ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ፣  

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃሳብ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድ ተወደሰ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስስኮስ ለአምባሳደሮች ባደረጉት ንግግራቸው መንግሥታት በመካከላቸው ውጤታማ ዲፕሎማሲን ለመፍጠር ከፈለጉ በመካከላቸው ቅንነትና መተማመን እንዲኖር፣ ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችል ፍትሃዊ እና ሐቀኛ ውይይት እንዲያደርጉ፣ አለመግባባት ከተፈጠረ መፍትሄን ለማግኘት ስህተትን አምኖ መቀበል እንደሚያስፈልግ ገልጸው ይህ ሳይሆን ሲቀር ሃያላን መንግሥታት አቅመ ደካማ በሆኑት መንግሥታት ላይ የበላይነትን በመጎናጸፍ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ወደ አመጽ ሊወስዱት ይችላሉ ማለታቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢና እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን ለመቋቋም አምባ ገነናዊ መንግስታዊነትን መዋጋት ያስፈልጋል ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍርንችስኮስ መልዕክት በመጥቀስ ለመንግሥታቱ ድርጅት ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ይህን የተናገሩት ያለፈው ሰኞ ታህሳስ 29 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏችው የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች ባስተላለፉት መልዕክት እንደነበር ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስስኮስ ለአምባሳደሮቹ ባደረጉት ንግግራቸው መንግሥታት በመካከላቸው ውጤታማ ዲፕሎማሲን ለመፍጠር  ከፈለጉ መልካሙ መንገድ ቅንነትና መተማመን እንዲኖር፣ ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችል ፍትሃዊና ሐቀኛ ውይይት እንዲኖር ማድረግ፣ አለመግባባት ከተፈጠረ መፍትሄን ለማግኘት ስህተትን አምኖ መቀበል እንደሚያስፈልግ ገልጸው ይህ ሳይሆን ሲቀር ሃያላን መንግሥታት አቅመ ደካማ በሆኑት መንግሥታት ላይ የበላይነትን በመጎናጸፍ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ወደ አመጽ ሊወስዱት ይችላሉ ማለታቸው ይታወሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ይህን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃሳብ በሙላት እንደሚጋራ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ተናግረዋል።

ብሔረተኝነት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንቅፋት ነው፣

በአንዳንድ አገሮች ዘንድ እየታየ የመጣው አምባ ገነናዊ መንግሥታዊነት ለተባበሩት መንግሥታት ሕልውና ጥሩ አይደለም ያሉት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ የተበባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮችም በመካከላቸው የሚታዩትን ችግሮች ለማስወገድ በርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ሃስብ እንደሚስማሙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. የመንግሥታቱ ጉባኤ የድርጅቱን ሕብረት ደረሰበትን ደርጃ ለማወቅ ከአገራቱ መሪዎች ጋር ባደረገው የአሰሳ ጥናት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉዞውን የሚያደናቅፉ መጠነ ሰፊ ችግሮች ቢኖሩበትም፣ አባል አገራት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማፈላለግ የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ፣ በተጨማሪም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል አገሮች ሰላምን ለማስጠበቅ ያስቀመጡትን ሕጎች መመልከት በቂ ነው በማለት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ አስረድተዋል።

የልማት ዕርዳታ ፖሊሲን በድጋሚ ማጤን፣

በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት ስር ሆነው የራሳቸውን ጥቅምና የስልጣን የበላይነት ለመጎናጸፍ የሚፈልጉ አገራት፣ የራሳቸው ሃሳብ ብቻ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ብለው የሚያደርጉት ጥረት አዲሱ የቅኝ ግዛት ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለዲፕሎማቶቹ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ለአገሮች የሚደረጉ ዓለም አቀፍ የልማት ዕርዳታዎች ያደጉት አገሮች በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ላይ የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ለዚህም ዋናው ማሳያ የሚሆነው ለጋሽ የአውሮጳ ሃብታም አገሮችና ሰሜን አሜርካ በማደግ ላይ ላሉት አገሮች የሚሰጧቸውን ዕርዳታ እነርሱ በሚፈልጉት የልማት ዘርፍ ላይ እንዲያውሉ ጫና መፍጠራቸውን አስታውሰው፣  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የልማት ዕርዳታ ፖሊሲን በድጋሚ ማጤን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እቅዶችን ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ፣

በማደግ ላይ የሚገኙትን ደሃ አገሮች ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለደሃ አገሮች ትኩረትን እንዲሰጥ አሳስበው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዲፕሎማቱ አካላት ባሰሙት ንግግር ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና ተቋማት ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ሆነው እንዲያገለግሏቸው አደራ ማለታቸውንም አስታውሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምንም እንኳን መጠነ ሰፊ የሆኑ ችግሮች ቢኖርበትም በልማት ዕቅዶቹ ላይ ተሻሽሎን በማድረግ፣ በተለይም ለልማት የሚዉሉ የገንዘብ ድጋፍን በማሳደግ፣ በምልካም የልማት ጎዳና ላይ የሚገኙትን አገሮች በመርዳት፣ በአገሮች መካከልም የሚነሱ ግጭቶችንና ጦርነቶችን ለማስወገድ ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የሶርያን ተፈናቃዮን ለመርዳት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድምጽ ወሳኝ ነው፣

የሶርያን ቀውስ ማርገብና የተፈናቃዮችዋን ችግር ማቃለል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቀዳሚ ተግባር ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ይህ ተግባር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። የሶርያ ጦርነት ከሶርያ አልፎ ሌሎችንም  ዓለም አቀፍ ቀጠናዎችን በግልጽ ለመመልከት ያግዛል ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አውዛ በጦርነቱ የተጠቃችው ሶርያ ብቻ ናት ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቤርንዲቶ ኣውዛ፣

የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ ቅድስት መንበር ግሎባል ኮምፓክት በመባል በሚታወቀው ዓለም አቀፉ ስምምነት ውስጥ እንዲካተት ብላ ያቀረበችው ሃሳብ፣ የስደት ክስተቶች በምንም መልኩ ተስፋ የሚያስቆርጥ ምልክት መታየት እንደሌለበት፣ የስደተኞች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ ሰዎች ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት ሕጋዊ ዝውውር መብት እንዲከበርላቸው፣ ለስደተኞች ሊደረግ ስለሚገባ ከለላ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ የበኩሏን አስተያየት ማቅረቧን ገልጸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስደተኞች አስፈላጊ እገዛ እንዲደረግላቸው በማለት ያቀረቡትን ማሳሰቢያ፣ ስደተኞች የሚሄዱባቸው አገሮች ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

10 January 2019, 16:32