ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ እና የአሌክሳንድሪያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ሁለተኛ ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ እና የአሌክሳንድሪያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ሁለተኛ  

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ በግብጽ ጉብኝት ማድረጋቸው ተገለጸ።

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ ለአሌክሳንድሪያውን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወ ቅዱስ ታዋድሮስ ሁለተኛን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከላቸውን ሰላምታ አቅርበው በአቡ ዳቢ ከተማ የተደረገውን ስምምነት የሚያስታውስ ሰነድ እና ሜዳሊያ አበርክተውላቸውል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ሁለተኛ በበኩላቸው ለጋራ ውይይቶች መሠረት የሆኑ አራት ጉዳዮችን ጠቅሰው እነርሱም እውነተኛ ወዳጅነት፣ እያንዳንዱ ሐይማኖት የራሱን የእምነት ባሕል ጠንቅቆ ማወቅ፣ የጋራ ውይይት እና ጸሎት መሆናቸውን ገልጸው እነዚህም በመንፈስ ቅዱስ የታገዙ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረገውን የጋራ ውይይት አጠናክረው ለመቀጠል፣ በአመጽ ምክንያት በበርካታ ምእመናን ላይ የሚደርሰውን ስቃይ በሕብረት ለማስታወስ በማለት ሁለቱ የሐይማኖት አባቶች እርሱም በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ እና የአሌክሳንድሪያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወ ቅዱስ ታዋድሮስ ሁለተኛ ትናንት እሑድ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. በግብጽ መገኘታቸውን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጿል። ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ወደ ግብጽ ያደረጉት ጉዛ ዋና ዓላማ በግብጽ ዳሚዬታ በተባለ አካባቢ ከዛሬ 800 ዓመት በፊት በኢጣሊያ የአሲዚ ከተማ ተወላጅ የሆነው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የግብጹ ሱልጣን ማሊክ አል ካሚል የተገናኙበትን እለት ለማስታወስ እንደሆነ ታውቋል።

የአቡ ዳቢው የወንድማማችነት ስምምነት ሰነድ፣

ሁለቱ የሐይማኖት አባቶች በካይሮ እና በአሌክሳንድሪያ መካከል በሚገኝ የቅዱስ ቢሾይ ገዳም ውስጥ የተገኛኙ ሲሆን በዕለቱ ለብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ እና ከእርሳቸው ጋር ለተጓዙት የቅድስት መንበር ልኡካን በሙሉ ከፍተኛ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ሁለቱ የሐይማኖት አባቶች ተገናኝተው ሃስብ በተለዋወጡበት ወቅት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ በቅርቡ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል ከጥር 26 – 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በጋራ ሆነው ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚለውን የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውንም አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ ጨምረው እንዳስገነዘቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፈረሙት የወንድማማችነት ሰነድ በክርስትና እና በእስልምና የሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚታየውን የመቀራረብ ተስፋን የሚያድስ፣ የዓለም ሕዝቦች ለሰላም እና ለእርቅ በሕብረት ለመሥራት እየተወሰደ ያለውን ጥረት የሚያሳድግ እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ ለአሌክሳንድሪያውን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወ ቅዱስ ታዋድሮስ ሁለተኛን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከላቸውን ሰላምታ አቅርበው በአቡ ዳቢ ከተማ የተደረገውን ስምምነት የሚያስታውስ ሰነድ እና ሜዳሊያ አበርክተውላቸውል።

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ሁለተኛ የእርስ በእርስ ትውውቅ እና ጸሎት አስፈላጊ ናቸው፣

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ሁለተኛ በበኩላቸው ለጋራ ውይይቶች መሠረት የሆኑ አራት ጉዳዮችን ጠቅሰው እነርሱም እውነተኛ ወዳጅነት፣ እያንዳንዱ ሐይማኖት የራሱን የእምነት ባሕል ጠንቅቆ  ማወቅ፣ የጋራ ውይይት እና ጸሎት መሆናቸውን ገልጸው እነዚህም በመንፈስ ቅዱስ የታገዙ መሆን አለባቸው ብለዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ሁለተኛ አክለውም መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስትቲያን በግብጽም ሆነ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከሌሎች የሐይማኖት ተቋማት ጋር ጎን ለጎን መጓዟ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። በአገራቸው በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን ያስታወሱት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ሁለተኛ፣ በቤተክርስቲያናቸው ምእመናን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ወንድማማች የሆነውን የግብጽ ሕዝብ ለመለያየት የሚደረግ ፖለቲካ አዘል እንቅስቃሴ እንደሆነ አስረድተዋል።

በኢጣሊያ ውስጥ በባሪ የተደረገውን

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ሁለተኛ እንደገለጹት ከአገር ውጭ የሚገኝ የኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ምእመናን እና ካህናት ቁጥር እያደገ መሆኑን ገልጸው በውጭ አገር የሚገኙ ምእመናንን የሚከታተሉ የብጹዓን ጳጳሳት ቁጥርም ከ 3 ወደ 35 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል። በኢጣሊያ፣ ባሪ ከተማ ያለፈው አመት በሐምሌ ወር ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ፓትሪያርኮች እና ብጹዓን ጳጳሳት ለጋራ ጸሎት መገናኘታቸውን አስታውሰዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 March 2019, 15:47