ፈልግ

የቤተሰብን ጉዳይ የሚመለከት ዓለም አቀፍ ተቋም መመስረቱ ተነገረ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታዋቂ ድርጅቶች ጥምረት እነርሱም በሮም የሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ማዕከል፣ በስፔን ሙርሲያ ከተማ የሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲትና ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጥናት ማዕከል በጥምረት ሆነው የቤተሰብን ጉዳይ የሚመለከት ዓለም አቀፍ ተቋም መመስረታቸውን በቫቲካን ከተማ ባቀረቡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

የሕይወት ጥናት አካዳሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቸንሶ ፓሊያ “ቤተሰብ የማሕበረሰብ ሃብት ነው” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለማብራራት ባደረጉት ንግግራቸው ወቅት ቤተሰብንና የቤተሰብን ጉዳይ የሚከታተል ዓለም አቀፍ ተቋም መመስረቱን በቫቲካን ከተማ ባቀረቡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል። ይህን ዓለም አቀፍ ማዕከል ለማቋቋም በጋራ የተሰባብሰቡት ተቋማትም በሮም የሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የነገረ መለኮትና የጋብቻ ህይወት ጥናት ማዕከል፣ በስፔን የሚገኝ የሙርሲያ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲና በኢጣሊያ ውስጥ በሚላኖ ከተማ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ሕይወት ጥናት ማዕከል እንደሆኑ ገልጸዋል።

የቤተሰብ ሕይወት እንዲቀጥል ላደረጉት የኖቬል ሽልማት ሊሰጣቸው ይገባል፣

የቤተሰብ ሕይወት ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ በዘርፉ የተለየዩ ጥናቶችን በማድረግ ውጤት ያስመዘገቡ ተቋማትና ግለሰቦች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 20 የጥናት ማዕከላት በአስራ አምስት አገሮች ውስጥ መኖራቸውን ብጹዕ አቡነ ፓሊያ አስረድተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ኢጣሊያ፣ ስፔን፣ ፊንላንድ፣ ስሎቫኪያ፣ ቸክ ሪፓብሊክ፣ ሰሜን አሜርካ፣ ሜክስኮ፣ አርጀንቲና፣ ቺሊ፣ በኒን፣ ኬንያና ሆንግ ኮንግ መሆናቸውን ገልጸዋል። በጋዜጣዊ መግለጫቸው ብጹዕ አቡነ ቪንቸንሶ ፓሊያ እንደተናገሩት፣ ሕብረተሰባችን በተለያዩ ችግሮች ወስጥ በወደቀበት ባሁኑ ጊዜ ቤተሰብ የሕበረተሰብ  ዋና መሠረት በመሆን ሰፊ ሚናን ይጫወታል ብለዋል። በመሆኑም በችግሮች ውስጥም ቢሆን ሕብረተሰባችን ወደ ፊት እንዲጓዝ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኝ የቤተሰብ ክፍል የኖቬል ሽልማት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጥናት ማዕከልን በጥምረት የመሰረቱት ታዋቂ ተቋማትም በበኩላቸው የጥናት ማዕከሉ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስር ከሚገኙት የትምህርት ተቋማት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑት የትምህርት ተቋማት ጋር በሕብረት ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። ትኩረት በመስጠት ጥናታዊ ስራቸውን የሚያካሂዱባቸው ዘርፎችም በሕብረተሰብ ዘንድ የሴቶች ሚና፣ ሕጻናትና የዘመናችን ቴክኖሎጂዎችና የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎች የሚሉ እንደሚገኙበት፣ በሚላኖ ከተማ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ሕይወት ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፍራንቸስኮ በሌቲ ገልጸዋል።

07 December 2018, 16:19