በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን መከላከል የጋራ ሃላፊነት መሆኑ ተገለጸ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ. ም. በይፋ የከፈቱት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶችን ለማጠናከር ብሎ በተቀመጠው ስብሰባ፣ በሕጻናት ስነ ልቦናዊ ቁስልን የሚያስከትሉ ማንኛውም ዓይነት ሕገ ወጥ በደሎችን በሕብረት መከላከል እንደሚያስፈልግ፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ አሳሰቡ። ትናንት የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ. ም. ሁለተኛ ቀኑ ባስቆጠረው እና ከመላው ዓለም የተገኙት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሊቃነ መናብርት እና ተወካዮቻቸው፣ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚካፈሉት ስብሰባ ላይ ሃሳባቸውን በስፋት የገለጹት የካቶሊካዊ ምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ እንደገለጹት በታዳጊ ሕጻናት ላይ ስለሚደርሱ በደሎች ስንናገር በደሉ የደረሰባቸው ሕጻናት እና የታዳጊ ሕጻናት ወላጆችን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ፣ በደል አድርሰዋል ወይም ሕገ ወጥ ተግባርን ፈጸመዋል የተባሉትን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ወይዘሮ ሊንዳ በማከልም የቆሰለውን የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የተመለከተው የምሕረት ጌታ እግዚአብሔር የሰዎችን ቁስል በፍቅሩ ተመርተን እንድንጠግንላቸው ያግዘን ብለዋል።
የደረሰውን በደል ለይተን የማወቅ እና ሃላፊነትን የመውሰድ ግዲታ አለብን፣
ለተፈጸሙ በደሎች በሙሉ ተጠያቂነት ሊሰማን ይገባል ያሉት በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ፣ ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ፣ የበደሉ ክብደት ተሰምቶን የሕሊና ጸጸት ሊኖር እንደሚገባ፣ እውነትን እና ፍትህን የማግኘት ግዴታ፣ የተፈጠረውን ቁስል የመጠገን ግዴታ፣ ተመልሶ እንዳይደገም ማድረግ እና የተጠያቂነት ግዴታ ሊኖር ይገባል ብለዋል።
ሃላፊነትን በጋራ መወጣት ያስፈልጋል፣
የቅድስት ስላሴን ምስጢራዊ አንድነት ያስታወሱት ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ፣ የቤተክርስቲያን ወገን እንደመሆናችን የሰዎችን ስቃይ ለማስታገስ ጥረት ማድረጋ ያስፈልጋል ብለው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት እንደተናገሩት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማቃለል የምናደርገው ጥረት ሌሎች ማሕበራዊ ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚወሰድ የግል ሃላፊነት ሳይሆን፣ የቤተክርስቲያን የአንድነት ምስጢር የሚገለጥበት፣ ብዙዎች ብንሆንም እንደ አንድ አካል በመሆን የጋራ ጥረት የምናደርግበት ነው ብለዋል።
የመንፈሳዊ ማሕበራት እንቅስቃሴዎች ሚና፣
በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ጨምሮ ሌሎች በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ከቤተክርስቲያን አባቶች ከሆኑት ብጹዓን ጳጳሳት እና ካህናት በተጨማሪ የተለያዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማሕበራት አባላት ወይም ምእመናን ሃላፊነት እንደሆነ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ አስረድተዋል።