ፈልግ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ  

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መስረታዊ ጽንስ-ሐሳብ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በንቃት ትሳተፋለች!

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መስረታዊ ጽንስ-ሐሳብ፣ አጀማመሩ እና ታሪካዊ ሂደቱ
መግቢያ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በተሰኘው በእዚህ ሳምንታዊ ዝግጅታችን ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መስረት የጣሉ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎችን፣ ማኅበራውዊ አስተምህሮዎች እንዲሁም ይህንን የቤተ ክርስቲያኑዋን ማኅበራዊ አስተምህሮ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የጻፉዋቸውን፣ ሐዋሪያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳኖች በመዳሰስ ነባራዊ የሆነውን የዓለማችን፣ የቤተ ክርስቲያናችንን እና የሀገራችንን ሁኔታ በዳሰሰ እና ከግምት ባስገባ መልኩ ወደ እናንተ እናቀርባለን።
ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ከተመሰረተችበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬው ቀን ድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በተለይም ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች (ለድሆች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለሕጻናት፣ ለበሽተኞች፣ በማሕጸን ውስጥ ለሚገኙ ጽንሶች. . . ወዘተ) ድምጽ በመሆን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ በሕዝብ ላይ የሚደረሰውን ማኅበራዊ ጫና እና በደል በመቃወም ለዓለም ድምጽዋን ስታሰማ መቆየቷ ይታወቃል።
ቤተ ክርስቲያን ድምጽ አልባ ለሆኑ ሰዎች ድምጽ ትሆናለች!
የዓለማችን ችግሮች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም እድገት እና ብልጽግና በታሪክ ውስጥ በሚፈጠሩ፣ የተለያዩ አጋጣሚዎች የተነሳ፣ እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎችም እንደ ወቅቱ ሁኔታ የሚለያዩ ቢሆኑም በእነዚህ ማኅበራዊ እድገቶች፣ ቀውሶች እና ተግዳሮቶች ምክንያት፣ በተለይም በድሃው የማኅበረሰብ ክፍል እና ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት ላልቻሉ የተጨቆኑ ሕዝቦች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት ጭቆና ጠፍቶ በአንጻሩ ፍትህ እና የጋራ ተጠቃሚነት በዓለም ዙሪያ እንዲሰፍን የተለያዩ ሰላማዊ የሆኑ መንገዶች በመጠቀም የራሷን ከፍተኛ አስተዋጾ ማበርከቷ እና አሁንም ቢሆን ይህንን መልካም ተግባሩዋን አጠናክራ መቀጠሏ ይታወቃል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ጠቅላላ ይዘቱን እና ፅንሰ-ሐሳቡ
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ የማኅበርሰቡን መብት እና ግዴታን ከግምት ባስገባ መልኩ የሚከተሉትን ሁለት መሰረታዊ የሆኑ መርሆችን በማንገብ ይህንን አስተምህሮዋን ሕጋዊ መልክ ታላብሰዋለች፣ ሕጋዊነቱንም ታረጋግጣለች። ምን አላባት ቤተ ክርስቲያን ተግባሩዋ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እና አግልግሎት መስክ ብቻ ሊሆን ይገባል በማለት ልንሞግት እንችል ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን መስብከ፣ ክርስቶስን ለዓለም ማስተዋወቅ እነዚህን እና እነዚህን በመሳሰሉ መንፈሳዊ እና ስነ-ምግባራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮር ነው የሚገባት እንጂ፣ ከእዚህ ወጭ በመሄድ ስለማኅበራዊ ጉዳይ ማወራት ለምን አስፈልጋት?፣ ምንስ አገባት? ብለን ልንጥይቅ እንችል ይሆናል። ይህም ተግቢና ሊነሳ የሚገባው ጠቃሚ የሆነ ጣይቄ መሆኑን እንረዳለን።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህንን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን “በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ገብቼ መሳተፌ ተገቢ ነው” በማለት ለእዚህ ጥያቄ የሚከተለውን ማብራሪያ እና መስራጃ ታቀርባለች።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በንቃት ትሳተፋለች!
በእዚህም መሰረት በቅድሚያ ማንኛውም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የሚጀምረው ግብረገባዊ ሥነ-ስርዓቶችን በቀጥታ ከተፈጥሮ በላይ ካለው መለኮታዊ የሆነ ኃይል ካለው ስነ-ምግባር ጋር በማቆራኘት ይጀምራል። ይህም ማለት ማንኛውም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው አዎንታዊ የሆነ ስነ-ምግባር በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ከፈጣሪ ጋር ይገናኛል ማለት ነው።
በዚህም የተነሳ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የሆን እሴቶች በቀጥታ ከስነ-ምግባር ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው የተነሳ እነዚህም የስነ-ምግባርና የሃይማኖት እሴቶችን አቅፈው የሚይዙ ጉዳዮች በመሆናቸው የተነሳ ጭምር ቤተ ክርስቲያን የማኅበረሰቡ የሞራል፣ የስነ-ምግባር እና የሐይማኖታዊ እሴቶች እምብርት በመሆኗም ጭምር ቤተ ክርስቲያን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የመግባት መብት እንዲኖራት ያደርጋል ማለት ነው። የዚህን ዓይነት ጣልቃ ግብነት የምታደርገው ሙያዊ የሆነ ትንታኔዎችን በመስጠት የፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ በማስገደድ ሳይሆን ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ እና ስነ-ምግባራዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ እነዚህ ስነ-ምግባራዊ እሴቶችን በታሪክ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት በማሰብ የምታደርገው ጣልቃ ግብነት ነው።
ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ለምን ትገባለች?
ይህንን ቀደም ሲል የተገጸውን ጭብት ሐሳብ በሚገባ ማብራራት አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ይመስለናል። ቤተ “ክርስቲያን ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ለምን ትገባለች?” ቢባል መልሱ አንድ እና አንድ ነው። ማኅበረሰብ ስንል የሰዎች ስብስብ ማለት እንደ ሆነ ይታወቃል። የሰው ልጆች ተሰብስበው በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ ማኅበራዊ ግጭቶች ኢፍታዊ ተግባሮች፣ የመብት ጥሰት . . . ወዘተ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ክስተቶች በማኅበረሰብ ውስጥ ሊፈጠሩ ይችሉ ይሆናል፣ እየተፈጠሩም ይገኛሉ።
ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ነፍስ እንዳይጠፋ ትሠራለች
በማንኛውም ምክንያት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ተገቢ ያልሆኑ ግጭቶች የማኅበረሰቡን ሰላም በማወክ፣ በተለይም ደግሞ ሕጻናት፣ ሴቶችን እና አዛውንቶችን አደጋ ላይ በመጣል ማኅበራዊ ኑሮን አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ የሕዝቡን ሰላም በማወክ የእግዚኣብሔር ስጦታ የሆነውን የሰው ልጆች ነፍስ እንደ ዋዛ እንዲጠፋ ያደርጋል። በእዚህም ምክንያት የተነሳ ቤተ ክርስቲያን የእግዚኣብሔር ስጦታ የሆነ የሰው ልጆች ክቡር የሆነ ነፍስ እንደ ዋዛ እናዳይቀጠፍ፣ የግጭቶች ሁሉ መንስሄ የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮችን ነቅሳ በማውጣት ሰላማዊ በሆነ መልኩ ውይይት እንዲደርግ፣ ለችግሮች ሁሉ ሰላማዊ የሆነ ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመወያየት ባሕልን ባማከለ መልኩ ችግሮች እና አለማግባባቶች በሰላም ይፈቱ ዘንድ የበኩሏን ማኅበራዊ አስተዋጾ ማድርግ ሰለሚኖርባት በእዚህ አግባብ በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በትኩረት ትሳተፋለች።
በተመሳሳይ መልኩ ቤተ ክርስቲያን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ ሙያዊ ትንታኔ የመስጠት ሕጋዊ የሆነ መብት ባይኖራትም፣ ነገር ግን በተቃራኒው በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት የሚጎዳው ያው የሰው ልጅ መሆኑን አጥብቃ ስለምትረዳ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተሳትፎ ታደርጋለች። ምክንያቱም ፍታዊ የሐብት ክፍፍል በአንድ አገር ውስጥ የሌለ ከሆነ፣ መሰረታዊ የሚባሉ ተቋማት የማይሟሉ ከሆነ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ያወ የማኅበረሰብ ክፍል ነው፣ በተለይም ደግሞ ድሃ እና አቅመደካማ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል የእዚህ ጥቃት ሰለባ ይሆናል። በተመሳሳይ መልኩም በአንድ አገር የፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ በሚከሰተው ሙስና፣ ሕዝብን ያላማከለ ውሳኔ፣ ስነ-ምግባርን እና የተፈጥሮ ሂደትን ባላመከለ መልኩ የሰው ልጆችን ደህንነት እና ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ውሳኔዎች በሚተላለፉበት ወቅት ሰላማዊ የሆነ ተቃውሟን ቤተ ክርስቲያን የማስተጋባት ስነ-ምግብራዊ ግዴታ አለባት።
ምክንያቱም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች እና ኢፍታዊ ድርጊቶች ምክንያት የሚጎዳው ያው የሰው ልጅ በመሆኑ የተነሳ ሲሆን በተለይም አቅመ ደካማ የሆነ እና ድሃ በሆነው የማኅበረሰብ ክፍሎች በመሆናቸው የተነሳ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ስንመለከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ማኅበራዊ ፍትህ እንዲኖር፣ በተለይም ዝቅተኛ የተባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መብት ለማስከበር እና ብሎም ከፍ ሊያደርጋቸው አስቦ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑ እና ኢፍታው ተግባራትን ማውገዙ ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያንም የክርስቶስ ተከታይ በመሆኗ የተነሳ የክርስቶስን መንፈሳዊ፣ ስነ-ምግባራዊ እና ማኅበራዊ ተልዕኮን አጠናክራ የማስቀጠል መንፈሳዊ ግዴታ ስለተሰጣት በእዚሁ አግባብ ተግባሩዋን ማከናወን ይገባታል ማለት ነው።
የክርስቲያን ራእይ ታሪካዊ ገጽታ
በሁለተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮዎችን እንድትሰጠ መብት የሚሰጣት ደግሞ የክርስቲያን ራእይ ታሪካዊ ገጽታ ስላለው ነው። ቤተ ክርስቲያን ከማኅበርሰቡ እና ከታሪክ ጋር ከፍተኛ እና እውነተኛ ኅብረት አላት። እናም የሰው ልጅን ለማዳን እና ማህበረሰቡን ለማደስ ከሚሳተፉ አካላት ጋር በመሆን የሰው ልጆች ደስታ ደስታዬ፣ የሰው ልጆች መከራ እና ለቅሶ ደግሞ ለቅሶዬ ነው፣ በማለት ለሰው ልጆች ችግር መፍትሄ ለመስጠት የበኩሏን የማድረግ ግዴታ አለባት። በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መአከሉን ያደርገው የሰው ልጆች ላይ ነው።
ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሰረተችው የመላእክት ጠባቂ ለመሆን ሳይሆን የሰው ልጆችን አቅፋ፣ ደግፋ፣ በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ በማድረግ፣ በሰላም እና በደስታ እግዚኣብሔር የሰጣቸውን በረከት እየታቋደሱ እንዲኖሩ ለማድረግ፣ የሰው ልጆችን ለእግዚኣብሔር መንግሥት የማብቃት ተልዕኮ እንደ ተሰጣት ይታወቃል። በእዚህም መስረት ነው እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የሰው ልጆችን ደስታ እና ሰላም የሚንጥቁትን ተግባራት ለማስወገድ በማሰብ ነው እንግዲህ እነዚህን ማኅበራዊ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የምትቃወመው፣ የድኾችን እና ደካማ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍል ድምጽ ለማስተጋባት በማህኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የምትገባው እና ማኅበራዊ አስተምህሮችን የምታደርገውም በእዚሁ ምክንያት ነው።
አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
 

15 January 2019, 12:19