ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣  

ካርዲናል ፓሮሊን፣ አውሮጳን መልሶ መገንባት የሚቻለው የወንጌል እሴቶችን ሳይዘነጉ እንደሆነ አሳሰቡ።

በመካከለኛው ምዕራብ ኢጣሊያ ከተማ በሆነችው በፍራስካቲ፣ ለወጣቶች በተዘጋጀው  የፖለቲካ ዘርፍ  አጭር ኮርስ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ሽንፈት ያጋጠመው የአውሮጳን ሕዝብ፣ ከመንፈሳዊነት ያፈነገጠ ዓለማዊ አስተሳሰብ በቤተክርስቲያን ላይ ጫናን መፍጠር እንደሌለበት ማሳሰባቸውን የቫቲካን ዜና ዘጋቢ፣ ፌደሪኮ ፒያና የላከልን ዘገባ አመልክቷል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክርስቲያናዊ ማንነት በአውሮጳ አገሮች መካከል ሕብረትን ለመፈጠር በተደረገው ሂደት ውስጥ መሠረታዊ ሚና መጫወቱን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ሕብረቱን ለማምጣት ቁልፍ የሆኑ ክርስቲያናዊ እሴቶች አሁንም መኖራቸውን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እነዚህ ክርስቲያናዊ እሴቶች ፈተና እንዳጋጠማቸው ተናግረው፣ የፈተናው መነሻ የሆኑ አራት ምክንያቶች መኖራቸውን ሲዘረዝሩ የመጀመሪያው

አውሮጳን ለማሳደግ የተዘጋጀውን ቀዳሚ ውጥን ኪሳራ ማጋጠሙ፣ ሁለተኛው በፖለቲካው መስክ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡ፣ ሦስተኛው “መብት” ለሚለው ቃል የሚሰጥ ትርጉም እየሰፋ እና እየተለያየ መምጣት፣ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ውጤቶች የተፈጥሮ ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ የዘነጉ እና በመካከላቸውም ልዩነቶችን የወለዱ በመሆናቸው፣ አራተኛው የግሪክ - ሮማዊ አስተሳሰብ የሚገናኝበት መንገድ በመቋረጡ ምክንያት ነው በማለት አስረድተዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን ለወጣቶች ያስተላለፉት መልዕክት፣

የበጋን የዕረፍት ወራት በደንብ ለመጠቀም በማለት፣ የሮም ሃገረ ስብከት በፍራስካቲ ከተማ ባዘጋጀው የፖለቲካ ትምህርት ቤት አጭር ኮርስ

ላይ ለተገኙት በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአውሮጳ ወጣቶች አስተምሕሮአቸው ያቀረቡት፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ለኮርሱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ አውሮጳን መልሶ መገንባት የሚቻለው በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር እንደሆነ አስረድተው፣ ይህን ጥረት እውን ለማድረግ የክርስቲያን ማሕበረሰብም በበኩሉ ጠንካራ እና ገንቢ የሆኑ ምሳሌነታቸውን በተግባር መግለጽ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማሳሰቢያቸው፣ ቤተክርስትያን መንፈሳዊ እሴቶቿን ለመቀበል ፈቃደኛ በማይሆኑ እና በአውሮጳ ታሪክ ውስጥ ሽንፈት ባጋጠመው ዓለማዊ አስተሳሰብ ጫና ሊደረግባት  እንደማይገባ፣ በቫቲካን ሬዲዮ የጣሊያንኛ ቋንቋ አገልግሎት በኩል አሳስበው፣ በፍራስካቲ ከተማ ለወጣቶች እንዲሰጥ የተደረገው አጭር ኮርስ ዋና ዓላማ ወጣቶች በፖለቲካው ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

በፖለቲካው ዘርፍ የወጣቶች ተሳትፎ እና ሚና የላቀ እንዲሆን ማድረግ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምኞት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ እነዚህን የመሳሰሉ ጥረቶች ለማበረታታት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተው፣ መልካም የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በፖለቲካው ዓለም መሳተፍ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ይህን የቤተክርስቲያኒቱን ፍላጎት ለማሟላት የሮም ሃገረ ስብከት ምዕመናን ከፍተኛ ድምጽን መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ ኢጣሊያን መልሶ ለመገንባት የካቶሊኩ ማሕበረሰብ ተሳትፎ መሠረታዊ እንደነበር ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን         አስታውሰዋል። በዚያን ወቅትም ቢሆን እንደዛሬው ፖለቲካው የተወሳሰበ ነው ብለው፣ ዛሬም ቢሆን ችግሮቻችንን ለመፍታት ተረጋግቶ ማሰብ እና የወንጌል እሴቶችን ባለመዘንጋት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለው በጥረቶች መልካም ውጤቶችን ለማምጣት አዲስ የጋራ ሕብረትን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአውሮጳ ካቶሊካዊ ምዕመናን ምን ያህል ተሳትፎን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፣ የአውሮጳ ወጣቶችስ ቢሆኑ አውሮጳን መልሶ ለመገንባት የሚያግዙ ምን ያህል መልካም ምሳሌዎችን ማግነት የጠበቅባቸዋል ለሚሉት ጥያቄዎች በሰጡት መልስ እንዳስገነዘቡት ከሁሉ አስቀድሞ አውሮጳ የተገነባችው በክርስቲያናዊ እሴቶች እንደሆነ አስረድተው፣ ለአውሮጳ ሕብረት ብለው ብዙ የለፉት አባቶችም ቅዱስ ወንጌልን የጥረታቸው አጋዥ እና መሪ እንዲሆን ማድረጋቸውን አስታውሰው ዛሬ በአውሮጳ ውስጥ እያስተናገድን የምንገኘው ቀውስ በቅዱስ ወንጌል እሴቶች ማነስ ነው ብለዋል። ስለዚህ ወጣቶችም ብሆኑ መልካም የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት የቅዱስ ወንጌል እሴቶችን ዋና መመሪያቸው ማድረግ ይጠብቅባቸዋል ብለዋል።

ወጣቶች ከተቀመጡበት ተነስተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን ያስታወሱት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ አሁን የደረስንበት የዓለም ሁኔታ በግድ የለሽነት የምንመለከተው አይደለም ብለው፣ ወደ ኋላ በመመለስ የቀድሞ ፈተናዎችን ለማለፍ የተጠቀሙባቸውን መልሶች መፈለግ እንደሚገባ የሚያስስቡ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ እነዚያ የቀድሞ መልሶች ባለፉት ዘመናት ውድቀትን እንጂ ምንም ውጤት አላስገኙም ብለው፣ የሚጠበቅብን ያጋጠሙንን ችግሮች የምንወጣባቸውን አዳዲስ ዘዴዎችን ፈልጎ ማግኘት እና በእነዚህ ዜዴዎች በመታገዝ ትክክለኛውን መፍትሄ ማግኘት ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 August 2019, 16:17