ፈልግ

አራቱ “ታላላቅ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል አርእስት የተሰራ ጥናታዊ ፊልም ይፋ እንደ ሚሆን ተገለጽ

በመጪው ታኅሣሥ 04/2011 ዓ.ም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አራቱ “ታላላቅ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል አርእስት የቀረበ አንድ ጥናታዊ ፊልም በሮም ሀገረ ስብከት ይፋ እንደ ሚደረግ ይጠበቃል። ይህ በቴለቪዢን የሚተላለፈው ጥናታዊ ፊሊም የቫቲካን የኮሚኒኬሽን እና የሚዲያ ቢሮ ከቅድስት መንበር የሕትመት እና የዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር የቀረበ መሆኑን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህ ጥናታዊ ፊልም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ታላላቅ የተባሉ አራት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳትን በመምረጥ እነዚህ አራት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በርዕሳነ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ የከወኑትን አንኳር ተግባራትን እና ተግዳሮቶችን ያካተተ እንደ ሆነ ለመረዳት ተችሉዋል። በዚህም መሰረት በዚህ ጥናታዊ ፊል ውስጥ የተካተቱት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት የሚከተሉት ናቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኔደክቶስ 16ኛ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን አራቱ “ታላላቅ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል አርእስት የቀረበው ጥናታዊ ፊልም በተመለከተ መግለጫ የሰጡት በአሁኑ ወቅት የቅድስት መንበር የመገናኛ ብዙዓን ኤዲቶሪያል የበላይ ጽሕፈት ቤት የበላይ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ፓውሎ ሩፊኒ እንደ ገለጹት ይህ አራቱ “ታላላቅ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል አርእስት የቀረበው ጥናታዊ ፊልም ከላይ የተጠቀሱትን አራት ታላላቅ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳትን እኩል በሆነ መልኩ በማካተት የቀረበ የ75 ደቂቃ ቆይታ ያለው ጥናታዊ ፊልም እንደ ሆነ በመግለጫው ወቅት ይፋ አድርገዋል።

በዚህ ጥናታዊ ፊልም ውስጥ የተካተቱት እያንዳንዱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በድርጊታቸው የዓለምን እና የቤተ ክርስቲያንን የታሪክን ጎዳና ለውጠው እንደ ነበረ የሚዘግብ ጥናታዊ ፊልም እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ደግሞ ከአለፉት 60 አመታት ወዲህ በቤተ ክርስቲያን እና እንዲሁም በተለያዩ የዓለማችን ማኅበራዊ እና ፖሌትካዊ ጉዳዮች ውስጥ በእነዚህ አራቱ “ታላላቅ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት” አማካይነት የተከሰቱትን አብይት ድርጊቶች እና ተግዳሮቶቻቸውን ያካተተ ጥናታዊ ፊልም ነው። ይህ ጥናታዊ ፊልም ትረካውን የሚጀምረው “ለውጥ አራማጁ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት” በማለት ከሰየማቸው ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሕይወት እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን በመቀጠል “ርዕሰ ሊቃነ ጵጵስናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት” እና በይፋ ያልወጣ፣ ነገር ግን ጣፋጭ ሆነው ያለፉ በማለት የሰየማቸው ደግሞ የቀድሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በነዴክቶስ 16ኛ እንደ ሆነ ለመረዳት ተችሉዋል። በሦስተኛው ሚሌኒየም የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጀልባ በወጣትነት እድሜያቸው የተሳፈሩ እና በዚህ ጥናታዊ ፊልም ውስጥ “የእግዚአብሔር አትሌት” የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ሁለተኛ እንደ ሆኑ የተገለጸ ሲሆን በመጨረሻም የሁለተኛውን የቫቲካን ጉባሄ በታልቅ ትህትና ያስጀመሩ እና ወደ ፍጻሜው እንዲደርስ አቅጣጫ በማስቀመጥ ታሪክ የሰሩት በዚህ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ “መልካሙ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል ቅጽል ስም የተጠቀሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

በዚህ “ታላላቅ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል ጥናታዊ ፊልም ውስጥ የተጠቀሱት አራቱን ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በቀዳሚነት የተጠቀሱትን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ታሪክ እና አብይት ተግባሮቻቸውን በሚቀጥለው ዝግጅታችን እናስቃኝእችኋለን። አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

28 November 2018, 16:02