ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ስብሰባ ላይ፣ 2009 ዓ. ም.  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ስብሰባ ላይ፣ 2009 ዓ. ም.  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የዓለማችን ደሆች ተረስተው እንዳይቀሩ አደራ”!

የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የእርሻ ምርታቸውን እንዲያሳድጉ፣ የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም እንደሆነ የገልጹት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ ይህም በዓለማችን 70 ከመቶ የሚሆነውን ደሃ የገጠር አርሶ አደር ነዋሪን ለመርዳት የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ድርጅት በመሆኑ አገልግሎቱ የጎላ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ ኢፋድ እያካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ ነገ ሐሙስ የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው መልዕክት እንደሚያስተላልፉ፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አረላኖ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ ኢፋድ በ42ኛ ዙር የዳይሬክተሮች ቦርድ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች የምርት መጠንን እና ጥራትን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ላይ እንደሚወያይ ታውቋል። ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ባሁኑ ጊዜ በ181 አገሮች ጽሕፈት ቤቱን ከፍቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። ስብሰባውን ከሚካፈሉ የአባል አገራ ተወካዮች በተጨማሪ የዶሜኒካን ሪፓብሊክ ፕሬዚደንት፣ የሩዋንዳ የግብርና ሚኒስትር እና የኢጣሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ጁሴፐ ኮነቴ እንደሚገኙ ታውቋል።

ወጣቶችን በዘመናዊ የምርት አቅርቦት ሥራ ማሰማራት፣

የስብሰባው ተካፋዮች ትኩረት ሰጥተውበት ከሚወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው፣ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ገጠራማ አካባቢዎች በሚከናወን የግብርና አገልግሎት ላይ የሚውለውን መዋዕለ ንዋይ በማሳደግ ወጣቶችን በዘርፉ በስፋት ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ፣ ይህም የአፍሪቃ ወጣቶችን ስደት ለመቀነስ እንደሆነ ታውቋል። በመርሃ ግብሩ መሠረት እስከ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየው፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ስብሰባ ዓላማ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ውስጥ አዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በገጠራማው አካባቢዎች በመዘርጋት አነስተኛ የንግድ ተቋማት የሥራ ዕድሎችን እንዲከፍቱ እና እንዲያመቻቹ ለማድረግ ነው ተብሏል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብሰባው ላይ መገኘት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከ2006 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ 2009 ዓ. ም. ድረስ በተካሄዱት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ስብሰባዎች ያስተላለፏቸውን መልዕክቶች ያስታወሱት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አረላኖ በዘንድሮ ስብሰባ ወቅትም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት በጉጉት እንደሚጠበቅ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አክለውም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት የጋራ ውይይቶች አስፈላጊ እንደሆኑ፣ በአገሮች እና በሕዝቦች መካከል ሕብረት እና መተጋገዝ ሊኖር እንደሚገባ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ልዩነቶች እየተስፋፉ ከመጡ የሚፈለገውን እድገት በዓለማችን ማምጣት አይቻልም ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ንግግራቸውን በመቀጠል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ከተመሠረተበት ከ1969 ዓ. ም. አንስቶ በቅድስት መንበር እና በግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ መካከል ያለው ግንኙነት የጠበቀ እንደሆነ አስረድተው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ለድርጅቱ ማደግ ያበረከቱት አስተዋጽዖ ሰፊ እንደነበር አስታውሰዋል።         

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የእርሻ ምርታቸውን እንዲያሳድጉ፣ የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም እንደሆነ የገልጹት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ ይህም በዓለማችን 70 ከመቶ የሚሆነውን ደሃ የገጠር አርሶ አደር ነዋሪን ለመርዳት የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ድርጅት በመሆኑ አገልግሎቱ የጎላ ነው ብለዋል። ቅድስት መንበርም ይህን በሚገባ በመገንዘብ ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ፣ ከዚያ በፊትም ከ1956 ዓ. ም. ጀምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ለሰው ልጆች ሕይወት ሊሰጥ የሚገባውን ክብር በማስቀደም፣ አውዳሚ የጦር መሣሪያ ምርትን ከማሳደግ ይልቅ የእርሻ ምርትን ለማስደግ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በገጠራማው አካባቢ በሚኖሩ ማሕበረሰብ መካከል በመዘርጋት ማገዝ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

ሰብዓዊ መብትን ማክበር፣ ደሃ እና አቅበ ደካማ ለሆኑት ድጋፍ ማድረግ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወጣትነት ዕድሜአቸው ጀምረው የጣሩበት የአግልግሎት ዘርፍ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ፣ ቅዱስነታቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ስብሰባ ላይ በሚገኙበት ጊዜ ከገጠራማው አካባቢ ከመጡትን የአርሶ አደር ተወካዮች ጋር እንደሚገናኙ ገልጸው፣ በጥቅምት ወር 2012 ዓ. ም. በአማዞን አካባቢ አገሮች ስለሚካሄደው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በተመለከተ እንደሚወያዩ ገልጸዋል።

እነዚህ አካባቢዎች ለም እና ለግብርና ምርት ምቹ ቢሆኑም በርካታ ወጣቶች አካባቢውን ለቀው የሚሰደዱበት በመሆኑ ይህ እንዳይሆን በወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በተወለዱበት አካባቢ የሥራ ዕድልን መፍጠር፣ የትምህርት እና የስልጠና እድሎችን ማመቻቸት፣ ወጣቶችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በመንግሥታት መካከል እንዲሁም በሕዝቦች መካከል መተጋገዝ እንዲኖር በማድረግ፣ የገንዘብ ድጋፍን በማሳደግ ልማትን ማምጣት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ዓላማ ቢሆንም በተለይ ሕብረት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ አሳስበው ያለ መተጋገዝ ልማትን ማምጣት አይቻልም ብለዋል። በተለይም ልማትን ለማምጣት የሚያግዙ የተለያዩ የሥራ ፈጠራ እቅዶች፣ የአዳዲስ ሃሳቦች እና የአመለካከቶች ጥምረቶች በመሆናቸው መጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 February 2019, 15:12