ፈልግ

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቃወመው ዓለም አቀፍ ቀን ታስቦ ዋለ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቃወመው ዓለም አቀፍ ቀን ታስቦ ዋለ 

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቃወመው ዓለም አቀፍ ቀን ታስቦ ዋለ

በየካቲት 1/2011 ዓ.ም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነቱን በማስመልከት በዓለም ዙሪይ በሚገኙ የዓለማችን ማኅበርሰቦች ዘንድ ስለ ሁኔታው አስከፊነት ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲቻል በማሰብ የሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሕገውጥ የሰዎች ዝውውር ቀን ተዘክሮ ማለፉን ለቫቲካን ዜና ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን በተመለከተ በቅድስት መንበር ሥር የሚተዳደረው እና የሰዎች ሁለንተናዊ ሰብዓዊ እድገት የሚመለከተው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ የሆኑት አባ ሚካኤል ቼርኒ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደ ገለጹት “በአሁኑ ወቅት በዓለም በሰብአዊነት ላይ በጭካኔ መንፈስ የሚደረጉ ግድያዎች እና በደሎች ካሁኑ ካልተገቱ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ ዙሪያ የተሰማሩ ሰዎች መጪውን የዓለም የኢኮኖሚ ኃይል የመቆጣጠር ጉልበት ሊያዳብሩ እንደ ሚችሉ” ያላቸውን ሥጋት ጨምረው ገልጸዋል።

“እነዚያን ሲያፌዙብኝ እና እነዚያን ሲያሰቃዩኝ የነበሩትን ሰዎች ባገኛቸው፣ ተንበርኪኬ እጆቻቸውን መሳም እጀምራለሁ፣ ምክንያቱም ይህንን በደል ባይፈጸሙብኝ ኖሮ የክርስትናን ሐይማኖት ባለተቀበልኩኝ፣ የምንኩስና ሕይወት ባልጀመርኩ ነበር” በማለት ተናግረው የነበሩት ቅድስት ባኪታ እንደ ነበሩ የሚታወስ ሲሆን እኝህ ቅድስት እ.አ.አ. በ1869 ዓ.ም በአሁኑ በደቡብ ሱዳን በዳርፉር ተወልደው የነበሩ፣ ከወላጆቻቸው እጅ ታፍነው ተወስደው በወቅቱ የባሪያ ንግድ ስያጧጡፉ በነበሩ ሰዎች ምክንያት ተሽጠው በልጅነታቸው የባርነት ሕይወት አሳልፈው ያለፉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የእኝህ ቅድስት ዓመታዊ በዓል በየካቲት 1/2011 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። የቅድስት ባኪታ አመታዊ በዓል በሚከበርበት ወቅት እርሳቸው በሕይወታቸው በባርነት ቀንበር ሥር እንደ ነበሩ እና የባሪያ ንግድ ሰለባ መሆናቸውን በማስታወስ፣ በዛሬው ዘመናዊ በሚባለው ዓለማችን ውስጥ ሳይቀር በአሁኑ ወቅት በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የተነሳ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በሕገወጥ መንገድ በመዘዋወራቸው ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ለዘመናዊ ባርነት እየተጋለጡ የሚገኙ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በስቃይ ውስጥ እንደ ሚገኙም ይታወቃል።

አለመታደል ሆኖ ቅድስት ባኪታ የባሪያ ንግድ ሰለባ በመሆን ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ከደረሰባቸው በኋላ ያንን ስቃይ ሁሉ ተቋቁመው በመጨረሻ የክርስትና እምነት ከተቀበሉ በኋላ ሕይወታቸውን በእመንት ዓይን በመመልከት በታላቅ ትዕግስት ከባርነት ቀንበር ስር ለመውጣት እንደ ቻሉ ሁሉ፣ ዛሬም ቢሆን በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች የተነሳ አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ በርካታ ሰዎች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ምክንያት በሚደርሳባቸው ከፍተኛ በደል የተነሳ ለዘመናዊ ባርነት እየተጋለጡ፣ በከፍተኛ ስቃይ እና መከራ ውስጥ እንደ ሚገኙ ይታወቃል።

የካቲት 01/2011 ዓ.ም የቅድስት ባኪታ አመታዊ በዓለ በሚዘከርበት ወቅት ከዚህ ቀን ጋር መሳ ለመሳ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመቃወም ስለ ጉዳዩ አስከፊነት እና ኢሰባዊ ድርጊት መሆኑን በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ታስቦ የሚውል ቀን ሲሆን የሰው ልጆች “ሰው” በመሆናቸው ብቻ ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ መኖር ሲገባቸው የሰው ልጆች በሰው ልጆች አማካይነት ዛሬም ቢሆን በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ተዘፍቀው እንደ ሚገኙ የአደባባይ ምስጢር ነው።

በቅድስት መንበር ሥር የሚተዳደረው እና የሰዎች ሁለንተናዊ ሰብዓዊ እድገት የሚመለከተው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ የሆኑት እና በተጨማሪም የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂ ሰዎች ጉዳይ የሚመለከተው ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አባ ሚካኤል ቼርኒ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደ ገለጹት “ዛሬ የሚከበረው የቅድስት ባኪታ ዓመታዊ በዓል እርሳቸው በሕይወት ዘመናቸው እኛ ማሰብ ክምንችለው በላይ ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ደርሶባቸው የነበረ ሲሆን ነገር ግን እነዚህን ሁሉ መከራዎችን እና ስቃዮች ተቋቁመው የክርስትናን እምነት ተቀብለው፣ ገዳማዊት ሆነው በመጨረሻም ለቅድስና ማዕረግ መብቃታቸውን” ገልጸዋል። ይህንን የእርሳቸውን አመታዊ በዓል በማክበር ላይ በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በመቃወም የሚዘከረው ቀን ላይ እኛም የጉዳዩን አስከፊነት በሚገባ ለመረዳት እንችል ዘንድ፣ ዓይናችን ይከፈት ዘንድ፣ ጸሎት ማድረግ እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን በዚህም መልኩ ዓይኖቻችንን በመክፈት በአከባቢዎቻችን እየተፈጸሙ የሚገኙትን ተግባራት በሚገባ በመመልከት ችግሩን በጋራ ለመፍታት የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

ይህንን አስከፊ ሁኔታ በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 30/2011 ዓ.ም በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት እኛ በዓይናችን የማናያቸው ነገር ግን ይህንን አስገዳጅ የስደተኞች ፍልሰት አጋጣሚውን በመጠቀም ወንዶችን፣ ሴቶችን እና ሕጻናትን ሳይቀር ለአስገዳጅ የጉልበት ሥራ፣ አስገዳጅ የወሲብ ሥራ፣ የአካል ክፍሎችን በሕገወጥ መልክ ከሰዎች አካል ላይ በመንቀል በሕገወጥ መልክ ለንግድ በማቅረብ ሥራ፣ አስገዳጅ በሆነ መልኩ በልመና ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የማደርግ ሥራ ወይም አስገዳጅ በሆነ መልኩ በወንጅል ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ የማስገደድ ሥራ በመሥራት ከእነዚህ ዘርፎች ተጠቃሚ የሚሆኑ የተደራጁ ወንጀለኞች እንደ ሚገኙ ቅዱስነታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

09 February 2019, 08:59