ፈልግ

ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፣ ለህሙማን አዘኔታ እና ርኅራኄ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2011 ዓ. ም. ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን፣ ለሕሙማን አዘኔታ እና ርህራሄን ማሳየት እንደሚስፈልግ አሳስበዋል። ዛሬ ለ27ኛ ጊዜ ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ ከቫቲካን የቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የልኡካን ቡድንን ይዘው ወደ ሕንድ ካልካታ የተጓዙት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራስንችስኮስ የተላከ መልዕክት ወደ ስፍራው ማድረሳቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮ ታስቦ ለዋለው ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን መሪ ቃል እንዲሆን ብለው የመረጡትን “በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” ከ(ማቴ. 10:8) የተወሰደውን ጥቅስ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፣ ክርስቲያናዊ ማሕበራዊ ሕይወትን በማገናዘብ ከሚከናወኑ ማሕበራዊ አገልግሎቶች መካከል በጤናው ዘርፍ የሚሰጥ የሕክማና አገልግሎት፣ የሕዝቦች ብዝሃነት በሚታይበት በዛሬው ዓለማችን የተለያዩ ባሕሎችንም ያገናዘበ ሐዋርያዊ የጤና አገልግሎት መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ሐዋርያዊ አገልግሎታችንን ለሁሉ ለማዳረስ ብለን የምናደርገው ጥረት የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ወገን ነው ያሉት ብጹዕነታቸው ይህም በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳይሆን የወንድማማችነትን ፍቅር በማሳደግ እርስ በእርስ ለመተጋገዝ እና በነጻ የተቀበልነውን የፍቅርን ጸጋ ከሌሎች ጋር ለመካፈል ያግዛል ብለዋል።

   

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ልኡካን ዛሬ በካልካታ ባሳለፈው ቆይታ፣ ነገረ መለኮታዊ መንገድን በተከተለ የጤና አጠባበቅ ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ የጤና ባለሞያዎች በድህነት ሕይወት ውስጥ ለሚገኙት ሕሙማን የሚያቀርቡትን ሐዋርያዊ አገልግሎት አስመልክቶ የተዘጋጀውን አዲስ መመሪያ ከስብሰባው ተካፋዮች ጋር በዝርዝር መመልከቱ ታውቋል። የቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የልኡካን ቡድን ትናንት እሁድ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ. ም. በካላካታ ከሚገኙት የእርዳታ መስጫ ማዕከላት መካከል ወደ አንዱ በመሄድ የዕርዳታ አገልግሎትን በማግኘት ላይ የሚገኙትን ሕሙማንን፣ ተንከባካቢ ሌላቸው እና ከማሕበረሰቡ የተገለሉትን፣ የስነ አዕምሮ ችግር ያለባቸው ሴት ተረጂዎችን መጎብኘታቸው ታውቋል።

ዛሬ ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2011 ዓ. ም. ታስቦ የዋለውን 27ኛ ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ በብጹዕ ካርዲናል ፓትሪክ ደ ሮዛሪዮ የተመራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የቀረበ ሲሆን በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ማጠቃለያ ላይ ለሕሙማኑ የምስጢረ ቀንዲል አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት መከናወኑ ታውቋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት ሁሉ፣ ለሕሙማን ስለሚደረግ እንክብካቤ እና የሕክምና አገልግሎት ትርጉም ሲያብራሩ፣ ለሕሙማን እንክብካቤን በምናደርግበት ወቅት አስቀድሞ ሕመማቸው እና ስቃያቸው ሊሰማን ይገባል ብለው ይህ ሳይሆን የሚደረግ የሕሙማን እንክብካቤ እውነተኛ እንክብካቤ ሊሆን አይችልም ብለዋል። ሕመማቸው እና የደረሰባቸው መከራ ሊሰማን ይገባል በምንልበት ጊዜ በያዛቸው በሽታ መጠቃት አለብን ማለት ሳይሆን የሚገኙበትን ሁኔታ በመረዳት፣ ከልብ በመጨነቅ፣ ሰብዓዊ ርህራሔን በማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። የእግዚአብሔር ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ በመራራት፣ ለሐጢአታቸው ይቅርታን ለማስገኘት ወደ ዓለም እናደመጣ ሁሉ በሕመም ውስጥ የሚገኝ ሰው በምናገኝበት ጊዜ የርህራሔን ልብ በማሳየት እንክብካቤን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው ይህን በማድረጋችን የእግዚአብሔር ቸርነት እና ፈውስ እንዳልተለያቸው በተግባር መመስከር እንችላለን ብለዋል። ይህም በሕመም ላይ ለሚገኙት ሰዎች ማበርከት የምንችለው ትልቁ ስጦታ እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን በታመሙት ሰዎች በኩል ማየት እንችላለን፣

ለታመሙት ሰዎች የሚደረግ ስነ መለኮታዊ እንክብካቤ እና ይህን እንክብካቤ ለማድረግ የሚያድረገን ጥሪ የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሃሳብ ያስታወሱት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን ለስብሰባው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት በታመሙት ሰዎች በኩል ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት መቻል እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እና የቤተክርስቲያንም ትልቅ ሃብት እንደሆነ ስረድተው፣ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ስቃይ በመቀበል ያሳየውን ምሳሌ እንድንከተል፣ የርሕራሄ ልብ እንዲኖረን ቤተክርስቲያን ትጠራናለች ብለው ለዚህም ጥሪ በቂ መልስ የሰጠው እና የሕሙማን ተንከባካቢ የነበረው ቅዱስ ካሚሎ ደ ለሊስ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሁላችንም ወሰን የሌለውን የእግዚአብሔር ፍቅር ተቀብለናል ያሉት ብጹዕ ካዲናል ፒተር ታርክሰን ሁላችንም በተሰጠን የፍቅር ስጦታ መጠን ሌሎችን ማገዝ ይኖርብናል ብለዋል። ሕሙማንን ለመንከባከብ ወይም ለማከም በምትጠቀሙት እጆቻችሁ ላይ ፍቅርን ጨምሩበት ያለውን የቅዱስ ካሚሎ መልዕክት ለሕሙማን የሚደረገውን አገልግሎት ፍሬያማ ያደርገዋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ይህ የእኛ ተስፋ እና ፍላጎት ሊሆን ይገባል ብለዋል። በመጨረሻም የበሽተኞች ፈውስ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሕሙማን ርህራሔን የምናደርግበት ልብ በመስጠት ታግዘን ብለዋል።      

11 February 2019, 15:32