ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ 

ቅድስት መንበር የምታደርገው የጋራ ውይይት ለሕዝቦች ጥቅም መሆኑ ተነገረ፣

በሕዝቦች መካከልም ይሁን በመንግሥታት መካከል ውይይቶችን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ ለዲፕሎማሲ መዳበር ውይይት አንዱ መንገድ መሆኑን ገልጸው፣ መስዋዕትነትን ቢያስከፍልም ውይይትን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ በውይይት ማንኛውንም ዓይነት ችግር ለማለፍ የሚያስችል ድልድይ መገነባት እንደሚቻል፣ የመፍትሄ አቅጣጫን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከተማ ለሚገኝ የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንትና የዓለም አቀፍ ሕግ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ቪንቼንሶ ቡዎኖሞ፣ የቅድስት መንበር የውይይትና የዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚያተኩረው ከመንግሥታት ጋር ሳይሆን ከአገራት ጋር መሆኑን ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ የአንድ አገር መንግሥት ቢወድቅ ወይም ቢለዋወጥ፣ ቅድስት መንበር ከዚያ አገር ጋር ወይም ለዚያ አገር ሕዝብ ያላት ትኩረትና ግንኙነት ስለማይቋረጥ ነው ብለዋል። ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ ማብራሪያቸውን በመቀጠል ቅድስት መንበር በማንኛውም መንግሥት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንደማትገባ አስረድተው ነገር ግን የሕዝቦች ሕይወት ችግር ላይ ሲወድቅ መመልከት፣ ሰብዓዊ መብት ሲረገጥ መመልከት እንደማይዋጥላት ገልጸው፣ አቅሟ በፈቀደ ሁሉ አገልግሎቷን የምታበረክተው ለሰዎች ጥቅም መሆኑን አስረድተዋል። ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ በማብራሪያቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት በቅርቡ የተለያዩ  አገራት አምባሳደሮችን በቫቲካን ተቀብለው ያደረጉትን ንግግር አስታውሰው፣ ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እና ተቋማት ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ሆነው እንዲያገለግሉ አደራ ማለታቸውንም ማለታቸውን ገልጸዋል። ቅድስት መንበር ከመንግሥታት ጋር በምታደርጋቸው ስምምነቶች መካከል አንዱና እጅግ አስፈላጊው ለሰው ልጅ የሚሰጠው ትኩረት እንደሆነ አስረድተዋል።

የቤተክርስቲያን ነጻነት እና የሐይማኖት ነጻነት፣

ቅድስት መንበር ከመንግሥታት ጋር ስለ ምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በተመለከተ የቅድስት መንበር አቋም ግልጽ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ፣ ቅድስት መንበር የቤተክርስቲያንን ነጻነትን በአንድ በኩል የሐይማኖት ነጻነትን በሌላ በኩል ትመለከታለች ብለው፣ በአገሮች መካከል የሚከናወን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቀዳሚ ዓላማውን በኤኮኖሚያዊ ማሕላዊ ግንኙነቶች ላይ እንደሚያተኩት አስረድተው እነዚህን የግንኙነት መንገዶች ቅድስት መንበር ተግባራዊ የምታደርግባቸው የዲፕሎማሲ እና የዓለም አቀፍ ሕግ አሰራሮች አሏት ብለዋል።

መልካም ዜናን ለሁሉ ማብሰር፣

ቅድስት መንበር በዓለም አቀፍ ደርጃ በተግባር ከምታከናውኗቸው የቆየ የዲፕሎማሲ መንገድ፣ በታሪክ ሂደትም ቢታይ፣ ከሁለት ሺህ ዓመታት ወዲህ የምታከናውነው ግንኙነት መሠረትን የሚያገኘው፣ ለዓለም በሙሉ ከምታበስረው የወንጌል መልካም ዜና መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተናገሩትን አስታውሰው፣ ዛሬ በዘመናችም ቢሆን ወንጌልን ለሕዝቦች በሙሉ የማብሰር ጎዳናን የተከተለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የቤተክርስቲያን ተልዕኮ መሆኑን ቅድስት መንበር ታረጋግጣለች ብለዋል።

በማንኛውም መንገድ ውይይት ይደረግ፣

በሕዝቦች መካከልም ይሁን በምንግሥታት መካከል ውይይቶችን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ ለዲፕሎማሲ መዳበር ውይይት አንዱ መንገድ መሆኑን ገልጸው፣ መስዋዕትነትን ከፍለውም ቢሆን ውይይትን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ከውይይት ማንኛውንም ዓይነት ለመሻገር የሚያስችል ድልድይ መገነባት እንደሚቻል፣ የመፍትሄ አቅጣጫን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ለተቸገሩት ወይም ለደሄዩት ጥንቃቄን ማድረግ፣

በዲፕሎማሲ ጎዳና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዋና ርዕስ አለም አቀፍ ትብብር መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ፣ በኤኮኖሚ ያደጉት አገሮች በማደግ ላይ ለሚገኙት አገሮች የሚያደርጉት ዕርዳታ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ተልዕኮ፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በማደግ ላይ ላሉት አገሮች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለዕድገት በሚያመች መንገድ ዕርዳታን እንዲያደርጉ ማሳሰብና ሃሳብ ማካፈል እንደሆነ አስረድተዋል። አንዳንድ ጊዜ አንድ አገር የሚገኝበትን የኤኮኖሚ ሁኔታ ቤተክርስቲያን የምታወቀውን ያህል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደማያውቅ ያስረዱት ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ አገሮችን በማስተዋወቅ ደረጃ የቅድስት መንበር ሚና ትልቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር፣

መሠረታዊ የሆኑ የሰው ልጅ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ መብቶችን በተመለከተ፣ እነዚህ መብቶች ከሐይማኖት ነጻነት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክተው የተናገሩት ፕሮፌሰር ቡዎኖሞ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከኢነዚህ ሰብዓዊ መብቶች ውጭ እንዳልሆነና ቤተክርስቲያንም የሰው ልጆች ድነትን እንዲያገኝ በምታደርገው የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የሐይማኖት ነጻነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው ቅድስት መንበር የሐይማኖት ነጻነ ይከብር ብላ ድምጽ በምታሰማበት ጊዜ ለካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የእምነት ተከታዮች መሆኑን በሮም ከተማ ለሚገኝ የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንትና የዓለም አቀፍ ሕግ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ቪንቼንሶ ቡዎኖሞ አስረድተዋል።    

15 January 2019, 15:52