ፈልግ

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲት አውዛ በስብሰባው ላይ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲት አውዛ በስብሰባው ላይ  

በእምነቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ለሰላም አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ።

እውነተኛው ሃይማኖታዊ ርህራሄ ሁሌም እግዚአብሔርን እና ጎረቤትን እንድንወድ ያስገድደናል ያሉት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ሁሉን የሚያቅፍ ማሕበረሰብን ለመገንባት እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ የሐይማኖት መሪዎች እና የእምነት ሰዎች ከፍተኛ እገዛን ሊያበረክቱ ይችላሉ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል ከጥር 26 – 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች በጋራ ባካሄዱትን ስብሰባ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካፈላቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ወደ አቡ ዳቢ ባደረጉት 27ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከአል አዛር ታላቁ ኢማም ከሆኑት ከአል ጣይብ ጋር በመካከላቸው ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ስምምነት መፈራረማቸው ታውቋል። በሁለቱ የሐይማኖት መሪዎች መካከል የተደረሰው ስምምነት በክርስቲያን እና ሙስሊም ማሕበረሰብ መካከል ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች መካከል ሰላምን እና እርቅን ለማምጣት በጎ ፈቃድ ላላቸው በሙሉ መልካም መንገድ የሚከፍት ነው ተብሏል። በሁለቱ የሐይማኖት መሪዎች መካከል የተፈረመውን ስምምነት ያስታወሱት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲት አውዛ፣ በእምነቶች መካከል የሚደረግ ውይይት በማስመልከት በኒው ዮርክ ከተማ ላይ ትናንት ጥር 29 ቀን 2011 ዓ. ም. በተደረገ ስብሰባ ላይ መገኘታቸው ታውቋል።  

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲት አውዛ በስብሰባው ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግራቸው ትክክለኛ የሐይማኖት ትምህርት ለሰላም፣ ለእውነተኛ ነጻነት፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፣ በተለይም ለሴቶች የሥራ እና የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት፣ ሕጻናትን እና አረጋዊያንን በመንከባከብ እና ከጥቃት በመከላከል ረገድ የሚያደርገው አስተዋጽዖ ትልቅ እንደ ሆነ አስረድተዋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል አዛር ታላቁ ኢማም በሆኑት አል ጣይብ መካከል የተፈረመው እና “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ለዓለም ሰላም እና አብሮ ለመኖር በሚል ርዕስ የተፈረመውን ሰንድ ያታወሱት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ትናንት በኒዮርክ ከተማ በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ በአቡ ዳቢ ከተማ  የተከሄደው የእምነት ተቋማት እና የሐይማኖት መሪዎች ስብሰባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድ የሚካሄደውን 8ኛ ዙር የተለያዩ ሐይማኖቶች የጋራ ውይይት ሳምንትን ለማክበር ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሯል ብለዋል።

ወንድማማችነትን የሚያሳድጉ መንገዶች፣

በተለያዩ የእምነት ተቋማት መካከል የሚደረግ ውይይት በዓለም ውስጥ ሰላምን ለማምጣት መልካም መንገድ ከመሆኑም በላይ በሕዝቦች መካከል እውነተኛ እድገትን ለማምጣት እንደሚያግዝ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ አስረድተው በዓለማችን የሚነሱ የአመጽ ድርጊቶች ተገቢ እና ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የእግዚአብሔርን ስም መጠቀም ትርጉም የለውም ብለዋል። እውነተኛው ሃይማኖታዊ ርህራሄ ሁሌም እግዚአብሔርን እና ጎረቤትን እንድንወድ ያስገድደናል ያሉት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ሁሉን የሚያቅፍ ማሕበረሰብን ለመገንባት እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ የሐይማኖት መሪዎች እና የእምነት ሰዎች ከፍተኛ እገዛን ሊያበረክቱ ይችላሉ ብለዋል። “በተለያዩ እምነቶች መካከል የሚደረገውን ውይይት ማሳደግ ያስፈልጋል” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በተለያዩ የእምነት ተከታዮች እና የተለያየ ባሕል ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት የሕዝቦችን ዕለታዊ ሕይወት በመጋራት ደስታቸውንና ሐዘናቸውን በጋራ ለመካፈል ያግዛል ብለዋል።

የእርስ በእርስ ትውውቅን ማሳደግ፣

የሌላ ወገን አባል መሆን በእውነተኛ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ግልጽ እና ድፍረት የታከለበት የጋራ ውይይት ያስፈልጋል ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር በመጥቀስ የተናገሩት አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ የእምነት ነጻነትን ጨምሮ ለሰው ልጆች መብት የቆመ የጋራ ውይይት ካልተደረገ በስተቀር እውነተኛ ውይይት ተደርጓል ማለት አይቻልም ብለዋል። በመሆኑም ትክክለኛ እና እውነተኛ ውይይትን ለማድረግ የሌላውን ታሪክ እና ባሕል በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል ብለው እውነተኛ ውይይትን ማካሄድ የሚቻለው ከሁለቱም ወገኖች በኩል አንዱ ስለ ሌላው ለማወቅ በሚያደርገው ጥረት እና ባለው ፍላጎት ሲታገዝ እንደሆነ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አስረድተዋል። አቡነ ቤርናዲቶ በማከልም እውነተኛ ውይይት በፍትህ ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነትን እንደሚጠይቅ አስረድተው እውነተኛ ወንድማማችነትም በተለያዩ እምነቶች መካከል ግልጽ ውይይት እንዲኖር በማድረግ ሁለ ገብ ማሕበራዊ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ያደርጋል ብለዋል።

በተለያዩ እምነቶች መካከል የሚደረግ ውይይት የሚያስገኘው ውጤት፣

በተለያዩ እምነቶች መካከል የሚደረግ ውይይት የሚያስገኘውን መልካም ውጤት የጠቆሙት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ከሁሉም አስቀድሞ በማህበረሰብ ዘንድ ቅድሚያ ሊሰጥባቸው የሚገቡትን ርዕሠ ጉዳዮች መለየት፣ በሁለተኛ ደረጃ በማህበረሰቡ መካከል በድህነት ለሚሰቃዩ እና ለተቸገሩት ሰዎች የሚቀርቡትን የእርዳታ አገልግሎቶችን በጋራ ማካሄድ፣ ለወላጅ አልባ ሕጻናት የሚሰጠውንም የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን በጋራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ አስረድተው በሦስተኛ ደረጃ፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮች በሕብረት ሆነው የእግዚአብሔር ስም የሚከበርበትን እና የእርሱ ፍቅር የሚገለጥበትን ሥራ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበው የእግዚአብሔር ፍቅር በተግባር የሚገለጠው የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጨቆኑትን ነጻ በማውጣት እንደሆነ አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲት አውዛ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ እንደገለጹት፣ የተለያዩ የእምነት ተቋማት በየበኩላቸው ለሰው ልጅ ሕይወት ዋጋን በመስጠት የሚቀርቡት አገልግሎቶች ለእውነተኛ እድገት እና ሰላም ጥሩ መንገድ ይሆናል ብለዋል።  

07 February 2019, 16:01