ፈልግ

የስብሰባው ማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ ስነስርዓት የስብሰባው ማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ ስነስርዓት 

ቤተክርስቲያን በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ወደ ኋላ የማትል መሆኗ ተገለጸ።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርክ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉ የስብሰባው አባላት እንደገለጹት የምናሳየው ለውጥ በቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት ተልዕኮ አዲስ ምዕራፍን የምንጀምርበት እና ታላቅ የጸጋ በረከት ያለበት ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ ከየካቲት 14 ቀን እስከ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ሲካሄድ የቆየው ስብሰባ ማጠቃለያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነስርዓት ላይ ስብከተ ወንጌል ያቀረቡት፣ በአውስትራሊያ የብሪስቤን ከተማ ሊቀ ጳጳሳት እና የአውስትራሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ማርክ ኮሌሪጅ፣ ቤተ ክርስቲያን በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ወደ ኋላ የማትል መሆኗን ገልጸው ቤተክርስቲያን ለሁሉም ሰው አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ለመሆን ቃል መግባቷን አስታውቀዋል። .

ትናንት እሁድ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ በሚገኘው ሬጂና የጸሎት ቤት ውስጥ ለስብሰባው ተካፋዮች የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሆናቸው ታውቋል። በአውስትራሊያ የብሪስቤን ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ማርክ ኮሌሪጅ ያቀረቡት ስብከተ ወንጌል፣ ቤተክርስቲያን በታዳጊ ሕጻናትን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ያደረገችው ጥረት   ደካማ በመሆኑ ባሳየችውን ድክመት እና ውድቀት እጅግ መጸጸቷን የሚገልጽ፣ ከእግዚአብሔር ምሕረትን በመለመን ወንጌልን የማብሰር አገልግሎቷን በአዲስ መንፈስ የምትቀጥል መሆኗን ገልጸዋል።

መንፈሳዊ ስልጣን እና አገልግሎት መለያየይ የለባቸውም፣

በቤተክርስቲያን ውስጥ በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ጠንካራ አቋሞችን ለመውሰድ እና መንገዶችን ለማግኘት የተደረገውን የአራት ቀን ስብሰባን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ማርክ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማገልገል የሚያግዛት የመንፈስ ቅዱስ ሃይል እንደተሰጣት፣ ይህን ሃይል በመቀበል ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ማዋል እንደሚያስፈልግ አሳስበው ከዚህ በተለየ ለሌላ አገልግሎት የሚውል ከሆነ ወደ ውድቀት እና ወደ ጥፋት ሊያመራ እንደሚችል አስረድተዋል። 

ቤተክርስቲያንን ለማሳደግ የተሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ሃይል እና ስልጣን ሰዎች በስሕተት ለጥፋት እንደተጠቀሙት፣ ራስን ለመከላከል አቅም የሚያንሳቸውን ለመበደል እና ለመጉዳት መጠቀማቸውን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ማርክ ተናገረው ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ሰማያዊውን ስልጣን ወደ ጎን አድርገው ምድራዊውን ስልጣን ተጠቅመዋል ብለዋል።

የእውነተኛ ለውጥ ጥሪ፣

በእውነት አስተማማኝ እና የምዕመናኖችዋን ደህንነቷን የምታስጠብቅ ቤተክስቲያንን ማየት እንፈልጋለን ያሉት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ማርክ ይሁን እንጂ ከሰማያዊው የሃይል እና የስልጣን ጸጋ በረከት ይልቅ ምድራዊውን ስልጣን በማስቀደም ለቤተክርስቲያናችን እና ለራሳችን ያለንን ክብር ቀንሰናል ብለዋል። ሰማያዊው ሰው እንዲወለድ ምድራዊው ሰው መሞት ይኖርበታል ያሉት ብጹዕ አቡነ ማርክ፣ አሮጌው አዳም ለአዲሱ አዳም ስፍራን መስጠት አለበት ብለው ይህም የሚሆነው እውነተኛ ለውጥን የምናደርግ ከሆነ ነው ብለዋል። አለበለዚያ የመንፈሳዊ አገልግሎት ስልጣናችን ምድራዊ አስተዳደር ሆኖ ይቀራል ብለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” ባሉት ሐዋርያዊ ሰነዳቸው ምድራዊ አስተዳደር ወይም ስልጣን ቤተክርስቲያን የደረሰባትን ቀውስ በሚገባ ተመልክቶ የመገንዘብ ብቃት አይኖረውም ማለታቸውን አስታውሰዋል። የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ሕመም ለመረዳት የሚያስችል እውነተኛ ለውጥን ማሳየት እንደሚያስፈልግ የአውስትራሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ማርክ ኮሌሪጅ አሳስበው፣ ሕመማቸው ሕመማችን፣ የጥቃቱ ሰለባዎች ጠላቶቻችን ሳይሆኑ ወገኖቻችን ናቸው ብለዋል።

አዲስ የተልዕኮ ጊዜ እንዲሆን ያስፈልጋል፣

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርክ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉ የስብሰባው አባላት እንደገለጹት የምናሳየው ለውጥ በቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት ተልዕኮ አዲስ ምዕራፍን የምንጀምርበት እና ታላቅ የጸጋ በረከት ያለበት ነው ብለዋል። በማከልም ያለፉት አራቱ የስብሰባ ቀናት የጥቃቱ ሰለባዎችን ሕመም እና የኢየሱስ ክርስቶስን የስቃይ ጩሄት ያዳመጥንበት ነው ብለዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ የቆሰለ ልብ ተስፋ መወለዱን መዘንጋት የለብንም ብለው ይህም ተስፋ በዙሪያችን የተሰበሰቡት የመላው ዓለም ምዕመናን ጸሎት እንደሆነ ገልጸው ቤተክርስቲያንን የትንሳኤው ብርሃን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመራታል ብለዋል። አዲስ የወንጌል ተልዕኮ አድማሳችንን በማስፋት በቃል ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ እና ተግባራዊ የሚሆኑ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ፣ የጥቃቱ ሰለባዎች ፍትህን አግኝተው የሚፈወሱበትን፣ ሌላ በደል እንዳይደገምባቸው የሚያደርግ፣ በደሉን የፈጸሙት ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ፣ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል የተጠሩትም በቂ ቅድመ ዝግጅት እንዲሰጣቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለው ቤተክርስቲያን ለሁሉም ሰው አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ሥፍራ እንድትሆን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመግታት ወደ ኋላ ማለት የለብንም፣

በቤተክርስቲያን ውስጥ የታዳጊ ሕጻናት እና የወጣቶች ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ብጹዓን ጳጳሳት እና ካህናት ከመላው ምእመናን ጋር በመተባበር ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶችን፣ ለምን እንደተፈጸሙ የሚያስረዱ ማብራሪያዎችን በማቅረብ፣ ወደ ፊትም እንዳይደገሙ ለማድረግ ጊዜን በመውሰድ በጋራ ከመሥራት ወደ ኋላ እንደማይባል ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
25 February 2019, 15:52