ፈልግ

ቅድስት መንበር ቻይና ባዘጋጀችው ዓለም አቀፍ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኤግዚቢሽን የምትሳተፍ መሆኗ ተገለጸ።

በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ፣ ቤይጂንግ ከተማ ከሚያዝያ 20/2011 ዓ. ም. ጀምሮ በሚቀርብ ዓለም አቀፍ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኤግዚቢሽን ላይ ቅድስት መንበር የምትካፈል መሆኗን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታወቀ። ቅድስት መንበር በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ መሳተፍ በሁለቱ መንግሥታት መካከል እየተደረገ ላለው ውይይት እና የባሕል ግንኙነት ድልድይ እንደሚሆን መግለጫው አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ በሚታዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ስትካፈል ይህ የመጀመሪያዋ መሆኑ ታውቋል። ቅድስት መንበር የምትሳተፍበት ይህ ከሚያዝያ 20/2011 ዓ. ም. እስከ መስከረም 26/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ መሆኑ ታውቋል። ቅድስት መንበር ይህን ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን የምትካፈለው ከቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥት በቀረበላት ግብዣ መሆኑ ሲታወቅ ዓላማውም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሃሳብ ለማጠናከር ነው ተብሏል።

ቅድስት መንበር የምታቀርበው ኤግዚቢሽን የሚያካትተው ለመድሐኒትነት በሚሆኑ ዕጽዋዕት የሚናገሩ ከሐዋርያዊ ቤተ መጽሐፍት የተሰበሰቡ ሠነዶችን መሆናቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በቫቲካን ሙዚዬም የሚገኝ እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን በፒተር ቨንዘል የተሳለ፣ የአዳም እና ሄዋን የምድረ ገነት ሕይወት የሚያመለክት ምስል ቅጂ ለእይታ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል። ምስሉም ሰዓሊው ከፍተኛ የስዕል ችሎታን እና ጥበብን በመጠቀም፣ ተፈጥሮን እና በውስጡ የሚኖሩትን እንስሳት በአስደናቂ መልኩ ለማሳየት የሞከረበት እንደሆነ ታውቋል። ቅድስት መንበር የምታቀርበው ኤግዚቢሽን በተጨማሪም በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዘውን “ብርሃን ይሁን” በሚል አርዕስት የተዘጋጀችውን ዓለም አቀፍ መልዕክት የምታቀርብ መሆኑ ታውቃል። ለእይታ ከሚቀርቡት ምስሎች መካከል በቫቲካን የሚገኘውን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚያሳይ ከነሐስ የተሳለ ምስል እና በወርቅ የተለበጠ የወይራ ዛፍ ምስል መሆናቸው ታውቋል።

የአካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ መወያየት፣

የቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ባዘጋጀችው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ ቅድስት መንበር መሳተፏን ይፋ ያደረጉት በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ የሚመለከት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጃን ፍራንኮ ራቫዚ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ጃን ፍራንኮ ራቫዚ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰኞ ሚያዝያ 7/2011 ዓ. ም. በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ ከተማ የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የረጅም ዓመት መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ታሪክ ያለው ካቴድራ በእሳት አደጋ መጎዳቱን ከገለጹ በኋላ እንዳስገነዘቡት በሕዝቦች መካከል የሚደረጉ ውይይቶ ከሐይማኖታዊ ወይም ከመንፈሳዊ ይዘት በተጨማሪ ስነ ጥበብን፣ ባሕልን እና ሳይንሳዊ ምርምሮችን የሚያጠቃልሉ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ካቀረቡት መካከል ቅድስት መንበር የምታቀርበውን ኤግዚቢሽን በምክትል አስተባባሪነት የሚመሩት ሞንሲኞር ቶማስ ትራፍኒ እንዳስታወቁት ቅድስት መንበር የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ ባዘጋጀችው ኤግዚቢሽን መሳተፏ ምሳሌያዊ እና ባህላዊ እንደሚሆን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

ሞንሲኞር ቶማስ ትራፍኒ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት ቅድስት መንበር በአለም አቀፍ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኤግዚቢሽን እንድትሳተፍ ጥያቄው የቀረበው ከቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ በኩል መሆኑን ገልጸው የሚያቀርቡት ኤግዚቢሽንም ታሪካዊ እንደሚሆን አስረድተዋል። ለኤግዚቢሽኑ የተመረጡት ርዕሶችም ብርሃን፣ ውሃ፣ አበቦች፣ ድንጋይ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት አስረድተው በተቻለ መጠን ተፈጥሮን የሚመለከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቅድስት መንበር ተፈጥሮን ለመንከባከብ የምታደርገውን ከፍተኛ ጥረት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በኩል መግለጿን አስታውሰዋል።             

ቅድስት መንበር በቤጂንግ ከተማ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ መሳተፏ በሁለቱ መንግሥታ መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀው ግንኙነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረ ገልጸው በኤግዚቢሽኑ መልክ የሚሳዩት የአትክልት ሥፍራ መልካም የባሕል ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል። የአትክልት ሥፍራ እንዲዘጋጅ የተመረጠበት ዋና ዓላማ፣ የጋራ መኖሪያ በሆነው ምድራችን በወንድማማችነት አብሮ በመኖር ለምድራችንም የሚያስፈልገውን እንክብካቤን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው ብለዋል።

የኤግዚቢሽናቸው ዋና ሃሳብ የፈለቀው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከሚለው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንደሆነ ያስረዱት ቅድስት መንበር የምታዘጋጀውን ኤግዚቢሽን በምክትል አስተባባሪነት የሚመሩት ሞንሲኞር ቶማስ ትራፍኒ፣ አብዛኛው የአገሩ ዜጋ ክርስቲያን ባልሆነበት አገር ይህን የመሰለ ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት ቀላል እንዳልሆነ ገልጸው ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በኤግዚቢሽኑ በኩል የሚተላለፉ መልዕክቶች ለተለያዩ ባሕሎች አንድነት እንደ መገናኛ ድልድልይ ሆነው የሚያገለግሉ በመሆናቸው ዝግጅታቸው ውጤታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 April 2019, 13:18