ፈልግ

የሚዲያ ባለሞያዎች የሐዋርያትን እና የሰማዕታትን ቋንቋ መማር ያስፈልጋል። የሚዲያ ባለሞያዎች የሐዋርያትን እና የሰማዕታትን ቋንቋ መማር ያስፈልጋል። 

የማሕበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ከሕይወት ምስክርነት ጋር መዛመድ አለበት።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት መስከረም 12/2012 ዓ. ም. የቫቲካን ሚዲያ አገልግሎት ሠራተኞችን በሬጂና ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተቀብለው ንግግር ባደረጉበት ወቅት የማሕበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ከምስክርነት ጋር እንዲሆን ማሳሰባቸውን የቅድስት መንበር ሚዲያ አገልግሎት በርዕሠ አንቀጹ አስታውቋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው የቤተክርስቲያኒቱ ማሕበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የክርስቲያን ሰማዕታት የሕይወት ምስክርነትን የታከተለ መሆን አለበት ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማሕበራዊ ሚዲያ በኩል የምናደርጋቸው ግንኙነት የሕይወት ምስክርነት የሚታይበት፣ ትክክለኛ የራስ ማንነትም የሚገለጽበት፣ ሌሎችንም እንደማንነታቸው የሚያቀርብ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን እና የሰማዕታትን የሕይወት ምስክርነት የተከተለ መሆን እንዳለበት አሳስበው ይህን በተግባር ለማሳየት የቤተክርስቲያኒቱ የሚዲያ አገልግሎት ባለሞያዎች የሐዋርያትን እና የሰማዕታትን ቋንቋ መማር ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ካለው የቫቲካን ሚዲያ ተቋም ሃላፊዎች፣ ጋዜጠኞች እና የቴክኒክ ባለሞያዎች ጋር ሲገናኙ የመጀመሪያቸው መሆኑ ታውቋል። በአዲስ መልክ የተቋቋመው የቫቲካን ሚዲያ ተቋም ከዚህ በፊት በቅድስት መንበር ውስጥ አገልግሎት ስያበረክቱ የቆዩ ዘጠኝ የማሕበራዊ መገናኛ መምሪያዎችን አንድ አድርጎ በሥሩ የያዘ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናትናው ዕለት ለተቀበሏቸው በርካታ የተቋሙ ሠራተኞች ባደረጉት ንግግር በማሕበራዊ መገናኛ ዘርፍ በኩል የሚቀርቡ ዕለታዊ አገልግሎቶች በእውነት እና በግልጽ የሚታየውን የሰማዕታትን ምሳሌ የተከተል መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አደራ ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች፣ ማለትም ለአድማጮች፣ ለተመልካቾች እና ለአንባቢያን በቀርቡ የቪዲዮ ምስሎች፣ የሬዲዮ ቃለ መጠይቆች ወይም ጽሑፎች መጠንን የተመለከተ ሳይሆን የቅድስት መንበር ሚዲያ ወይም የክርስቲያን ሚዲያ ማለት እውነትን የተከተለ ምስክርነት ይዘት ያለው መሆን እንዳለብት አስገንዝቧል። ይህን ምስክርነት ለመስጠት በሚዲያው ዘርፍ የተሰማሩት ሰራተኞች ከሁሉ አስቀድሞ በሚያቀርቡት ዘገባ ሆነ መረጃ ውስጥ ማኖር ፣ መተባበር ፣ የሚያጋጥሙ ተጨባጭ እውነታዎች ልብን የሚነኩ መሆን አለባቸው በማለት ቅዱስነታቸው ለሠራተኞቹ ባቀረቡት አደራ አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በሌሎች ሰዎች አስገራሚ ታሪኮች ልባችን የተነካ በሕይወታችንም ላይ ተጽዕኖን የሚፈጥሩ መሆን አለባቸው ብለው፣ ለእነዚህ ታሪኮች ውበት፣ እውነተኛነት እና ተስፋን እንዴት መመስከር እንደምንችል ማወቅ አለብን ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቫቲካን ሚዲያ ሰራተኞች ያደረጉት ንግግር ሊካሄድ በተቃረበው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋዜማ ላይ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። የአማዞን አካባቢዎችን የሚመለከተው የደቡብ አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በርካታ የመገናኛ ተቋማትን እና የማሕበራዊ ሚዲያ አገልግሎቶችን የሚያሳትፍ መሆኑን የዜና አገልግሎቱ አክሎ አስታውቋል። የቫቲካን ዜና አገልግሎት ርዕሰ አንቀጽ ውንጌልን መሠረት ያደረገ የሚዲያዎች ምስክርነት በዛሬው ዘመን እምነትን ከፖለቲካ ጋር ለሚያዛምዱት፣ የቤተክርስቲያንን ሕይወት ወይም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስጋን ከወንበዴዎች ጦርነት ጋር ለሚያዛምዱ ጥሩ ትምህርት ይሆናቸዋል ብሎ በማከልም የቤተክርስቲያን አስተምህሮችን ለመፈክርነት፣ ለክፍፍል፣ በምዕመናን፣ በሐዋርያዊ አባቶች እና በቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ላይ ለሚያፌዙት ትምህርትን ይሰጣል ብሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለቫቲካን ሚዲያ ሠራተኞች ባደረጉት ንግግር የሰማዕታትን ምሳሌ መከተል ከወንጌል ምስክርነት አንዱ ነው ብለው ለቤተክርስቲያን ሲሉ ሕይወታቸውን የተሰውት የእኛ ሰማዕታት ናቸው ብለዋል። የሰማዕታት ምስክርነት፣ ሕይወታቸውን ለወንጌል፣ ለጥላቶቻቸው ፍቅር፣ ራሱን ስለሌሎች ድነት ሲል መስዋዕት ላደረገው ለኢየሱስ ክርስቶስ ሲባል መሰዋት ነው ብለዋል።

በመሆኑም አንድ ክርስቲያን፣ በማሕበራዊ ሚዲያ በኩል መልዕክት ወይም መረጃን በሚያስተላልፍበት ወቅት የመከፋፈል ሳይሆን አንድነትን፣ የጥላቻን ሳይሆን የፍቅርን መልዕክት እንደሚያስተላልፍ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። የቤተክርስቲያን ሕልውናም በልዩነት፣ በአመጽ እና በጦርነት  አስተሳሰብ እንደተዋጠ የፖለቲካ አካሄድ አለመሆኑን የቫቲካን መገናኛ አገልግሎት በርዕሠ አንቀጹ አስገንዝቧል።

24 September 2019, 15:46