ፈልግ

90 ዓመታትን ያስቆጠረ የላቴራን ውል ስምምነት በአቶ ፍራንችስኮ ፓቼሊ ጥረት መሆኑን ሰነዶች አረጋገጡ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የላቴራን ውል በመባል ይታወቃል፣ በሁለት ወገኖች መካከል መደማመጥ እና መግባባት የታዩባቸው ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ ወደ ስምምነት በመድረስ ሁለቱ ወገኖች ታሪካዊ የተባለለትን የስምምነት ውል ተፈራርመዋል። ውሉ ከተፈረመ እነሆ ዘጠና ዓመታት ተቆጥረዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰው ስምምነት በምን ላይ ነው? የውሉን ስምምነት የተፈራረሙ ወገኖች እነ ማን ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም።

ያለፈው ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ እና ሉምሳ ተብሎ በሚጠራ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ ጉባኤ ተካህዶ ማለፉ ይታወሳል።  ጉባኤው የተዘጋጀው ከ90 ዓመታት በፊት ማለትም በየካቲት 4 ቀን 1921 ዓ. ም. የተፈረመውን የላቴራን ውል ስምምነት ምክንያት እንደነበር ከቫቲካን የዜና አገልግሎት የደረሰን ዘገባ አስታውቋል።  የቫቲካን መንግሥት እና በቫቲካን ከተማ ከፍተኛ የሕገ ቀኖና ትምህርት ቤት በጋራ ሆነው ያዘጋጁትን ስብስባ፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆንት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የተካፈሉ ሲሆን ከእርሳቸው በተጨማሪ፣ በቫቲካን ከፍተኛ የሕገ ቀኖና ትምህርት ቤት ዋና ዳይሬክተር እና የቫቲካን መንግሥት ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጁሰፔ ዳላ ቶሬ እንደገለጹት በኢጣሊያ መንግሥት እና በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ መካከል ሲካሄድ የቆየውን የጋራ ውይይት በመካከላቸው የነበረውን አለመግባባት ለማስወገድ በየካቲት 4 ቀን 1921 ዓ. ም. የተፈረመው የላቴራን ስምምነት አለመግባባቶችን በማስወገድ ዘላቂ መፍትሄ አስገኝቷል ብለዋል።

በጊዜው በኢጣሊያ መንግሥት እና በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ መካከል የተካሄዱትን ውይይቶች የቫቲካንን መንግሥት በመወከል የተከታተሉት አቶ ፍራንችስኮ ፓቸሊ የተባሉ፣ ምሁር፣ የሕግ አዋቂ፣ የዩኒቨርሲቲ መምሕር፣ ታዋቂ አደራዳሪ እና በቀድሞ ስማቸው ኤውጀኒዮ ፓቸሊ በመባል ለሚታወቁት በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለተባሉ የፒዮስ 12ኛ ታላቅ ወንድማቸው ነበሩ።

በቫቲካን ከፍተኛ የሕገ ቀኖና ትምህርት ቤት ዋና ዳይሬክተር እና የቫቲካን መንግሥት ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጁሰፔ ዳላ ቶሬ እንደገለጹት አቶ ፍራንችስኮ ፓቸሊ በኢጣሊያ መንግሥትን እና በቫቲካን መንግሥት መካከል በተካሄደው ውይይት ላይ በአደራዳሪነት የተጨወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ስምምነት እንዲደርሱ አድርገዋል ብለዋል። የቫቲካን መንግሥት ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጁሰፔ ዳላ ቶሬ በማከልም አቶ ፍራንችስኮ ፓቸሊ ተባባሪያቸው እና አይሁዳዊ የሕግ ባለሙያ ከሆኑት፣ በኢጣሊያ የፍሎረንስ ከተማ ተወላጅ ከሆኑት ፌደሪኮ ካሜዎ ጋር በመሆን አዲስ ለሚመሰረት መንግሥት የሚሆን የመጀመሪያ የህግ ንድፍ በግንቦት 30 ቀን 1921 ዓ. ም. ላይ አዘጋጅተው በቅድስት መንበር ኦፊሴላዊ ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የጤና መታወክ ቢያጋጥማቸውም፣

የአቶ ፍራንሲስኮ ፓቸሊ ወንድም ልጅ ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ጆርጂያ ካሮሌይ ፓቸሊ የቫቲካን የዜና አገልግሎት ሠራተኞችን ወደ መኖሪያቸው ተቀብለው ባስተናገዱበት ጊዜ እንደገለጹት አቶ ፍራንችስኮ የጤና መታወክ ቢኖርባቸውም በቫቲካን መንግሥት ዙሪያ ለሚነሱት ጉዳዮች በሙሉ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማቅረብ የቅርብ ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር በቤታቸው ውስጥ በክብር የተቀመጡ ሰነዶች ይመሰክራሉ ብለዋል። ወይዘሮ ጆርጂያ በማከልም አቶ ፍራንችስኮ ፓቸሊ በየጊዜው ከተለያዩ የሙሶሊኒ የመንግሥት ተወካዮች ጋር የሚያደርጓቸው ውይይቶች እና የሚደርሱባቸው ስምምነቶች የእርቅ ማስታወሻ በተባለ ሰነዳቸው ውስጥ ተጽፈው እንደሚገኙ አስረድተው የእርቅ ማስታወሻቸውም በ1951 ዓ. ም. ለሕትመት የበቃ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም ሙሉ አመኔታ ያደረጉበት እንደሆነ ገልጸዋል።

የፈቃድ ማግኛ መታወቂያ ወረቀት ተሰጣቸው፣

በመሆኑም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ፣ አቶ ፍራንችስኮ ፓቸሊ በማንኛውም ጊዜ ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በአካል በመምጣት ማግኘት ወይም ማነጋገር እንደሚችሉ የሚያስችል እንዲሁም እንደ ሌሎች የቫቲካን መንግሥት ሠራተኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉበትን የፈቃድ ካርድ አዘጋጅተው መስጠታቸውንም ወይዘሮ ጆርጂያ ፓቸሊ ገልጸዋል። 

ቤተሰባዊ ጥረት የታከለበት ነው፣

አቶ ፍራንችስኮ ፓቸሊ፣ ታናሽ ወንድማቸው ከሆኑት ከኤውጀኒዮ ፓቸሊ ጋር ቀጥተኛና ግንኙነት እንደነበራቸው ሲታወቅ፣ ኤውጀኒዮ ፓቸሊ በወጣትነት ዕድሜአቸው ለጵጵስና ማዕረግ ከበቁ በኋላ በጀርመን አገር የቅድስት መንበር እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል። ቀጥለውም የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመሆን የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልጋይ በመሆን አገልግለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ የሚል መጠሪያ ስም የተሰጣቸው ኤውጀኒዮ ፓቸሊ፣ በቫቲካን መንግሥት እና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል በነበሩት ድርድሮች መካከል ለሚፈጠሩት እንቅፋቶች ስጋት እና ፍርሃት ቢያድርባቸውም ታላቅ ወንድማቸው የሆኑት አቶ ፍራንችስኮ ፓቸሊ፣ በተሰጣቸው አደራ እና እምነት ወደ ሰላማዊ ውል ላይ ያደረሱት ስምምነት ዛሬ የላቴራን ውል ስምምነት በመባል ይጠራል።       

12 February 2019, 17:09