ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ መጠልያ ከሌላቸው ሰዎች ጋር በተገናኙበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ መጠልያ ከሌላቸው ሰዎች ጋር በተገናኙበት ወቅት  

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስም የሚከናወኑ የልግስና ተግባራት

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስም በእየለቱ የሚከናወነው የልግስና ተግባር “በስውር የሚያህ አምላክህ በስውር ይከፍልሃል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱሳችንን መርዕ ከግምት ባስገባ መልኩ የሚከናወን ሲሆን በዚህም የተነሳ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስም በእየዕለቱ የሚከናወኑ የልግስና ተግባሮች የብዙ የመገናኛ ብዙዓንን ቀልብ እንዳይስቡ ተደርገው የሚከናወኑ እለታዊ ተግባራት ናቸው። እ.አ.አ በ2018 ዓ.ም ብቻ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኙ ለነበሩት ሰዎች የቤት ኪራይ እና ከዚህ ጋር ተያያዢነት ያለው ውጪ ለመሸፈን በማሰብ ይህ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የእርዳታ ማዕከል 3.5 ሚልዮን ኤውሮ ውጪ በማድረግ ድሆችን ተጠቃሚ አድርጉዋል።

የዝህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቤተክርስቲያን እያከናወነችው የምትገኘው የልግስና ተግባር ታሪክ የሚጀምረው ከሐዋርያት ዘመን አንስቶ ነው። ኢየሱስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደ ተናገረው እኛ ሁላችን በመጨረሻው ቀን በእግዚኣብሔር ፊት ቀርበን የምንዳኘው እዚህ በምድር ላይ እያለን ባከናወነው የፍቅር እና የልግስና ተግባር ላይ መሰርቱን ባደረገ መልኩ ነው (ማቴ 25፡31-46)። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ ሲናገር “ከተግባር የተለየ እምነት በራሱ የሞተ ነው” በማለት በጻፈው መልእክቱ መናገሩ የሚታወቅ ሲሆን በተጨማሪም “ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረውምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣ ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል?” (ያዕቆብ 2፡14-16) በማለት እምነታችን በበጎ ተግባራት እና ምጽዋዕት በመስጠት ጭምር ሊገለጽ እንደ ሚገባው ይናገራል።

የምጽዋዕት አሰጣጥ ታሪክ አጀማመር

በመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ዘንድ ለድሆች የሚደረገውን ማነኛውንም ዓይነት ድጋፍ የሚያስተባብሩ እና በተለየ መልኩ የሚያስተዳድሩ ዲያቆናት ነበሩ። ከዚያም በመቀጠል ቤተክርስቲያን ለድሆች የምታደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ፣ በተደራጀ እና ማዕከላዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደር ይቻል ዘንድ በማሰብ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በእርሳቸው ስም በተቋቋመ ተቋም እንዲመራ መደረጉን ከታሪክ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህም ተቋም በይፋ የተቋቋመው በ 18ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በኢኖስነት 3ኛ በተፈረመው ሕጋዊ ሰነድ ነበር። ቤተክርስቲያን በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስም የምታደርገውን ድጋፍ በይፋ የተጀመረው በእዚያን ጊዜ ነበር። የመጀመሪያው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የነበረውን በላቲን ቋንቋ “ሬሩም ኖቫሩም” (እ.አ.አ. 1891 ዓ.ም) የተሰኘውን ሐዋርያዊ መልእክት ይፋ ያደረጉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሥር በሚታዳደረው ተቋም አማካይነት ማነኛውም ዓይነት አስፈላጊ ድጋፍ ለድሆች እንዲዳረስ አድርገዋል። በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ በማበብ ላይ በነበረው የኢንዱስትሪ አብዮት የተነሳ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ በተፈጠረው የሥራ እድል የተነሳ ባሕላዊ የሆነ የኗኗር ዘይቤዎቻቸውን በመተው በዚህ የኢንዱስትሪ አብዮቱ በፈጠረው አዲስ የሥራ እድል ለመጠቀም በማሰብ በየፋብሪካዎቹ ውስጥ የተቀጠሩት ሰዎች በደረሰባቸው ከፍተኛ በደል የተነሳ ለድህነት በመጋለጣቸው ይህንን ችግር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመፍታት በማሰብ መላው ቤተክርስቲያን የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ እና ይህ ድጋፍ ደግሞ በተቀናጀ መልኩ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሥም ለተፈለገው ዓለማ ተደራሽ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት አድርገው አልፈዋል።

ይህንን ታሪካዊ ሂደት ካለፈ በኋላ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስም የሚከናወኑት የበጎ አድራጎት ተግባራት በዓለም ዙሪያ ተስፋፍተው በተለይም ለድሃው ማኅበረሰብ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጾ በማደርግ ላይ እንደ ሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን በሮም እ.አ.አ. በ2018 ዓ.ም በሮም ከተማ ውስጥ ለሚገኙ ድሆች ከ 3.5 ሚልዮን በላይ ኤውሮ ወጪ በማድረግ የቤት ኪራይ መክፈል ላልቻሉ ሰዎች፣ በተጨማሪም የመብራት፣ የጋዝ፣ የመድኃኒት እና ለመሳሰሉት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማሙላት ላልቻሉ ሰዎች እገዛ ማድረጉም ተገልጹዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 May 2019, 15:38