ፈልግ

ወጣቶች በ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት ወጣቶች በ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት 

በወጣቶች ጉዳይ ላይ የሚነጋገር ዓለም አቀፍ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ ተነገረ።

የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ አሌሳንደር፣ በቫቲካን ከተማ የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት የተመለከተው የጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቀጣይነት ያለው እንደሆነ ገልጸው ጽሕፈት ቤታቸውም በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ሲኖዶሱ ያረቀቀውን ሰንድ በመመልከት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመጭው ሰኔ 11 ቀን እስከ ሰኔ 15 ቀን 2011 ድረስ የሚቆይ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን በቫቲካን ከተማ የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የዚህ ዓለም ዓቀፍ የውይይት መድረክ ዋና ዓላማ 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዘንድሮ ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ ወጣቶች፣ እምነት እና ጥሪያቸውን በጥበብና ማስተዋል፣ በሚገባ ተገንዝበው ትክክለኛ ውሳኔን እንዲያደርጉ በሚል ርዕስ ያደረጉትን የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውጤት የእስካሁኑን ሂደትና የወደፊቱን ቀጣይ ጉዞን ለማቀድ እንደሆነ ታውቋል።

ዓለም አቀፍ ጉባኤውን የሚሳተፉ አባላት ተመርጠዋል፣

ከሰኔ 11 እስከ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በሚቆየው ዓለም አቀፍ የወጣቶች መድረክ ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ከመላው የዓለም ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የተወጣጡ ወጣቶች፣ እንዲሁም በእነዚህ ጳጳሳት ጉባኤዎች ስር ከሚገኙት ቁምስናዎችና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የተወጣጡ ወጣቶች እንደሚሆኑ የውይይት መድረኩን ያዘጋጀው፣ በቫቲካን የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ጽሕፈት ቤቱ በተጨማሪ በ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ አጠቃላይ መደበኛ ስብሰባን ከተካፈሉት ወጣቶች መካከልም አንዳንዶቹ በውይይት መድረኩ ላይ በመገኘት ያለፈው ጉባኤን ልምድ ሊያካፍሉ እንደሚችሉ፣ ከእነርሱ በተጨማሪ በወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ሰፊ እውቀት ያላቸው ዓለም ዓቀፍ ምሁራንም እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

በቫቲካን ከተማ የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ አሌሳንደር አዊ ሜሎ እንደገለጹት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጠቅላላ የጳጳሳቱ ሲኖዶስ ያቀረቡትን ሐዋርያዊ መመሪያን፣ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በወጣቶች ጉዳይ ላይ ለመምከር ዝግጅት ካደረገበት ጊዜ አንስቶ እስከ 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ማጠቃለያ ድረስ የተካሄደውን የጉባኤውን ሂደት የሚያጠቃልል ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስም ያወጣው የመጨረሻ ሰነድ ተግባራዊ የሚሆኑባቸው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎችም በጥልቀት በማጤን ተግባራዊ ለማድረግ የየአገሮቻቸውን ወጣቶች የሚያሳትፉበት ይሆናል ብለዋል። አባ አሌሳንደር አዊ ሜሎ እንደገለጹት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤታቸው በወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት አፈጻጸም በቂ እውቀት ያለው በመሆኑ፣ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ወጣቶችን ወደ ውይይት መድረኩ በመጋበዝ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ተወያይቶበት ያቀረበውን የጉባኤ ውጤት ወጣቶች ተቀብለው በተግባር እንዲያውሉ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ፣ የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ አሌሳንደር አዊ ሜሎ እንደገለጹት፣ ጽህፈት ቤታቸው ዘንድሮ በመካከለኛዋ የላቲን አሜርካ አገር በፓናማ ዘንድሮ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ ለ34ኛ ጊዜ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ዙሪያም ብዙ ሥራ ማከናወናቸውን አስረድተዋል። ጽሕፈት ቤታቸው ቅድሚያን በመስጠት እየሠራ የሚገኘው፣ ወጣቶች፣ እምነት እና ጥሪያቸውን በጥበብና ማስተዋል፣ በሚገባ ተገንዝበው ትክክለኛ ውሳኔን እንዲያደርጉ በሚል ርዕስ መሆኑንም ገልጸዋል። በመሆኑም በፓናማ ከሚከበረው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል መልስ፣ ወጣቶች ከዚህ በዓል የቀሰሙትን ልምድ ይዘው፣ በሮም ከመጭው ሰኔ 11 ቀን እስከ ሰኔ 15 ቀን 2011 ድረስ፣ በቫቲካን ከተማ የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው  የውይይት መድረክ ላይ እንዲገኙ መደረጉን አስረድተዋል። አባ አሌሳንደር ጽሕፈት ቤታቸው እስካሁን 10 የውይይት መድረኮችን አዘጋጅቶ እንደነበር ገልጸው አሁን በመዘጋጀት ላይ ያለው የውይይት መድረክ፣ በጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የጉባኤ ውጤትን አንድ ባንድ የሚመለከት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ስር በሚገኙ ቁምስናዎች የተዋቀሩ የወጣት ማሕበራትና እንቅስቃሴዎች ማከናወን ያሉባቸውን ተግባራት የሚመለከት በመሆኑ ልዩ የውይይት መድረክ ይሆናል ብለዋል።

ወጣቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ቤትክርስቲያን ከእግዚአብሔርን የተቀበለችሁን ጸጋ በመመልከት ላይ ትገኛለች ያሉት አባ አሌሳንደር ይህ ወቅት ቤተክርስቲያን ወጣት ልጆቿን ለማዳመጥ የተዘጋጀችበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፣ በፓናማ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው በጸሎት አማካይነት የመንፈስ ቅዱስ ሃይል የሚገለጥበትና የእርሱንም ፈቃድ ለመቀበል ልባቸውን የሚከፍቱበት ወቅት እንደሚሆን አስረድተዋል። በተጨማሪ የፓናማው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል፣ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ከመላው የዓለም ወጣቶች ጋር ባቀረቡት ሰነድ ላይ ለማስተንተን አጋጣሚን የሚያመቻችላቸው እንደሆነ ገልጸዋል። 

ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቀጣይነት ያለው ነው፣

የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት ጳጳሳዊ መምሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ አሌሳንደር፣ በቫቲካን ከተማ የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት የተመለከተው የጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቀጣይነት ያለው እንደሆነ ገልጸው ጽሕፈት ቤታቸውም በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ሲኖዶሱ ያረቀቀውን ሰንድ በመመልከት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስና፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የተመለከቱት፣ ወጣቶችን የሚመለከት የመጨረሻ ሰነድ የእቅዳቸው መጨረሻ ሳይሆን ከዚያም አልፎ ለተግባራዊነቱ በርትተን የምንሰራበት፣ ውጤቱንም የምናይበት መሆን ያስፈልጋል ብለው ውጤቱንም በቀዳሚነት ማየት የሚፈልጉት ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። ስለዚህ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤታቸው ያጸጋጀው ዓለም አቀፍ መድረክ ወደ ፊት በየአገሮቻቸው፣ በየቁምስናቸውና በየመንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ ሃሳባቸውን የምናውቅበት፣ ድምጻቸውንም የምናዳምጥበት አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል። 

11 January 2019, 15:00