ፈልግ

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የተፈጸመው የጸሎተ ፍትሐት ስነ ስርዓት፤ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የተፈጸመው የጸሎተ ፍትሐት ስነ ስርዓት፤ 

“ካርዲናል አኪሌ ሲልቬስትሪኒ ጠንካራ የቤተክርስቲያን አገልጋይ የነበሩ እና ለጋራ ውይይቶች ትኩረትን የሰጡ ነበሩ”።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የነበሩ እና የምስራቅ ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጉባኤ ተጠሪ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል አኪሌ ሲልቬስትሪኒ፣ ሐሙስ ነሐሴ 23/2011 ዓ. ም. ማረፋቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ዓርብ ነሐሴ 24/2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የተፈጸመው የጸሎተ ፍትሐት ስነ ስርዓት የመሩት የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ፣ ካርዲናል አኪሌ ሲቬስትሪኒ የጋራ ውይይትን የሚወዱ፣ ቤተክርስቲያንን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በትጋት ያገለገሉ መሆናቸውን ተናገርዋል። የጸሎተ ፍትሐት ስነ ስርዓት ፍጻሜን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመሩ መሆናቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ፣ አንቶኔላ ፓሌርሞ የላክችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለቤተክርስቲያን እና ለሕብረተሰብ የቀረበ የአገልግሎት ሕይወት፣

ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ፣ በጸሎት ስነ ስርዓቱ ወቅት ባሰሙት ንግግር ካርዲናል አኪሌ ሲልቬስትሪኒ በካርዲናሎች የመማክርት ጉባኤ ውስጥ ባበረከቱት ረጅም የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ ቤተክርስቲያንን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ቅድስት መንበርን እና ሕብረተሰብ በትጋት ያገለገሉ መሆናቸውን አስታውሰው፣ የአገልግሎት ዘርፋቸውም ሰላምን በማስከበር፣ ሰብዓዊ መብቶችን በማረጋገጥ እና ሌሎችንም ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሰፊ ተግባራት የነበሩበት መሆኑን አስታውሰዋል። ካርዲናል አኪሌ ሲቬስትሪኒ፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉባቸው 36 ዓመታት፣ ለሰው ልጅ ትኩረት መስጠትን፣ ባህሉን ማወቅን፣ ችግሮችን የመፍታትን፣ ቤተክርስቲያንን እና ሕብረተሰብ በትጋት የማገልገል ችሎታን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ የመጡበት ዓመታት መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ካርዲናል ሲልቬስትሪኒ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣
ካርዲናል ሲልቬስትሪኒ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣

በዲፕሎማሲያዊ ተልእኮ ያበረከቱት አገልግሎት በርካቶች ነበሩ፣

ካርዲናል አኪሌ ሲቬስትሪኒ፣ ከካርዲናል ካሳሮሊ ጋር በመተባበር በዲፕሎማሲያዊ ተልእኮአቸው፣ በቀዝቃዛ ጦርነት ዓመታት የኮሚኒስት ስርዓትን ከሚያራምዱ አገሮች ጋር የጋራ ውይይቶችን በማድረግ ሰፊ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውን ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ አስታውሰዋል። ከእነዚህ አገሮች ጋር የነበራቸው የጋራ ውይይት ያተኮረው በእነዚህ አገሮች ውስጥ በስደት የምትገኝ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሕልውና እንዲረጋገጥ ለማድረግ እንደነበር ብጹዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለኢጣሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አጭር ሰላምታን አቀረቡ፣

የጸሎተ ፍትሐት ስነ ስርዓት ፍጻሜን የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በስነ ስርዓቱ ላይ ከተገኙት የኢጣሊያ መንግሥት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሆነው ከተመረጡት ከክቡር አቶ ጁሴፔ ኮንቴ ጋር የአጭር ጊዜ ቆይታን በማድረግ ሰላምታ የተለዋወጡ መሆናቸውን እና ካርዲናል አኪሌ ሲቬስትሪኒን ያስታወሱ መሆናቸውን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።

ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ ሲያስታውሷቸው፣

ካርዲናል አኪሌ ሲቬስትሪኒ በፕሬዚደንትነት የመሩት የዶመኒኮ ታርዲኒ ፋውንዴሽን ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ፣ ካርዲናል አኪሌ ሲቬስትሪኒን በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፣ ኩላዊት ቤተክርስቲያንን በመውደድ፣ ለወጣቶች የተፈጥሮ ጸጋ ትልቅ ሥፍራን ሰጥተው አገልግሎታቸውን ያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሕይወታቸውን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ እንደመሆናቸው መጠን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በርካታ የጋራ ውይይቶችንን ያካሄዱ፣ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ታላቅነትን ለማወቅ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለር. ሊ. ጳጳሳት ያበረከቱትን ከፍተኛ ድጋፍ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ማገልገል ማለት በጥበብ ሀብታም መሆን፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሚሰጡት አገልግሎትም ውጤታማ መሆንን ይገልጻል ያሉት ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እምነታቸውን በጣሉብን ጊዜ ሁሉ አቅማችንን እና የአገልግሎት ብቃታችንን ይበልጥ ለማሳደግ ያግዘናል ማለታቸውን አስታውሰው፣ ይህም ከካርዲናል አኪሌ ሲቬስትሪኒ መማር ያለብን ትልቅ ትምህርት ነው ብለዋል።

በቅድስት መንበር የምስራቅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጉባኤ ተጠሪ ነበሩ፣

ካርዲናል ሲልቬስትሪኒ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣
ካርዲናል ሲልቬስትሪኒ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ሆነው ከማገልገል በተጨማሪ የምስራቅ ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጉባኤ ተጠሪ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል አኪሌ ሲልቬስትሪኒ ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ፍሬያማ የሆኑ የጋራ ውይይቶችን በማድረግ፣ በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ፣ ጭቆና እና ስደትን ለመከላከል ተባብረው የሠሩ፣ የመፍትሄ መንገዶችንም ማግኘት የቻሉ መሆናቸውን ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ አስታውሰዋል። 

31 August 2019, 12:59