ፈልግ

ቅድስት መንበር የወከለቻቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ቅድስት መንበር የወከለቻቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ 

ካርዲናል ፓሮሊን “የአየር ንብረት ለውጥ ለማስተካከል ቅን የፖለቲካ ፍላጎት ያስፈልጋል”።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመቀጠልም የቅድስት መንበርን ሦስት የመፍትሄ ሃሳቦችን ሲገልጹ፣ ግልጽና መሠረት ያለውን ስነ ምግባር መከተል፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ፣ ድህነትን ማስወገድ፣ ለሁለ ገብ የሰው ልጅ እድገት ጥረት ማድረግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ የሚያግዙ፣ በሃላፊነት የተሞሉ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ በዛሬና በነገ የሰው ልጅ ቀዳሚ ፍላጎቶች ላይ ትኩረትን ያደረገ ዘላቂነት ያለው ጥረት እንደሆኑ አብራርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በፖላንድ ካቶቪች ከተማ እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። የብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን መልዕክት የሚያተኩረው ከዚህ በፊት በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ደንቦችን የየአገራቱ ማህበራዊ ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ የገቡትን ቃል ኪዳን የሚያጠናክር ነው ተብሏል።

የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ በ2007 ዓ. ም. የተካሄደው ጉባኤ ዋና ዓላማ የምድርን ሙቀት መጨመር ተከትሎ በፍጥረታት ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ የመፍትሄ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት የተደረገበት እንደነበር ይታወሳል። በ2007 ዓ. ም. ፓሪስ ላይ የተቀመጠው ጉባኤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ለዲፕሎማቶች ካሰሙት የስጋት ንግግር በኋላ እንደሆነ ይታወሳል።   

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ የላኩትን የከበረ ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ፣ ቅዱስነታቸው ጉባኤውን በሙሉ ልብ እንደሚደግፉትና ብርታትንም እንደሚሰጡ የገልጹበትን መልዕክት በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው አሰምተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በንግግራቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል አስቸኳይ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በጉባኤው ከቀረቡት ሪፖርቶች እንደተገነዘቡት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል የመንግሥታት ሕብረት በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ የገቡትን ቃል ለመፈጸም ያሳዩት ጥረትና ያደረጉት እንቅስቃሴ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል። ከመጠን በላይ የሆነውን የምድር ሙቀት ለመገደብ እድሉ አሁንም አለ ያሉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ መንግሥታት የገቡትን ቃል ኪዳን ፍሬያማ ለማደረግ ግልጽ፣ ዘላቂና ጠንካራ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ወይም ፍላጎት ያስፈልጋል የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰነድ በመጥቀስ አሳስበዋል። አክለውም እነዚህን መንገዶች ባስቸኳይ ተግባራዊ ለማድረግ ቴክኖሎጂን መሠረት ወዳደረጉ ነጻ የልማት ሞዴል መሸጋገርና የተቃጠለ ጋዝ ልቀትን ከልክ በላይ በከባቢ አየር ውስጥ የመጨመር ባህሪያት ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ተግባር ላይ የሚውሉ ንድፈ ሃሳቦች፣

ብጹዕ ካርዲና ፓሮሊን፣ ነጻ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅን የሆኑ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት በመንግሥታት ወስጥ እንዳለ በማለት ለጉባኤው ተካፋዮች ጥያቄአቸውን አቅርበውላቸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመቀጠልም የቅድስት መንበርን ሦስት የመፍትሄ ሃሳቦችን ሲገልጹ፣ ግልጽና መሠረት ያለውን ስነ ምግባር መከተል፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ፣ ድህነትን ማስወገድ፣ ለሁለ ገብ የሰው ልጅ እድገት ጥረት ማድረግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ የሚያግዙ፣ በሃላፊነት የተሞሉ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ በዛሬና በነገ የሰው ልጅ ቀዳሚ ፍላጎቶች ላይ ትኩረትን ያደረገ ዘላቂነት ያለው ጥረት እንደሆኑ አብራርተዋል።

የተግባር ንደፈ ሃሳቦች፣

የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል ለወጡ እቅዶች ተግባራዊነት ከሚያግዙ መሠረታዊ መንገዶች መካከል ሙስናን መከላከል፣ በዕቅዶች አፈጻጸምና በውሳኔ አሰጣጥ ሕዝብን በሙሉ ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አሳስበዋል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ደንቦችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር፣ ማሕበረሰብን ከጉዳት መጠበቅ ወይም መከላከል፣ ድህነትን ማስወገድ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ለደረሰባቸው የሕብረተሰብ ክፍል ልዩ ትኩረትን መስጠት፣ ይህንን በተግባር ለመተርጎም ትምህርትን ለሁሉ ማዳረስ፣ ስልጠናን መስጠትና በሕዝቦች መካከል የአንድነትና የመተጋገዝ ፍላጎትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሕዝብ ድምጽ ይሰማ፣

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማከልም እነዚህንና ሌሎች ጠቃሚ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ከሕዝቦች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት፣ አስተያየቶቻቸውንም በጽሞና ማዳመጥ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው፣ የሳይንስ ጠበብትን፣ የሲቪል ማሕበራትን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማሳተፍ የፖለቲካ ሃይሎች ወይም መንግሥታት የሚወስዷቸው ውሳኔዎችና የገንዘብ ድጎማዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሳሰቡት ሁሉ ለሰው ልጅ ኑሮ ጤናማ የሆነ ሥፍራ እንዲኖር የሚያደርግ ሁኔታ እንዲመቻች አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 December 2018, 15:44