ፈልግ

በሶርያ ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል፣ በሶርያ ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል፣ 

ቅድስት መንበር የረሃብተኞችን እና የሕሙማንን ጩኸት ችላ ማለት እንደማይገባ አሳሰበች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በኒዮርክ በተካሄደው የእስራኤል እና የፍልስጤም የሰላም ድርድር ላይ ተገኝተው የመን የምትገኝበትን ሁኔታ በማስታወስ ባሰሙት ንግግር ለተረጅዎች ሰብዓዊ እርዳታን ማቅረብ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው የሶርያ ጦርነት እና አመጽ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በኒውዮርክ ከተማ በዋናነት የእስራኤል እና ፍልስጤም የሰላም ድርድርድ እንዲሁም ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጉዳይ ላይ ለመምከር በጠራው፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብስሰባ ላይ፣ የሶርያን፣ የየመንን እና የኢራቅን፣ እንደዚሁም የመካከለኛውን ምስራቅ አገሮች የሰላም ጉዳይ አስመልክተው ሃሳብ ማቅረባቸው ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በሰው ልጆች ላይ ጫና የሚፈጥሩትን ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመቀነስ የሚያግዝ ቀዳሚ እርምጃ የጋራ ወይይት፣ የመቻቻል እና በሰላማዊ አብሮ የመኖር ባህልን ማሳደግ እንደሆነ አስረድተዋል።

እስራኤላዊያን እና ፍልስጤማውያን ወደ ድርድር መመለስ አለባቸው፣

በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የሚካሄደውን የስላም ድርድር መልካም አቅጣጫ እና ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ከተፈለገ ለሁለቱም ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፎርችን ማቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ አስታውሰው፣ ሁለቱን አገሮች ማለትም እስራኤልን እና ፍልስጤምን እንዲሁም ሌሎች የተቀሩትን የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን ወደ ሰላም ጎዳና ለመመለስ የሚደረገውን የኒኮላይ ምላደኖቭ የሰላም ጥረት አስታውሰዋል። በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የሚታየወ አለመታማመን ሁለቱን አገሮች ወደ አመጽ ሊመራቸው እንደሚችል የገለጹት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ ይህም በሁለቱ ወገኖች ባሉ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሕይወት መጥፋት አደጋን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ እንደተናገሩት፣ የተጀመረው የነጻ ውይይት መድረክ የመፍትሄ መንገዶችን በማግኘት ወደ ተግባር የሚሸጋገር እንጂ ሁለት መንግሥት፣ ሁለት ሕዝብ በሚለው የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ በሚፈጠሩ እንቅፋቶች ላይ አተያየቶችን በመጠቆም ብቻ የሚያበቃ መሆን የለበትም ብለዋል። ለፍልስጤም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና የሥራ ኤጀንሲ አማካይነት አስፈላጊውን ሰብዓዊ እገዛን ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን ሁለቱ አገሮች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ቀርበው በመካከላቸው እርቅ እና ሰላምን ለማምጣት የሚያደርጉትን የጋራ ውይይት ሊተካ እንደማይችል ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አስረድተዋል። በመሆኑም ሁለቱ አገሮች ተጎራብተው መኖር የሚያስችላቸውን የሰላም ውይይት እንዲያደርጉ ማበረታታት ያስፈልጋል ብልዋል።

በሶርያ ሰብዓዊ መብት ይከበር፣

ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ ለጸጥታው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር፣ በሶርያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች አመጽ መኖሩን ያስታወሱ ሲሆን ይህም ወደ ከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል። በምግብ፣ በውሃ፣ በሕክምና እርዳታ እና በትምህርት እጦት ምክንያት በመሰቃየት ላይ የሚገኙ ሰዎች ጩሄት እያዳመጡ በዝምታ መቀመጥ የማይቻል መሆኑን የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ያለ አሳዳጊ መንገድ ላይ የተተው በርካታ ሕጻናት፣ ያለ ረዳት የቀሩ በርካታ እናቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሶርያ ሕዝብ ላይ የሚደርስ የጦርነት ስቃይ እጅግ በማሳሰባቸው ምክንያት፣ ለዚያ አገር ሕዝብ ሰላምን እና እርቅን የተመኙበትን መልዕክት ያለፈው ሰኔ 21/2011 ዓ. ም. ለሶርያው ፕሬዚደንት ለአቶ በሽር አል አሳድ መላካቸውን ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ በላኩት መልዕክታቸው የሶርያ ሕዝብ ከሞት እና ከመቁሰል አደጋ እንዲተርፍ፣ የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ ከመኖሪያው እንዳይፈናቀል፣ የተፈናቀሉትም ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፣ የታሰሩት ነጻ እንዲወጡ፣ በእስር የሚቆዩትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ዕድል እንዲያገኙ፣ የፖለቲካ እስረኞች ሰብአዊ መብት እንዲከበር፣ እንክብካቤም እንዳይጎድልባቸው፣ ለሕዝባቸው በጎ የሆነው ሁሉ እንዲያደርጉላቸው የሶርያውን ፕሬዚደንት አቶ በሽር አል አሳድን ማሳሰባቸውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ አስታውሰዋል።

የጦር መሣሪያ ሽያጭ እና የመን ጉዳይ፣

በየመን የሚካሄደው ጦርነት ሰብአዊ ሁኔታ ወደ ከፋ ደረጃ መድረሱን አቡነ ቤርናዲቶ አስታውሰው ባሁኑ ሰዓት ሕዝቡ ያለ ምግብ እና ያለ ሕክምና አገልግሎት መቅረቱን ገልጸዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮፍራም አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ይፋ ያደረገውን ሪፖርት የጠቀሱት አቡነ ቤርናዲቶ በየመን ከ2006 ዓ. ም. ጀምሮ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት 20 ሚሊዮን ሰዎች በቂ ምግብ የሌላቸው መሆኑን አስታውሰዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድንጋጌ ቁጥር 2481 መሠረት የተኩስ አቁም ውል ተግባራዊ እንዲሆን እና የጦር መሣሪያ ሽያጭም እንዲገታ ማድረግ እንደሚያፈልግ አሳስበዋል።

በባሕረ ሰላጤው አገሮች አካባቢ ሰላማዊ መፍትሄዎች ማግኘት፣

ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በመጨረሻም ከኢራቅ በኩል የሚታየውን ተስፋ ሰጭ የዕርቅ እና የመልሶ ግንባታ ጥረቶችን ገልጸው፣ በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረው ጽንፈኛ እስላማዊ መንግሥት አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የክርስቲያን ማሕበረሰብ እና ጎሳዎች ላይ ይፈጽም የነበረውን የግድያ እና የጥፋት ተግባርን አስታውሰዋል። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አካባቢያዊ ግጭቶች እንዳይስፋፉ፣ ለባሕረ ሰላጤው አካባቢ አገሮች ሰላማዊ መፍትሄዎችን ማግኘት ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
25 July 2019, 16:46