ፈልግ

ሊቀ ጳጳሳት ፖል ሪቻርድ ጋላጌር፣ ሊቀ ጳጳሳት ፖል ሪቻርድ ጋላጌር፣  

ሰብዓዊ መብቶች እና በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረጉ ውይይቶች የሰላም እና የእድገት መሠረቶች ናቸው።

መሠረታዊ የሆኑ የሰው ልጆች ዓለም አቀፍ መብቶችን ማስከበር እና መንከባከብ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ለማሻሻል የሚያግዝ ቀዳሚ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተግባር እንደሆነ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ጋላገር በጀኔቭ በተካሄደው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነቶች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ፖል ሪቻርድ ጋላጌር፣ ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. በጀኔቭ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 40ኛ የሰብዓዊ መብቶች የምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደገለጹት፣ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር እና በእምነቶች መካከል ውይይቶችን ማድረግ ለሰላም እና እደገት መሠረታዊ እንደሆኑ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ጋላገር በገለጻቸው እንዳስረዱት የእያንዳንዱን ሰው መብት ማስከበር መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዘላቂ ሰላምን እና ሁለገብ ማሕበራዊ እድገትን ለማምጣት ዋና መንገዶች መሆናቸውን ገልጸው ይህም ከሃይማኖት ነጻነት እና በእምነቶች መካከል ከሚደረጉ ከሃሳብ ልውውጦች ሊለያይ አይችልም ብለዋል።

መሠረታዊ የሆኑ የሰው ልጆች መብቶች በአዳዲስ ሕጎች እየተጠቁ ነው፣

መሠረታዊ የሆኑ የሰው ልጆች ዓለም አቀፍ መብቶችን ማስከበር እና መንከባከብ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ለማሻሻል የሚያግዝ ቀዳሚ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተግባር እንደሆነ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ጋላገር በጀኔቭ በተካሄደው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ገልጸዋል። የእነዚህ ተግባራት ጥምረት እና ዓለም አቀፋዊነት ቅድስት መንበር በምታከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ትልቅ ቦታ የተሰጠባቸው እንደሆነ አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳሳት ጋላገር ንግግራቸውን በመቀጠል አሁን እየተከሰተ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ መሠረታዊውን የሰው ልጆች መብቶችን የሚጋፋ አንዳንድ አዳዲስ ሕጎች እየወጡ መሆናቸው ከዚህ በፊት የሰው ልጆች መብቶችን ለማስከበር ከወጡ ወይም ከጸደቁ ሕጎች ጋር ቅራኔን ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለዋል።

የሐይማኖት ነጻነት ጥያቄዎች የሚያነሱት አመጾች፣

በተለያዩ አካባቢዎች በሐይማኖት ነጻነት ጥያቄ ምክንያት የሚነሱ አመጾች ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት የገለጹት ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ጋላገር ይህም መሠረታዊው የሰው ልጆች መብቶች መጣሳቸውን ያመለክታል ብለዋል። እነዚህ መሠረታዊ መብቶች ለግለ ሰብም ቢሆን ገደብ ሊጣልባቸው እንደማይገባ አስረድተው ምእመናን በሕብረት ሆነው እምነታቸውን በነጻነት ለመግለጽ የሚያቀርቡት የመብት ጥያቄ መልስ ሊሰጠው ይገባል ብለው ይህም በዚህ ነጻነት በመታገዝ የሐይማኖት መሪዎቻቸውን ለመምረጥ እንዲሁም ዘመናዊ ሆነ ባሕላዊ የመገናኛ መንገዶችን ተጠቅመው መልዕክቶቻቸውን ማስተላለፍ ይችላሉ ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ምዕመናን በማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ መድረኮች በመገኘት ሃሳባቸውን የማጋራት መብት ሊኖራቸው ይችላል ብለዋል።

የሐይማኖት ነጻነት እና በእምነቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች የ2030 ዓ. ም. እቅድ ማሳኪያ መንገዶች ናቸው፣

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነቶች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ፖል ሪቻርድ ጋላጌር ገለጻቸውን በመቀጠል የሐይማኖት እና የህሊና ነጻነቶች በእምነቶች መካከል ውይይቶችን ለማሳደግ፣ ዘላቂ እድገትን ለማምጣት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት መሠረታዊ እንደሆኑ አስረድተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የወጠናቸውን የአራት ዓመት እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ከተፈለገ ከኤኮኖሚ እድገት ውጥኖች በተጨማሪ መንፈሳዊ፣ ስነ ምግባራዊ እና ሐይማኖታዊ አቅጣጫዎችን መመልከት እንደሚያስፈልግ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ጋላገር አሳስበዋል። ይህም በጥር ወር 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት አርብ ኤምሬቶች ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከአል አዛር ታላቁ ኢማም ከሆኑት ከአል ጣይብ ጋር በሐይማኖቶች መካከል ወንድማማችነትን ለማሳደግ ያደረጉትን ስምምነት መሠረት ያደርጋል ብለዋል።

ታዳጊ ሕጻናትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያግዝ የቅድስት መንበር ጥረት፣

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነቶች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ፖል ሪቻርድ ጋላጌር ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባቀረቡት ንግግር እንደገለጹት ቅድስት መንበር በታዳጊ ሕጻናት እና አቅመ ደካማ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል ጥረት እንደምታደርግ ገልጸው ታዳጊ ሕጻናት አገልግሎቶችን የሚያገኙባቸው የቤተክርስቲያን ተቋማት ለደህንነታቸው ሙሉ ዋስትናን እንዲሰጡ ለማድረግ ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

      

27 February 2019, 15:33