ፈልግ

ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን “ቫቲካን ከቻይና መንግሥት ጋር የምታደርገውን ውይይት አጠናክራ ትቀጥላለች”

ከ19ኛው እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ “ቫቲካን ከሌሎች አገራት ጋር ያደረገቻቸው ስምምነቶች” በሚል መሪ ቃል ከየካቲ 21/2011 ዓ.ም ጀመሮ በግሪጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቬርሲቲ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ ጉባሄ ላይ የተገኙት በቫቲካን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት በተለይም ደግሞ ከቻይና ሪፖብሊክ ጋር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገው ቀጣይነት ያለው ውይይት ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ እንደ ሆነ ገልጸው ለቤተ ክርስቲያኗ እና ለአገሪቱ ለቻይና ሪፖብሊክ  መልካም ፍሬ ማፍራት እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል። በመቀጠልም ከቫቲካን ጋር እስካሁን ድረስ ስምምነት የሌላቸው የአፍሪካ አገራት ጋር ስምምነት ይፈረም ዘንድ ቫቲካን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደ ሆነች ጨምረው ገልጸዋል።

የዚህ ዘገባ አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ከቻይና ጋር እ.አ.አ. በመስከረም 22/2018 ዓ.ም በቤጅንግ የተፈረመውን ስምምነት ተግባራዊ በሆነ መልኩ ለመጀመር “በአሁኑ ጊዜ በቻይና ውስጥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ሹመትን ለመፈፀም የሚያስችል ጊዜያዊ ስምምነት ማድረጉ አስፈላጊ ነው፣ በዚህም የስምምነቱን ተግባራዊነት ማረጋገጥ ይቻላል” በማለት ከጉባሄው በኋላ በተለይ ለቫቲካን ዜና የተናገሩት ካርዲናል ፓሮሊን “ይህ ረጅም ጊዜ የፈጀ ሥራ የተካሄደበት  በመጨረሻም ለእኛ ቤተ ክርስቲያን እና ለአገሪቱ መልካም ፍሬዎች የሚያስገኙ ውጤቶችን ማምጣት እንችላለን ብለን ተስፋ የምናደርግበት ስምምነት ነው” ብለዋል።

መግባባት ላይ ያልተደርሰባቸው ሁለት ጉዳዮች

“ለሐይማኖት ዝግ ከሆነ አገር ወደ የሐይማኖት ነጻነት”  የሚሉት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ከቻይና መንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት ላይ "እነዚ ሁለት ጉዳዮች በሁለቱም ወገኖች የጋራ አቋም ላይ ተደርሶ ዕውቅና ያልተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን” የገለጹት ካርዲና ፔትሮ ፓሮሊን እነዚህ አስፈላጊ እና ዋና ዋና የሆኑ ጉዳዮች በቀጣይነት ውይይት የሚደርግባቸው እንደ ሆነ ጨምረው ገልጸዋል።

ለሐይማኖት ነፃነት እና ለጋራ ጥቅም የተደርጉ ስምምነቶች

“የሐይማኖት ነጻነትን በመለከተ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን ያለምንም ጣልቃ ገብነት በቻይና ማከናወን ትችል ዘንድ በተዳጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን”  የገለጹት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ይህም ጥያቄ የካቶሊክ እምነትን ብቻ የተመለከተ ጉዳይ ሳይሆን የማነኛውም ዓይነት ሐይማኖት ተከታይ በቻይና እምነቱን በነጻነት ያካሂድ ዘንድ የሚጠይቅ እንደ ሆነ ገልጸው ይህም ለአገሪቷ እና ለሕዝቦቿ ጭምር በሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ሰንድ ላይ “Gaudium et spes ላይ እንደ ተጠቀሰው “በተቀናጀ መልኩ ሁለንተናዊ ማለትም መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ልማትን ለማጎልበት እና ሰላምን ለማጠናከር የሚረዳ” መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በቁጥር አነስተኛ ካቶሊኮች የሚኖሩባቸው አገራት

በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የካቶሊክ ምዕመናን ከሚኖሩባቸው አገራት ጋር ስምምነት ማደርግን በተመለከተ የተናገሩት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እ.አ.አ 1964 ዓ.ም ከቱኒዚያ ጋር፣ እ.አ.አ. 1983 ዓ.ም ከሞሮኮ ጋር፣ እ.አ.አ. 1993 ከእስራኤል ጋር፣ በመጨረሻም እ.አ.አ 2015 ዓ.ም ከፍልስጤም ጋር የተፈረሙ ስምምነቶች እንደ ሚገኙ የገለጹት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ባለፉት አመታት ውስጥ ቫቲካን ክርስቲያን ካልሆኑ አገራት ጋር ጭምር ስምምነት ለመፈራረም ሙከራ መደረጓን ጨምረው ገልጸዋል።  

ቫቲካን ከቻይና መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት የምታደርገው ለምንድነው? ቅድስት መንበር ከቻይና መንግሥት ጋር የምታደርገውን ውይይት የጋራ መተማመን ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው። በቻይና የሚኖሩ የካቶሊክ እመነት ተከታይ የሆኑ ምዕመናን ምንም እንኳን በሐይማኖታቸው የተነሳ ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ቢደርስባቸውም ለእምነታቸው ታማኝ ሆነው ቆይተዋል። ታዲያ እንደነዚህ ዓይነት ውይይቶች ምን ሊያስገኙ ይችላሉ?

ውይይቶች ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ናቸው!

ውይይቶች ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት መሠረታዊ የሆኑ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ውይይት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥም ሆነ በአለም ውስጥ ካለው ግንኙነት አኳያ የቤተ ክርስቲያኗን የአኗኗር ዘዴ የሚደግፍ አስፈላጊ ነገር ነው። መወያየት ማለት ከሕብረተሰብ፣ ከሃይማኖቶች እና ከባህሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ማለት ነው። የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ሰነድ እንደ ሚያመለክተው ውይይት ሐዋሪያዊ የሆነ ተግባር መሆኑን የገለጸ ሲሆን ይህ ውይይት በብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን ነገር ግን ክርስቲያን ካልሆኑ የማኅበርሰብ ክፍሎች፣ ከሲቪል ባለስልጣኖች እና ከሁሉም በጎ ፈቃድ ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረግ እንደ ሆነ ይገልጻል። ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ሰነዶች መካከል “በዚህ ዘመን የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን” (Gaudium et Spes no.21) በተሰኘው ሰነድ ውስጥ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እንዳሰፈረው “ለሁሉም ሰዎች፣ አማኞች እና እምነት የሌላቸው ሰዎች ጭምር አብሮ የሚኖሩባትን ዓለም ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋጾ ማድረግ ይኖርባቸዋል፣ ይህ ያለ እውነተኛ እና በጥበብ መንፈስ ከሚደረግ ውይይት ውጪ እውን ሊሆን አይችልም” (21) ይላል።

“ቤተክርስቲያን ራሷ ከምትገኝበት ከአለም ጋር መወያየት ይኖርባታል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ “Ecclesiam Suam” በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም (የራሱ (የክርቶስ) ቤተ ክርስቲያን) በሚል አርእስት በጻፉት ሐዋሪያዊ መልእክት ላይ ይህንን በተመለከተ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ “ቤተክርስቲያን ራሷ ከምትገኝበት ከአለም ጋር መወያየት ይኖርባታል። ቤተ ክርስቲያን ስትናገር ራሷ መልእክት ትሆናለች” (ቁ.67) በማለት ያስቀምጣል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “መልካም ፈቃድ ካላቸው፣ በራሷ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ይሁን ከራሷ ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር የሚደረጉትን ውይይቶች ለመደገፍ ዝግጁ ናት” (97)።

በሰዎች፣ በተቋማት እና በማህበረሰቦች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች የጓደኝነት ስሜት ሊፈጥሩ የሚችሉ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ያደርጋሉ። በማነኛውም ሁኔታ ገንቢ የሆነ ውይይት ለማድረግ በቅድሚያ መተማመን ያስፈልጋል። የጋራ መተማመን የብዙ ትናንሽ የሚባሉ እርማጃዎች፣ እንቅስቃሴዎች እና ግንኙነቶች ፍሬ ሲሆን ይህም በተደጋገሚ በረጋ መንፈስ እና በከፍተኛ ጥበብ የሚፈጸም ተግባር ሊሆን ይገባል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 8/2009 ዓ.ም እንደ ተናገሩት “ሁልጊዜም ቢሆን ያልተዘጉ በሮች አሉ" በማለት ሁሌም ለውይይት በራችንን መክፈት እንደ ሚገባን ያመለክታሉ።

ቤተ ክርስቲያን ከቻይና መንግሥት ጋር የምታደርገው ውይይት ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ያስፈልገዋል

በቅርብ ጊዜያት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለምሳሌም ብጹዕ ጳውሎስ 6ኛ ከቻይና ጋር ጥንቃቄ የተሞላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀመር በማድረግ በቀጣይነት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዴክቶስ 16ኛ ከቻይና መንግሥት ጋር የሚደረገውን ውይይት ውጤታማ እንዲሆን ግልጽ አቅጣጫ በመስቀመጣቸው የተነሳ  ምስጋና ይድረሳቸውና በአሁኑ ወቅት በቅድስት መንበር እና በቻይና መንግሥት መካከል በተወሰነ መልኩም ቢሆን ውይይት ለማድረግ የተቻለ ሲሆን እያንዳንዱ ውይይት የራሱ የሆነ አዲስ መንገድ የከፈተ እና በሚገነባው የጋራ ግንኙነት ላይ የራሱን አዲስ ጡብ  ወይም የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጠ በተስፋ የተሞላ የመነቃቂያ ሐሳቦችን ያፈለቀ እና እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ያስቻለ አጋጣሚ ነው። በጣም በቅርብ ጊዜ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን ግላዊ ሕይወት፣ አስተምህሮ እና አቀራረብ በመመልከት ቻይናን ጨምሮ በብዙ ሕዝቦች እና ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ የውይይት መድረኮች እንዲከፈቱ በማበረታታት ላይ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያን የምታደርጋቸው ውይይቶች በእውነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው  

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውይይትን በራሱ እንደ አንድ መቋጫ ወይም መደምደሚያ ግብ አድርጋ አትመለከትም። ያላትን ሁሉ አቅም ተጠቅማ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ጥቅሞችን ለማግኘት “አስፈላጊ የሆኑትን መሰረታዊ መርሆች አሳልፋ ለመስጠት ተዘጋጅታለች ማለትም አይደለም። ይህንን ጉዳይ ከቻይና ጋር በተያያዘ መልኩ ስንመለከተው በቻይና በሚገኙ የካቶሊክ ማኅበርሰቦች ላይ የደረሰውን  መከራ መርሳት ማለት አይደለም። ቤተ ክርስቲያን የምታደርጋቸው ውይይቶች ሁልጊዜም ቢሆን በእውነት እና በፍትህ ላይ የተመሰረቱ፣ ከሰው ልጅ ጋር ሊነጣጠል በፍጹም የማይችለውን መልካም ጎን እና መሠረታዊ መብቶችን በማስከበር ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው። አንድ ግልጽ ሊሆን የሚገባው አስፈላጊ ነገር ቤተክርስቲያን በቻይና የምታደገው ተልዕኮ የመንግሥት መዋቅሮችን ወይም አስተዳደሮችን ለመቀየር ወይም የፖለቲካ ኃይል ለማዋቀር ወይም ባለሥልጣኖችን ለመቃወም ያለመ እንዳልሆን ልብ ሊባል ይገባዋል። ቤተክርስቲያን ተልዕኮዋን  በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አከባቢ የምታደግ ከሆነ የራሷን ትክክለኛ ማንነት በመካድ ከብዙ የፖሌቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ልክ እንደ አንዱ ተፎካካሪ በመሆን፣ መለኮታዊ የሆነውን ጥሪ በመርሳት ወይም በመካድ፣ በእንደነዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመግባት ለጊዜያዊ ጥቅሞች ማስፈጸሚያንት ያለሙ ተግባራት ውስጥ በፍጹም አትሳተፍም።

ቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ እና ሐቀኛ የሆኑ ውይይቶችን ማድረግ ትፈልጋለች

ትክክለኛ እና ሐቀኛ የሆኑ ውይይቶች ቤተ ክርስቲያን በማኅበርሰቡ ውስጥ ሆና መሥራት እንድትችል የሚያደርጋት ሲሆን ይህም ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ሕጋዊ የሆነ ጥበቃዎችን በማድረግ የጋራ ጥቅሞች ዙሪያ እንድትሠራ ያስችላታል። በዚህ አግባብ ቤተ ክርስቲያን የትችት/ሂስ ቃላቶችን በምትናገርበት ወቅት ዓላማዋ ውዝግብ ለመፍጠር ሳይሆን ትክክለኛ እና ገንቢ መንፈስ ያለው ኅብረተሰብ ለመፍጠር በማሰብ የምታደገው ነው። ትችቶች/ሂስ ተጨባጭ የሆኑ የሐዋሪያዊ ሥራዎች የፍቅር መገለጫ ተመክሮዎች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ፣ ምክንያቱም ደካማ የሆኑ ሰዎችን ስቃይ፣ ድምጻቸውን ለማሰማት የተሳናቸው ሰዎች ድምጻቸው እንዲሰማ ጥንካሬን ስለሚፈጥር ነው።

ቅድስት መንበር ከቻይና ጋር በእውነተኛ መንፈስ የሚደረጉ ውይይቶችን አጠናክራ ትቀጥላለች

ከቻይና ጋር በተያያዘ መልኩ የቅድስት መንበር ያላት አቋም እና እምነት በአክብሮት እና በእውነተኛ መንፈስ የሚደረጉ ውይይቶች ምንም ያህል አስቸጋር እና አደገኛ ቢሆኑም እንኳን በእዚህ አኳኅን የሚደረጉ ውይይቶች እንዲካሄዱ ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች በማሰናዳት እንዲካሄዱ የምትጥር ሲሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ ውይይቶችን በማድረግ ሐሳቦችን በመቀያየር እና በመግባባት ግንዛቤን በመፍጠር በመኃል ያሉትን አለመግባባቶችን በመፍታት ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንደ ሚፈጠር ታምናለች።

ቫቲካን በተለሳለሰ መልኩ የምታከናውነውን ተግባር ቻይና በጥንቃቄ ትመለከተዋለች

ቅድስት መንበር “በተለሳለሰ ኃይል” በዓለም ደረጃ እያከናወነች የምትገኘውን እንቅስቃሴ ቻይና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እየተከታተለች መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ ምልክቶች አሉ። የቻይና ታሪክ በተመሳሳይ መልኩ እየቀጠለ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠሩ ሰዎች በጥበብ የተሞላ ውሳኔዎችን ማድረግ ይኖርባቸዋል። የቅድስት መንበር ከቻይና መንግሥት ጋር ለሩብ ምዕተ አመታት ያህል ውይይት ስታደግ የቆየችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፣ በዘመናት ውስጥ ያሉትን ምልክቶች ለማንበብ ለሚፈልጉ እና በታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘት ለመገንዘብ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ የቤተክርስቲያኗ ሐዋሪያዊ ዓላማ ይህ መሆኑን ያሳያል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከቻይና መንግሥት ጋር በቻይና የሚገኙትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮችን በተመለከተ በተደጋጋሚ ውይይት እያደረገች እንደ ምትገኝ የሚታወቅ ሲሆን በቻይና የሚገኙትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጉዳይ በተመለከተ ከዚህ ቀደም በርካታ ውይይቶች ከቻይና መንግሥት ጋር መደረጋቸው ይታወሳል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 March 2019, 15:16