ የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል። በአማዞን አካባቢ አገሮች ሴቶች ሰላምን እና እርቅን በማምጣት ረገድ የሚጫወቱት ሚና በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን የአገልግሎት ቦታን ሰፋ ያደረገዋል ብለዋል።

መንፈስ ቅዱስን በማዳመጥ አንድነትን ማጠናከር፣

መንፈስ ቅዱስ የሚለውን በማዳመጥ፣ በእርሱ በመመራት ላይ የሚገኝ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ በጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን ላይ የሚደርስ አደጋን ሥነ-ምሕዳራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ በአስቸኳይ መታደግ እንደሚያስፈልግ ተወያይቷል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ፍጥረትን መጠበቅ እና መንከባብከብ ለሰው ልጆች የተሰጠ ሃላፊነት ብለው በአማዞን አካባቢ አገሮች የሚገኝ የተፈጥሮ ደን በምድራችን ብቸው እና ውብ የሆነ የአትክልት ሥፍራ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህ የምድራችን ገነት በአካባቢው በተነሳው የሰደድ እሳት ምክንያት ወደር የማይገኝለትን ቅርስ ሊያሳጣ የሚችል መሆኑን ሲኖዶሱ አስታውቋል። በሕብረት መጓዝ ማለት በስቃይ ላይ የምትገኝ እናት ምድራችን የምታስተጋባውን ጩሄት በጋራ ማዳመጥ እንደሆነ የገለጸው ሲኖዶስ በአማዞን አካባቢ አገሮች የሚገኙ ልዩ ልዩ አገር በቀል ድርጅቶች ያቀረቡት ጥሪ በከፋ አደጋ እንዳንወድቅ የሚያሳስብ ነው ብሏል። እርስ በእርስ ተገናኝተን አንድ ሆነናል፤ መልካም ሕይወት ማለት ሁሉ የተመቻቸ ማለት አይደለም። አንድ ሆነናል ማለት የባልንጀራችንን እና የጋራ ምድራችንን ስቃይ ማዳመጥ ማለት ነው። በሰውን ልጆች መካከል የሚፈጠር መከፋፈል ውድቅ መሆን አለበት፤ እንዲሁም የማህበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን ወይም ልዩነቶች መወገዝ እንዳለባቸው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አሳስቧል። የግሎባላዜሽን ስርዓት ሊካዱ የማይችሉ ጥቅሞችን ለሰው ልጆች ሕይወት ማበርከቱ ቢታወቅም በሌላ ጎኑ እጅግ በጣም ጎጂ የሆነ፣ በፍጆታ ላይ የተመሰረተ የካፒታሊስት ስርዓት እንዲስፋፋ መንገዶችን አመቻችቷል። የደሃ አገሮች ሕዝቦች ጉልበታቸውን ጨርሰው ያመረቱቸው ምርቶች ወይም ሸቀጦች ወዳደጉት አገሮች ሲመጡ በጣም አነስተኛ በሆነ ዋጋ ይቸበቸባሉ። የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ጥሪ፣ ድካማቸው ዋጋ እንዲኖረው እና የድህነት ሕይወታቸውም ለሁለቱ ወገኖች እኩል ዋጋን በመስጠት የስነ ምሕዳር ለውጦችን ሊያመጣ በሚችል፣ የፍትህ እና የሰላም ምሳሌ ወደሚሆን የንግድ ሥርዓት እንዲለወጥ የሚጠይቅ መሆኑን ሲኖዶሱ አስታውቋል።

የአማዞን አካባቢ ተወላጅ የሃይማኖት ሕይወት፣

በአማዞን አካባቢ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው ስቃይ የማያቋርጥ ትኩረት እንዲሰጠው በማለት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጥያቄውን አቅርቧል። ከአማዞን አካባቢ ሕዝቦች ባሕል መካከል የቅዱስ ወንጌል ፍሬን ማግኘት ማለት ሊሰበክላቸው የሚገባ ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞም ቢሆን በመካከላቸው የሚገኝ መሆኑን ሲኖዶሱ አስረድቷል። ቅዱስ ወንጌል በአንድ ባሕል ዘንድ ብቻ ተገድቦ የሚቀር እንዳልሆነ የገለጸው ሲኖዶስ ቤተክርስቲያን በአማዞን አካባቢ አገሮች መካከል የምትገኝ መሆኑን ያረጋግጣል ብሏል። በቅድመ ሲኖዶሱ ዝግጅት ወቅት አዎንታዊ ልምዶችን በማሰባብሰብ እንዲሁም በሲኖዶሱ ወቅትም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሚቀርቡ አዳዲስ ሀሳቦች በመታገዝ ለአማዞን አካባቢ አገሮች አዳዲስ መዋቅሮችን ለመመስረት ጥያቄዎች ቀርበዋል።

በአማዞን አካባቢ አገሮች ተወላጆች የሚቀርብ የቅድስና ሕይወት መልካም ምሳሌ እነደሚሆን ተገልጿል። በአካባቢው አገሮች የሚገኙ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ለነዋሪው ሕዝብ መብት በመታገል የወንጌል አገልግሎት ጥሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ እንዳለበት፣ ዘላቂነት ያለው ስልጠና እንዲሰጥ፣ በአገሬው ባሕል እና መንፈሳዊነት የታገዘ፣ የሰውን እና የተፈጥሮ ስርዓትን የተከተለ ሥነ-ምህዳርን ማሳደግ እና ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 October 2019, 15:14