ፈልግ

አብርሐማዊ ሐረግ ያላቸው የአይሁድ፣ የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የሌሎች ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች አብርሐማዊ ሐረግ ያላቸው የአይሁድ፣ የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የሌሎች ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች 

የሰውን ነፍስ በሕክምና እገዛ መግደል በጥብቅ ተወገዘ።

ሰኞ ጥቅምት 17/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ የተሰበሰቡት የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ለሞት የሚዳርግ የሕክምና መንገድን “ዩታናሲያ” በመጠቀም የሰውን ነፍስ ከስጋው እንዲለይ ማድረግ ስህተት መሆኑን በጋራ ባወጡት አቋማቸው አስታወቁ። ከፍተኛ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮቹ ከዚህ ጋር በማያያዝ ለሕሙማን አስፈላጊውን የህክምና እርዳታን በመስጠት ከሕመሙ መፈወስ ካልሆነም እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የመንከባከብ እና የሕመም ማስታገስ አገልግሎትን እየሰጡ ማቆየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብሉይ ኪዳን ዘመን አብርሐማዊ ሐረግ ያላቸው የአይሁድ፣ የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የሌሎች ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በሕብረት በገለጹት አቋማቸው የሰውን ነፍስ ለመግደል የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት የሕክምና ወይም የሕክምና ባለሙያ እርዳታን እንደሚቃወሙ አስታውቀው እንዲህ ዓይነቱ የሕክምና ዜደ የማይሻር እና መሠረታዊውን የሰው ልጅ ሕይወት ክብር የሚጻረር፣ ሥነ ምግባርን እና ሃይማኖትን የሚቃረን በመሆኑ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መከልከል እንዳለበት አሳስበዋል። ልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በጋራ የፈረሙበት ሰነድ ለሞት የሚዳርግ የሕክምና መንገድን ወይም “ዩታናሲያ”፣ ለሞት የሚያበቃ የሕክምና ባለሙያ እርዳታን የሚቃወም እና ለሕሙማን አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ በመስጠት ከሕመሙ መፈወስ፣ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ መንከባከብ እንደሚያስፈል የሚያሳስብ መሆኑ ታውቋል።

ነፍስን በሕክምና እገዛ መግደል በሥነ ምግባር እና በሃይማኖት እይታ የተሳሳተ ነው፣

ከሕክምና አቅም በላይ ሆኖ ለሞት የተቃረበን ነፍስ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ መንከባከብ ለሰው ልጅ የተሰጠ መለኮታዊ ስጦታ ነው ያሉት የአይሁድ፣ የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የሌሎች ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ይህ ሳይደረግ ቀርቶ እያወቁ ሆን ተብሎ ነፍስን ለመግደል የሚወሰዱ እርምጃዎች ከሰብዓዊ እና ሥነ ምግባራዊ ሃላፊነት ውጭ በመሆኑ ሊገታ ይገባል ብለዋል።

የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች “ለሰው ልጅ አክብሮት የተሞላበት እንክብካቤ ሊደረግለት ያስፈልጋል” ባሉት የጋራ አቋማቸው ለሞት ለተቃረበ ሕሙማን የሚደረግ እንክብካቤ መሰረታዊ ትርጉም ያለው ሰብዓዊ፣ መንፈሳዊ እና ሐይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል። የሐይማኖት ተቋማቱ ተወካዮች በመተባበር የጋራ አቋማቸውን እንዲገልጹ ያስተባበረው እና ሃሳባቸውን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት፣ በእስራኤል የአይሁድ እምነት ተወካይ መምህር አብርሃም ስቴንበርግ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በበኩላቸው በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ ሰኞ ጥቅምት 17/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ የተካሄደውን የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ስብሰባን እንዲያስተባብሩ መጠየቃቸው ታውቋል። የጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች የጋራ መግለጫ ረቂቅ እንዲያዘጋጁ ማስተባበራቸው ታውቋል። በቁጥር 30 የሆኑ የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች የጋራ መግለጫቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ በቫቲካን ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። በተወካዮቹ መካከል ካርዲናሎች፣ የአይሁድ እምነት መምህራን እና በእስልምና እምነት በዓለም ሁለተኛ ደረጃ የያዘው የኢንዶኔዢያው ሙሐማዲያ ድርጅት ተወካይ መገኘታቸው ታውቋል።

ለሕሙማን እንክባክቤ እና የማስታገስ አገልግሎት ሊሰጥ ይገባል፣

አብርሐማዊ ሐረግ ያላቸው የአይሁድ፣ የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የሌሎች ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በጋራ መግለጫቸው በየትም ሥፍራ በሕመም ለሚገኝ የሰው ልጅ በእውቀት የተደገፈ እንክባክቤ እና የማስታገስ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። ሞትን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶች ምክንያታዊነት የጎደላቸው መስለው ቢታዩም መጽናናትን ፣ ውጤታማ የሆኑ የህመም ማስታገሻ እርዳታዎችን መስጠት፣ ፍቅርን መግለጽ፣ በሞት አፍ አፍ ለሚገኝ ታካሚ እና ለቤተሰቧ ወይም ለቤተሰቡ መንፈሳዊ ብርታትን የመስጠት ሥነ ምግባራዊ እና ሃይማኖታዊ ግዴታ አለብን ብለዋል። በቫቲካን የተሰበሰቡት የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች የሕሙማንን ሰብዓዊ ክብር እና መብት ለማስጠበቅ የሚያግዙ ሕጎች እና ፖሊሲዎች እንዲረቀቁ በማለት ጥሪ አቅርበው በርካታ የሌሎች ሐይማኖት ተቋማት እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ የሕሙማንን ነፍስ በሕክምና እገዛ የመግደል ተግባርን ለማውገዝ መተባበር እንዳለባቸው ጠይቀዋል። በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ በንግግራቸው ይህን የተሳሳተ የሕክምና አሰጣት መንገድን ለማስቀረት የሐይማኖት ተቋማት ሕብረት እና የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። የሐይማኖት ተቋማት ሕብረት አስፈላጊነቱ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነቶችን ለይተው በማወቅ፣ ለእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ፣ ወንዶች እና ሴቶች ፍሬያማ የሆነ አገልግሎትን ለማበርከት ስለሚያግዝ ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 October 2019, 16:37