ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እና የኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ በሆስፒታሉ 150ኛ ዓመት መታሰቢያ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እና የኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ በሆስፒታሉ 150ኛ ዓመት መታሰቢያ፣ 

ካርዲናል ፓሮሊን ቤተክርስቲያን ለሕሙማን የምትሰጠውን ትኩረት እንደማታቋርጥ አስታወቁ።

በማቴዎስ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ታምሜ ጠይቃችሁኛል” ያለውን ያስታወሱት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በብዙ ሐዋርያዊ መንገዶች ተመልክታዋለች ብለው ከእነዚህም መካከል ለሆስፒታሎች እና ለሕክምና ተቋማት እገዛን በማድረግ፣ አገልግሎታቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ፣ የሰው ልጅ ማግኘት ያለበት የፍቅር አገልግሎት እንዳይቋረጥ ቤተክርስቲያን ዘወትር ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከተማ የሚገኘውን የሕጻናት ሕክምና አገልግሎት መስጫ ሆስፒታል 150ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ንግግራቸውን ያሰሙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ቤተክርስቲያን ለሰብዓዊ ፍጥረት ያላትን ክብር፣ ለሕሙማን የምትሰጠውን ትኩረት የማታቋርጥ መሆኑን አስታወቁ።

በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኝ እና “ባምቢኖ ጄሱ” ወይም “ሕጻኑ ኢየሱስ” በመባል የሚታወቀው እና ለሕጻናት በሚሰጠው የሕክምና አገልግሎቱ በስፋት የሚታወቀው ይህ ሆስፒታል፣ ከሕጻናት ለሕጻናት በተደረገ ስጦታ በመታገዝ ከ150 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ሆስፒታል መሆኑ ታውቋል። አንድ ዘመን ከግማሽ ያስቆጠረው ይህ ሆስፒታል ለሕጻናት በሚሰጠው የረጅም ጊዜ ልምዱ ሕጻናትን በማከም እና በመንከባከብ፣ የተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን በማካሄድ አሁን ወደሚገኝበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ከሆስፒታሉ ታሪክ ለመረዳት ተችሏል።  

በፍቅር ዓይን መመልከት፣

የሆስፒታሉን የሥራ አፈጻጸም፣ በሆስፒታሉ ውስጥ የተካሄዱ ሳይናሳዊ ምርምሮችን፣ የአገልግሎት እቅዱንም ለመግለጽ ተብሎ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ወይዘሮ ጁሊያ ግሪሎ፣ የላሲዮ ክፍለ ሀገር ፕሬዚደንት አቶ ኒኮላ ዚንጋሬቲ፣ የሮማ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ቨርጂኒያ ራጂ እና የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማሪዬላ ኤኖክ የተገኙ ሲሆን በወቅቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከውን የምስጋና መልዕክት እና ቡራኬን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ለስብሰባው ተካፋዮች አድረሰዋል። ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ለስብሰባው ተካፋዮች ካሰሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ቤተክርስቲያን ለሕሙማን የምትሰጠው ትኩረት በፍቅር የተሞላ እና ሐዋርያዊ ዓላማ እና ትርጉም ያለው በመሆኑ ምን ጊዜም ቢሆን አታቋርጠውም ብለዋል።  

ለሰው ልጅ ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል፣

የታመሙትን መጎብኘት እና መጠየቅ ስጋዊ ድነት የሚገኝበት የፍቅር ተግባር በመሆኑ ክርስቲያኖች በግልም ሆነ በጋራ ሆነው ማከናወን ይጠበቅባቸዋል በማለት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አሳስበዋል። ንግግራቸውን በመቀጠል በማቴዎስ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ታምሜ ጠይቃችሁኛል” ያለውን ያስታወሱት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በብዙ ሐዋርያዊ መንገዶች ተመልክታዋለች ብለው ከእነዚህም መካከል ለሆስፒታሎች እና ለሕክምና ተቋማት እገዛን በማድረግ፣ አገልግሎታቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ፣ የሰው ልጅ ማግኘት ያለበት የፍቅር አገልግሎት እንዳይቋረጥ ቤተክርስቲያን ዘወትር ጥረት ታደርጋለች ብለዋል። በዚህ ጥረቷ በኩል በተለይ የደከሙትን በመደገፍ እና ደጋፊ ለሌላቸው ፈጥና በመድረስ የፍቅር አገልግሎቷን ታበረክታለች ብለዋል።

የሆስፒታሉ ዓለም አቀፍ ተልዕኮ፣

በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኝ ይህ የሕጻናት ሕክምና መስጫ ሆስፒታል ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሕክምናን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ሆስፒታሉ ባሁኑ ጊዜ በካንቦዲያ፣ በመካከለኛ አፍሪቃ ሪፓብሊክ፣ በዮርዳኖስ፣ በሶርያ፣ በሕንድ፣ በታንዛኒያ፣ በጆርጂያ፣ በሩሲያ፣ በቻይና እና በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። ሆስፒታሉ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት የዘር እና የሐይማኖት ልዩነት ወይም ድንበር ሊገታ እንደማይችል ገልጸው በቅርቡ በመካከለኛ የአፍሪቃ ሪፓብሊክ ዋና ከተማ በሆነው በባንጊ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የሕጻናት የሕክምና ማስጫ ሆስፒታል አስታውሰዋል።                      

19 March 2019, 18:10