ፈልግ

የጸሎተ ፍትሐቱን ስነ ስርዓት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መርተዋል፣               የጸሎተ ፍትሐቱን ስነ ስርዓት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መርተዋል፣  

ካርዲናል ታርሲሲዮ ቤርቶኔ “ካርዲናል ፓዎሎ ሳርዲ የሞራል ስነ መለኮት ትምህርት ሊቅ ነበሩ”።

ያለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ. ም. ያረፉትን ካርዲናል ፓውሎ ሳርዲን በማስታወስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ. ም. በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ የቀድሞ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ታርሲሲዮ ቤርቶኔ፣ ካርዲናሉ ባሳለፉትን የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስን ሐዋርያዊ አስተምህሮችን እና ንግግሮችን በማስተባበር ከፍተኛ አገልግሎትን ያበረከቱ መሆናቸውን አስታውሰዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ታርሲስዮ ቤርቶኔ፣ ካርዲናል ሳርዲ ታላቅ የሞራል ስነ መለኮት ትምህርት ሊቅ እንደነበሩም አስታውሰዋል። በሰሜን ኢጣሊያ፣ ፒየሞንቴ ክፍለ ሀገር የተወለዱት ካርዲናል ፓዎሎ ሳርዲ ባደረባቸው የአጭር ጊዜ ሕመም፣ በተወለዱ በ84 ዓመት ዕድሜአቸው፣ በሮም መኖሪያቸው ውስጥ ያለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ. ም. ያረፉ መሆናቸው ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴ ፍጻሜ ላይ የቀረበውን ጸሎተ ፍትሐት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መምራታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ አሌሳንድሮ ዲ ቡሶሎ የላከልን ዜና አመልክቷል።

“የእውነት ብርሃን” ሐዋርያዊ መልዕክት ጽሑፍ ላይ ተባብረዋል፣

ካርዲናል ፓዎሎ ሳርዲ እንደ ጎርጎሮሳዊው 1976 ዓ. ም. ወደ ቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ለአገልግሎት መሠማራታቸውን የቀድሞ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ታርሲስዮ ቤርቶኔ አስታውሰው በዚህ የሥራ መደባቸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስን ሐዋርያዊ አስተምህሮችን እና ንግግሮችን በማስተባበር ከፍተኛ አገልግሎትን ያበረከቱ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ካስተባበሯቸው ሥራዎች መካከል እውነት፣ ነጻነት፣ ሕሊና፣ እና ሕግ የሚሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ጽንስን የማስወረድ ታሪክ ዛሬ እና ነገ፣

ካርዲናል ፓዎሎ ሳርዲ ካዘጋጇቸው ስነ ሞራላዊ አስተምህሮዎች መካከል “ትሕትና እና ሐቀኝነት” የሚሉት ጽሑፋቸው በወላጆች ዘንድ ትልቅ አድናቆትን እና ምስጋናን ያተረፈላቸው መሆኑን ያስታወሱት ካርዲናል ቤርቶኔ ለካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊ አስተምህሮ እድገት ተጠቃሽ እና አወያይ ጉዳዮችን ያካተተውን “ጽንስን የማስወረድ ታሪክ በዛሬው እና በነገው ዓለም በሚለው ጽሑፋቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖን ማበርከታቸውን አስታውሰዋል። ካርዲናል ቤርቶኔ በማከልም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ሐዋርያ የነበሩት ካርዲናል ፓውሎ ሳርዲ በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ወቅት በተለይም ለሕክምና ወደ ሆንፒታል እስከ ሄዱበት ጊዜ ድረስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ መንበረ ታቦት ላይ በመገኘት የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

15 July 2019, 16:59