ፈልግ

ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሕጻናት፣ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሕጻናት፣ 

ካርዲናል ፓሮሊን ከሰዎች ጋር የሚደረግ የጋራ ትብብር መቀነስ የለበትም ማለታቸው ተገለጸ።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ያለፈው ቅዳሜ ሰኔ 22/2011 ዓ. ም. ፖቴንሳ በተባለች የደቡብ ኢጣሊያ ክፍለ ሀገር ተገኝተው ባሰሙት ንግግር በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባ ማሕበራዊ ግንኙነት እና ትብብር መቀነስ የለበትም በማለት አሳሰቡ። ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በደቡብ ኢጣሊያ ክፍለ ሀገር በሆነችው በፖቴንዛ ዋና ከተማ ባዚሊካታ የተገኙት በሀገረ ስብከቱ ብጹዓን ጳጳሳት እና ወጣቷ አውሮጳ በተባለ ማሕበር እገዛ የሚታተም፣ አቬኒር ጋዜጣ ክፍል ባዘጋጀው በዓል ላይ መሆኑ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ፣ ኣመደዎ ሎሞናኮ ከላከልን ዘገባ ለማወቅ ተችሏል። ከጋዜጣው ዳይሬክተር ከሆኑት ማርኮ ታርኩዊኒኖ በኩል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ጊዜ እንዳስረዱት የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ዋና ዓላማ በአጭሩ ሲታይ በሕዝቦች እና በአገሮች መካከል ሰላምን ለማስፈን በምታደርገው ጥረቶች እና አውደ ጥናቶች ይጠቃለላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የቤተ ክርስቲያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው እንደገለጹት፣ የቤተ ክርስቲያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሦስት አበይት ጉዳዮችን ያስቀድማሉ በማለት በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውንም ዓይነት ችግር አቅሎ ከማየት ይልቅ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄን ማፈላለግ፣ ሰብዓዊ ክብርን በማስቀደም በተለይም ሕጻናትን፣ አዛውንትን፣ ስደተኞችን፣ የአመጽ እና የጦርነት ተጠቂዎችን ጉዳይ ችላ አለማለት ነው ብለዋል። በሁለተኛ ደረጃ ሃያላን መንግሥታት ወይም አገሮች የራሳቸውን እድገት እና ብልጽግና ከመመልከት ባሻገር ፊታቸውን በማደግ ላይ ወደሚገኙ ደሃ አገሮች ቢያዞሩ፣ ይህም ዓለማችን የምትገኝበትን ጠቅላላ እውኔታ ለመረዳት ስለሚያግዝ ነው ብለው፣ በሦስተኛ ደረጃ በድንገት ለሚከሰቱት ማሕበራዊ ችግሮች መፍትሄን ለማፈላለግ ብቻ ራስን መገደብ ሳይሆን ችግሮች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ የመከላከያ መንገዶችን አዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በየአገራቱ ከሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት፣

ሰኔ 6/2011 ዓ.ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅድስት መንበር እንደራሴዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት ያስታወሱት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በቅዱስ ወንጌል የሚመራ እንደሆነ አስረድተው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ቅዱስ ወንጌል ለቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊ ተልዕኮ ቀዳሚ መሣሪያ መሆኑን ዘወትር ያስገነዝባሉ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስት መንበር እንደራሴዎች በያሉበት አገር ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን በብርታት እንዲወጡ አደራ ማለታቸውንም ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።

ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚገኝ ደስታ፣

በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘመን ከችግር ነጻ የሆነ ወቅት አለመኖሩን የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማራመድ ላይ የሚገኙት የተሃድሶ መንገድም የተለያዩ ችግሮችን ሳያስነሳ አልቀረም ብለው ከዚህ በተጨማሪ ከሕዝባዊት ሪፓብሊክ ቻይና ጋር ለረጅም ዓመታት የተካሄደው የውይይት ሂደትም እንደዚሁ ቀላል እንዳልነበረ አስረድተዋል። ነገር ግን ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያሳዩት ጽናት እና መረጋጋት፣ አስጨናቂ ገጠመኞች ቢኖራቸውም ዘወትር ከፍተኛ ውስጣዊ ሰላምን ማግኘታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥት፣

ከቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥት ጋር የተደረሰውን ስምምነት በማስመልከት ባሰሙት ንግግር ካርዲናል ፓሮሊን እንደተናገሩት፣ በዚያች አገር ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚያበረክቱትን ብጹዓን ጳጳሳት ስያሜን በተመለከተ በሁለት መንግሥታት መካከል መልካም ስምምነት ላይ መደረሱን እና ባሁኑ ጊዜ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሙሉ ግንኙነት መመሥረታቸውን አስታውቀዋል። ከብጹዓን ጳጳሳት መካከል ሁለቱ ባለፈው ጥቅምት ወር በቫቲካን የወጣቶችን ጉዳይ በመከረው የመላው ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል። በቻይና የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን የእምነት ጥንካሬን፣ ጽናትን እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የእነዚህ ምዕመናን የእምነት ነጻነት እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያላቸው ግንኙነት ገደብ ሊደረግበት አያስፈልግም ብለዋል። ችግሮች ባይታጡም በመካከላችን መተማመን ካለ ማንኛውንም እክል በጋር ልንወጣው እንችላለን ብለው በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረሰው ስምምነት መልካም ፍሬን ሊያፈራ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፕሬዚደት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት፣

የሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ቫቲካን የሚያደርጉት ጉብኝት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ሐይማኖተኛ እና የእምነታቸውን እሴቶች አጥብቀው የሚይዙ በመሆኑ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መግባባት ይኖራል ብለዋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እሴቶች አደጋ ላይ መውደቁን የሩስያ መንግሥት በቅርብ እንደምትከታተለው ገልጸው የሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንኙነት በእነዚህ ጉዳዮች እና እንደዚሁም በተለይም ቅድስት መንበርን ባሳሰባት በሶርያ እና በምዕራባዊ ዩክሬን የሚካሄዱትን አመጾች በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ለእስራኤል እና ፍልስጤማ ሰላም ብቸኛው መንገድ የጋራ ውይይት ነው፣

በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በቅርቡ ያወጡትን ሁለት ሕዝብ፣ ሁለት መንግሥታት የሚለውን የእስራኤል እና የፍልስጤም የሰላም መንገድ በማስመልከት አስተያየታቸውን የገለጹት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሰላምን ለማንገስ እንደ ብቸኛ መንገድ እንደሚመለከቱት ገልጸው፣ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ ይህ ሃሳብ ተቀባይነትን ያገኘ መሆኑን አስረድተው ሁለቱ ሕዝቦች ይህን ሃሳብ ለመቀበል ፈቃደኝነታቸውን ባይገልጹም ወደ ፊት በመካከላቸው መተማመንን ለማምጣት  እና መልካም ግንኙነትን ለማሳደግ የጋራ ውይይት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ከእስልምና እምነት ጋር መኖር ስለሚገባ ውይይት፣

“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል ከጥር 26 – 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች በጋራ ባካሄዱትን ስብሰባ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካፈላቸውን የተናገሩት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ወደ አቡ ዳቢ ባደረጉት 27ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከአል አዛር ታላቁ ኢማም ከሆኑት ከአል ጣይብ ጋር በመካከላቸው ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውሰው ይህ ስምምነት ከእስልምና እምነት ተካታዮች ጋር ለሚደረግ የጋራ ውይይት መልካም እርምጃ ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚጎብኟቸው አገሮች ምርጫ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ የሚሄዱባቸውን አገሮች በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መልስ ሲሰጡ እንዳስገነዘቡት ከተለያዩ እምነቶች እና ባሕሎች ጋር የጋራ ውይይት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገንዝበዋል ብለዋል። በጦርነት እና አመጽ ውስጥ በሚገኙት አገሮች መካከል እርቅን እና ሰላምን ማውረድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እና አቶሚክ የጦር መሣሪያ አምራች አገሮችም እቀባ እንዲያደርጉ በማለት ቅዱስነታቸው ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

አውሮጳ እና የስደተኞች ሁኔታ፣

የስደተኞችን ሁኔታ በማስመልከት በሰጡት አስተያየት ካርዲናል ፔትሮ ፖሮሊን እንዳስረዱት ከሁሉም አስቀድሞ ቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት አስፈላጊነትን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለው ሰብዓዊ ክብርን፣ ለሰው ልጅ ሊሰጥ የሚገባውን ክብር በሚገባ ከተገነዘቡ ስደተኞችን በእንግድነት ተቀብሎ ማስተናገድ፣ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ማቅረብ ለአውሮጳው ማሕበረሰብ ክርስቲያናዊ ግዴታ ይሆናል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

03 July 2019, 14:56