ፈልግ

የሴቶች ሚና በቤተክርስቲያን የሴቶች ሚና በቤተክርስቲያን  

ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ የእናትነት ሚና እንዳላቸው ተገለጸ።

ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የማሕበረሰብ ለውጥ መታየቱን የገለጹት የቫቲካን ሙዜም ዳይሬክተር ወይዘሮ ባርባራ ጃታ፣ በእነዚህ ዓመታት መካከል በሴቶች ሚና ላይም ለውጥ መታየቱን ገልጸው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ የአገልግሎት አመታት የሴቶች ሚና ጎልቶ እንዲታይ ተደርጓል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከተማ በሚገኝ በቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና በተመለከተ ስብሰባ ተካሂዷል። “ማርች ኤይት” የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ስብሰባ ከቅድስት መንበር የመገናኛ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት፣ ከቫቲካን ሙዜም እና በቅድስት መንበር የምዕመናን እና የቤተሰብ ሕይወት እንክብካቤ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተወጣጡ ምሑራን ሴቶች ተገኝተው ገንቢ ሃሳባቸውን ማጋራታቸው ታውቋል። በቅድስት መንበር ጳጳስዊ የመገናኛ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት የስነ መለኮት ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ናታሺያ ጎቨካር፣ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና የሚገልጹ መንፈሳዊ ምስሎችን በማቅረብ ሰፊ ገለጻን አቅርበዋል።

የሴቶች ርሕራሄ፣

ወይዘሮ ናታሺያ ለስብሰባው ተካፋዮች ካሳዩኣቸው መንፈሳዊ ምስሎች መካከል የኢየሱስን እግር ሽቶ የቀባች ሴት (የማርታ እህት ማርያም) ምስል ለእይታ የቀረበ መሆኑ ታውቋል። በሰብዓዊ አስተሳሰብ ስንመለከተው ርህራሄ እና ትህትና የተገለጠበት መሆኑን አስረድተዋል። “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለመታሰቢያ ይነገርላታል” (ማር. 14. 9) በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ጠቅሰዋል።

ግንኙነታዊ ፍቅር

ቤተሰባዊ ፍቅር የተገለጠበት ሌላው መንፈሳዊ ምስል በማስመልከት ወይዘሮ ናታሺያ ባቀረቡት ገለጻ በትዳር ሕይወት ውስጥ ባል እና ሚስት በሚያደርጉት የፍቅር ግንኙነት በኩል ሚስት ለባል የምታካፍለው የፍቅር ግንኙነት ባል ብቻውን እንዳይሆን፣ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማው ያደርጋል ብለዋል።

በክፉ ነገር መካከል በጎ ነገርም አለ፣

የቅዱስ መስቀል ቅድስት ተሬዛን የሕይወት ታሪክ ያስታወሱት ወይዘሮ ናታሺያ፣ ይህች ቅድስት በናዚ ጦርነት ጊዜ በጠላቶች ተማርካ ወደ ወሕኒ በመውረድ እንድትሞት መደረጓን ገልጸው የማንም እውቀት ሳይታከልበት ፍቅር ብቻ በክፉ ነገር መካከል በጎ ነገርም መኖሩን እንድንገነዘብ ያግዛል ብለዋል።

ሴቶች ለሚያበረክቱት አገልግሎት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፣

የቫቲካን ሙዜም ዳይሬክተር ወይዘሮ ባርባራ ጃታ፣ የራሳቸውን የሥራ ልምድ በመጥቀስ ባሰሙት ንግግራቸው እድለኛ መሆናቸውን ገልጸው ከሥራ ባልደረቦቻቸው በኩል ለሚያከናውኗቸው ሞያዊ ሥራቸው፣ ለቤተ ሰባዊ ሕይወታቸው የዘወትር እገዛ እና አድናቆት እንዳልተለያቸው ገልጸው ሴቶች በማሕበራዊ ሕይወትም ሆነ በቤተክርስቲያን ለሚያበረክቱት አገልግሎት ትኩረት፣ ምስጋና እና አድናቆት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ማሕበራዊ ለውጦች፣

ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የማሕበረሰብ ለውጥ መታየቱን የገለጹት የቫቲካን ሙዜም ዳይሬክተር ወይዘሮ ባርባራ ጃታ፣ በእነዚህ ዓመታት መካከል በሴቶች ሚና ላይም ለውጥ መታየቱን ገልጸው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ የአገልግሎት አመታት የሴቶች ሚና ጎልቶ እንዲታይ ተደርጓል ብለዋል። ሴቶች ለሚያበረክቱት አገልግሎት እውቅና እና ትኩረት እየተሰጠ ነው ያሉት ወይዘሮ ባርባራ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ በኩል ሴቶች በማሕበረሰብ መካከል በብቃት እንዳይሳተፉ የሚያደርጉ በርካታ እንቅፋቶችን ማስወገድ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያን እናት ናት፣

በቅድስት መንበር የምዕመናን እና የቤተሰብ ሕይወት እንክብካቤ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ በቅርቡ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስወገድ የሚያስችሉ አማራጭ መንገዶችን ለማግኘት በቫቲካን የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስብሰባን አስታውሰው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን ሕመም ሴቶች እንዲገልጹት እድል ሲሰጣቸው ቤተክርስቲያን ራሷ እንድትናገር ማድረግ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መግለጻቸውን ገልጸው ይህም ለሴቶች የበለጠ የሥራ ጫናን መፍጠር ሳይሆን ሴቶች ቤተክርስቲያን የምትገልጥበት መሆኗን እንድንገነዘበው በማለት መሆኑን አስረድተዋል።

የብዙሃን መገናኛዎች ሚና፣ማሕበራዊ መገናኛዎች የሴቶችን ትክክለኛ ገጽታን ለማሕበረሰቡ በማሳየት ረገድ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ወይዘሮ ገብርኤላ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት ሁሉ ሴቶች እናት መሆናቸውን ማሕበረሰቡ በሚገባ እንዲያውቅ እና ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ትልቅ ሚናን መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

እያንዳንዷ ሴት እናት ናት፣

ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ወይዘሮ ገብርኤላ እንደገለጹት ያለንበት ዘመን ሴቶች እናት የመሆንን እሴት ዝቅ አድርጎ ቢመለከተውም፣ የሴቶች እናትነት የሚታውወቀው ልጅን በመውለድ ብቻ ሳይሆን የሴቶች እናትነት ለሰው ልጆች በሙሉ በምታቀርበው ስነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶቿ መታወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።          

08 March 2019, 16:37