ፈልግ

የፓናማ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓልን ለማክበር ተዘጋጅታለች፣ የፓናማ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓልን ለማክበር ተዘጋጅታለች፣ 

ፓናማ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለመቀበል መዘጋጀቷን አሳወቀች።

የበዓሉ ቀዳሚ ዓላማ የተካፋይ ወጣቶች ቁጥር ማሳደግ ሳይሆን ጸሎት እንደሆነና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ይህን ተልዕኮ የሰጡት ለፓናማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የመካከለኛ የላቲን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የምታስተናግደው የመካከለኛው የላቲን አሜርካ አገር ፓናማ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስንና ከእርሳቸውም ጋር ወደ ሁለት መቶ ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችን ለመቀበል ዝግጅቷን ማጠናቀቋ ታውቋል። በዝግጅቱ መላው የመካከለኛ የላቲን አሜርካ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤና የፓናማ መንግሥት መሳተፉን የዝግጅት ኮሚቴ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጃንካርሎ ካንዴንዶ ከስፍራው ለሬዲዮ ቫቲካን ገልጸዋል።

ዘንድሮ በፓናማ በተዘጋጀውን 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት ከ37 ሺህ በላይ መመዝገባቸውን፣ ከ167 ሺህ ወጣቶች በላይ ደግሞ በሚቀጥሉት ቀናት እንደሚመዘገቡ ታውቋል። ይህም ጠቅላላ የበዓሉ ተካፋይ የሚሆኑ ወጣቶችን ቁጥር ከ 200 ሺህ በላይ እንደሚያደርገውና ወጣቶቹም ከ155 አግሮች የሚመጡ መሆናቸው ታውቋል። ከእነዚህ ወጣቶች በተጨማሪ በዓሉ ወደ ሚከበርበት አገር ወደ ፓናማ መምጣት የማይችሉ አንድ ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በአምስቱም አህጉራት የሚገኙ ወጣቶች በዓሉን በየአገሮቻቸው እንደሚያከብሩት ታውቋል። በዝግጅቱ መርሃ ግብር መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመላው የዓለም ወጣቶች ጋር ሆነው በዓሉን ለማክበር ወደ ፓናማ የሚደርሱት ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2011 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።

የጋራ ጸሎትን ለማቅረብ የተዘጋጀ ክብረ በዓል፣

ቀዳሚ ዓላማ የበዓሉ ተካፋይ ወጣቶች ቁጥር ማደግ ሳይሆን ጸሎት እንደሆነ የዝግጅት ኮሚቴ ቃል አቀባይ አቶ ጃንካርሎ ከፓናማ ገልጸው ይህም ለአገራቸው እጅግ አስፈላጊ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ይህን ተልዕኮ የሰጡት ለፓናማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የመካከለኛ የላቲን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እንደሆነ አስረድተዋል። ይህን ታላቅ በዓል ለማዘጋጀት የተነሱት የፓናማ ብጹዓን ጳጳሳት ብቻ ሳይሆኑ የአገሪቱ መንግሥትም፣ በዓለም ወጣቶች በዓል ዝግጅት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ የራሱን የአስተዳደር መንገድን በመከተል፣ በበዓሉ ዝግጅት ላይ በመካፈሉ ለቤተክርስቲያን ትልቅ እገዛን አድርጓል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለመቀበል ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፣

ለ34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ዝግጅት ፓናማ አቅም የፈቀዳትን ሁሉ አድርጋለች ያሉት የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ቃል አቀባይ አቶ ጃንካርሎ ባሁኑ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለመቀበል ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፣ የሚጓዙበት መኪናም ተመርጧል ብለው። በተጨማሪም በፓናማ የሚገኙ የቤተልሔም የደሃ ቤተሰብ ማሕበር ደናግል ለጸሎት የሚያገለግል ወደ አንድ ሚሊዮን ከግማሽ የሚሆን መቁጠሪያ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢጣሊያ ወጣቶች በበዓሉ ላይ መሳተፍን በተመለከተ፣

ከአገሩ እርቀትና የትምህርት ወቅት በመሆኑ ወደ ፓናማ በመጓዝ በበዓሉ ላይ የሚገኙ የኢጣሊያ ወጣቶች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ክቡር አባ ሚካኤል ፋላብሬቲ፣ በኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ገልጸው ሆኖም ዘንድሮ በፓናማ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የሚካፈሉ የወጣቶች ቁጥር 1,300 መሆናቸውን ገልጸዋል።

በበርካታ ሀገረ ስብከቶችም ተመሳሳይ የወጣቶች በዓል ይከበራል፣

ከኢጣሊያ በዓሉ ወደሚከበርበት አገር ወደ ፓናማ የሚጓዝ የወጣት ቁጥር ትንሽ ቢሆንም፣ በኢጣሊያ ውስጥ በሚገኙት በርካታ ሀገረ ስብከቶች ተመሳሳይ የወጣቶች በዓል እንደሚከበር አባ ሚካኤል ፋላብሬቲ ገልጸው የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ወጣቶች በዓሉን እርስ በርስ ለመገናኘት፣ አብረው ለመጸለይና መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለመካፈል የሚያስችላቸውን ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዓሉ ከሚከበርበት ከፓናማ በቀጥታ በሚተላለፍ የቪዲዮ ምስል አማካይነት ተገናኝተው በስፍራው የሚደረጉ ፕሮግራሞችን አብረዋቸው የሚካፈሉ መሆኑን አባ ሚካኤል ፋላብሬቲ አስረድተዋል።                       

09 January 2019, 16:17