ካርዲናል ፓሮሊን “በኢራቅ ለሰማዕትነት የሚያበቃ እምነት ያላትን ቤተክርስቲያን ተመልክቻለሁ”።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በኢራቅ ያደረጉትን ጉብኝ ፈጽመው ወደ ቫቲካን ሲመለሱ ባሰሙት ንግግር፣ በኢራቅ ለሰማዕትነት የበቃች ቤተክርስቲያንን ተመልክተው መመለሳቸውን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሎን ኢራቅን የጎበኙት የላቲን ስርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠርን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ከአገሩ ምዕመናን ጋር ለማክበር እነደሆነም ታውቋል። ብጹዕነታቸው በጉብኝታቸው ወቅት የኢራቅ ቤተክርስቲያን በሚያጋጥማት በተለያዩ ስቃዮች መካከልም ቢሆን ከወንጌል የሚገኘውን ደስታ በመመስከር ላይ መሆኗን መመልከታቸአውን ተናገረዋል። ካርዲናል ፓሮሊን የኢራቅ ምዕመናን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዕለታት አንድ ቀን ኢራቅን ይጎበኛሉ የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸው በተጨማሪም በክርስቲያን ማሕበረሰብና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ህብረትን በመፍጠር በአገሪቱ ሰላም ማምጣት እጅግ አስፈላጊነት እንደሆነ አስረድተዋል።
ካርዲናል ፓሮሊን በንግግራቸው እንደገለጹት ከኢራቅ ክርስቲያኖች ጋር ያደረጉት ግንኙነት እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ከምዕመናኑ በኩል የተደረገላቸው አቀባበልም ደማቅ እንደነበር ተናገረዋል። በዚህ ጉዞ ወቅት ለኢራቅ ምዕመናን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከ ሐዋርያዊ ቡራኬን ማድረሳቸውን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኢራቅ ሕዝብ ያላቸውን ፍቅርና አለኝታነታቸውን፣ የሕዝቡን ማሕበራዊና መንፈሳዊ ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተሉ መግለጻቸውን አስረድተዋል። በማከልም ጉብኝታቸው የኢራቅ ሕዝብን ስቃይ በጥቂቱም ቢሆን የተጋሩበት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የሚታየውን የሰላም ተስፋን የተመለከቱበት፣ ይህን ሁሉ ለመገንዘብ እንዲችሉ ዕድሉን ለሰጣቸው እግዚአብሔር ምስጋናቸውን ያቀረቡበት አጋጣሚ እንደሆነ ተናግረዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ለምዕመናኑ ባቀረቧቸው የወንጌል አስተምሮአቸው የኢራቅ ምዕመናን ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሕያው ምስክር መሆናቸውን ተናግረዋል። ለዚህም ኩላዊት ቤተክርስቲያን የኢራቅ ምዕመናን እስከ ዛሬ ላሳለፉት የመከራ ሕይወት ዘወትር እንደምታመሰግን ገልጸው ለሌሎች ክርስቲያኖች መልካም ምሳሌ መሆናቸው ገልጸው ይህ ምሳሌ ለሌሎችም ትምህርት መሆን እንደሚችል ተናገረዋል። በማከልም ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በዓለም ውስጥ በሚደርስ መከራ ውስጥ መኖርና ከእግዚአብሔር በኩል በሚሰጥ መጽናናት ብርታትን ማግኘት የሚለውን አስታውሰዋል።
በኢራቅ ያደረጉትን ጉብኝት ያስታወሱት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹ ካርዲናል ፓሮሊን የሞሱል ከተማ በጦርነት መውደም እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ መኖሪያ ቤቶችና በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እንደወደሙ መመልካታቸውን በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህንን የጥፋት ዘመን የተሻገሩ በርካታ ምዕመናን አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶችና ሕጻናት በሕብረት ሆነው የምስጋና ጸሎታቸውን በዜማ ማቅረባቸውን ተናገረዋል። በኢራቅ የሞሱል ከተማን በጎበኙበት ወቅት ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት ከቦታ ቦታ በመዘዋወር እንደተመለከቱትና በዚህም ወቅት ከከተማይቱ የመንግስት ባለስልጣናት ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።
የአገሪቱ ምዕመናን ከቅድስት መንበር በኩል ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተላከ መልዕክተኛ መምጣቱን ሲሰሙ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው መግለጻቸውንም ተናግረዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም ለኢራቅ ሕዝብ በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸው በአዲሱ የአውሮጳዊያኑ ዓመትም ቢሆን ሕይወታቸውን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ላዋሉት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እግዚአብሔር አምላክ በቸርነቱ ሙሉ ጤናን እንዲሰጣቸው፣ በችግርና በጦርነት መካከል ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ለሚያበረክቱት ድጋፍ አቅም እንዲሆናቸው ተመኝተውላቸዋል።