ፈልግ

አረጋዊያን፣ አረጋዊያን፣ 

ቅድስት መንበር የአረጋዊያን ሰብዓዊ መብት እንዲከበር አሳሰበች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የቅድስት መንበር (ቫቲካን) ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ቤርናርዲቶ አውዛ በኒዮርክ ከትናንት ሰኞ ሚያዝያ 7/2011 እስከ ሚያዝያ 10/2011 ዓ.ም በኒዮርክ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባደርጉት ንግግር ቅድስት መንበር የአረጋዊያን ሰብዓዊ መብት ትኩረት ተሰጥቶት ጥበቃ እንዲደረግለት እና እንዲከበር ማሳሰቧን አስታውቀዋል።  

ሊቀ ጳጳሳት በርናዲቶ አውዛ በንግግራቸው ቅድስት መንበር በዚህ አሥረኛ የሥራ ጉባኤ ላይ እንድትገኝ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመጋበዟ የተደሰተች መሆኗን ገልጸው ለአረጋዊያን ሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና እድገት በሚደርግ ጥረት የበኩሏን አስተዋጽዖ ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአረጋዊያን የሚሰጥ ሰብዓዊ ክብር ማደግ እንዳለበት፣ አረጋዊያንን ከማሕበረሰብ መካከል የማግለል አዝማሚያ መወገድ እንዳለበት በተደጋጋሚ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ከማሕበረሰቡ መካከል ማግለልን ለማስቀረት የሚቻለው አረጋዊያን ለማሕበራዊ እና ባሕላዊ እድገት የሚያበረክቱት ዘላቂ አስተዋጽዖ መኖሩን ስንገነዘብ ነው ብለው በጀመሩት ጉባኤ ላይ የሚያነሱት ጥያቄዎች እና ውይይቶች እጅግ ጠቃሚ በመሆናቸው የተነሱበትን ዓላም ሊያሳኩ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

አረጋዊያን በድህነት፣ በሕመም፣ በጉልበት ማነስ፣ ከማሕበራዊ ሕይወት መገለል፣ በአመጽ፣ በብቸኝነት፣ በብዝበዛ፣ ለሰው ልጅ መሠረታዊ ፍጆታ በሆኑ በምግብ፣ በልብስ እና በመጠለያ እጦት እንደሚሰቃዩ፣ በበቂ የጤና እንክብካቤ ማነስ፣ በጠያቂ መጥፋት፣ አመጽ እና ጦርነት በሚቀሰቀስበት ጊዜ በቂ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው ሊቀ ጳጳሳት አቡነ በርናዲቶ አውዛ አስረድተዋል። እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ማሕበራዊ ችግሮች የሚደርሱባቸው ሰዎች በወጣትነት ዕድሜም ቢሆን የድሕነት ሕይወት የኖሩትን እንደሆነ አቡነ አውዛ ተናገረዋል። አቡነ አውዛ ከእርሳቸው ጋር ጉባኤውን ለመካፈል ከመጡት ልኡካን ጋር ሆነው ትኩረት ሊሰጥባቸው ያስፈልጋል ያሉትን ሃሳቦች ለጉባኤው አቅርበዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ አረጋዊያን ላካበቱት የሕይወት ልምድ እና እውቀት አስፈላጊውን ክብር እንዲሰጥ ስለሚያደርግ፣ እነርሱን በማሕበራዊ ሕይወት እንዲሳተፉ ማድርግ መገለልን የሚያስወግድ በመሆኑ ለማህበረሰቡ ትምህርት፣ ስልጠና፣ ዘላቂነት ያለው ግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአቅም ግንባታ ሥራ መሰራት እንደሚያስፈልግ አቡነ አውዛ አሳስበው አረጋዊያን የሕዝብ ታሪክ ሕያው ምስክር በመሆናቸው እና እያንዳንዱ ሰው በእነርሱ በመታገዝ የራሱን ታሪክ እንዲያውቅ እና ክብሩንም በሚገባ እንዲያውቅ ያግዛሉ ብለዋል።

በሁለተኛ ደርጃ ለአረጋዊያን የሚደረግ ማሕበራዊ የሕይወት ዋስትና እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ በርናዲቶ አውዛ ለአረጋዊያ ሊሰጥ የሚገባው ማሕበራዊ የሕይወት ዋስትና አደጋ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው አመጾች እና ጦርነቶች ሲቀሰቀሱ አረጋዊያን በሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃሉ ብለዋል። ሕግ በሚረቀቅበት ጊዜም ቢሆን አረጋዊያን ተረስተው እንደሚቀሩ ገልጸው ምክንያቱን ሲናገሩ እንደ አምራች የማሕበረሰብ ክፍል ስለማይቆጠሩ ነው ብለዋል። ይባስ ብሎ የማሕበረሰብ ሸክም ተደረገው ስለሚቆጠሩ ነው ብለዋል።

አረጋዊያን ከማሕበረሰቡ ዘንድ ሊሰጣቸው የሚገባ እገዛ እና ክብር በሚቀንስበት ጊዜ የሚያጋጥማቸው ችግር ግልጽ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳሳት አቡነ በርናዲቶ አውዛ ታመው በቤታቸው ወይም በሐኪም ቤት የሚገኙ አረጋዊያን በሕክምና መንገድ ሕይወታቸውን እንዲያጡ የሚደረጉ መሆናቸውን አስታውሰው ቅድስት መንበር ይህን ተግባር በጽኑ እንደምትቃወም ገልጸው በዚህ አደጋ ላይ ለሚገኙት አረጋዊያን ጥበቃ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ በርናዲቶ አውዛ ለጉባኤው ተካፋዮች ባቀረቡት ንግግር እንደገለጹት አረጋዊያንን በተመልከተ አዲስ መመሪያ ከማውጣት እና ሕግ ከማጽደቅ ይልቅ ከዚህ በፊት በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የወጡትን ዓለም አቀፍ ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ መልካም ይሆናል ብለዋል። አረጋዊያንን በማስመልከት የወጡ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር እና አስፈላጊው እንክብካቤ ሊሰጥባቸው የሚችለው አረጋዊያን የበሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን እና ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስ አቅመ እንደሚያንሳቸው ለወጣቶች እና ለጎስማሶች በቂ ግንዝቤን በማስጨበጥ እንደሆነ ብጹዕ አቡነ አውዛ አስረድተዋል።

እነዚህን መንገዶች መከተል ከዚህ በፊት የወጡ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን እናሻሽል ተብሎ በሚወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት ሌላ አዲስ እና የተወሳሰበ ችግር እንዳይከሰት ያግጻል ብለዋል። ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር በሕብረት የሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮችን የሚያቀራርብ እና የሚያስተባብር በመሆኑ ጥረታችንን በእጥፍ እናሳድግ በማለት አስተያየታቸውን ብጹዕ አቡነ በርናዲቶ አውዛ ገልጸዋ

ወጣቶች በሩን የሚከፍቱ ከሆነ ቁልፉ በአረጋዊያን እጅ ነው ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ አውዛ፣ ከማሕበረሰቡ መካከል ማንንም ለይቶ ማስቀረት፣ ማንንም ቀድሞ ማለፍ እንደማያስፈልግ፣ የትናንትም ሆነ የዛሬ ትውልድ አብረው መጓዝ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን አክለው ገልጸዋል።

በሚቀጥሉ የጉባኤው ቀናት ውስጥ የጉባኤው ተካፋዮች የቆሙለትን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን እና እቅዶችን፣ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጥረቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን ሃሳቦች አጽድቆ እንደሚለያይ ያላቸውን እምነት ገልጸው ምስጋናቸውን በማቅረብ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።                 

16 April 2019, 17:37