ፈልግ

TOPSHOT-PALESTINIAN-ISRAEL-GAZA-CHILDREN-POVERTY TOPSHOT-PALESTINIAN-ISRAEL-GAZA-CHILDREN-POVERTY 

ለፍልስጤም ተፈናቃዮችና ስደተኞች ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ ባቀረቡት መረጃ መሠረት ባሁኑ ወቅት በጋዛ ብቻ 5.6 ሚሊዮን ተፈናቃዮች እንደሚገኙና የሥራ አጥ ቁጥርም 43 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር ለፍልስጤም ተፈናቃዮች ተጨማሪ ድጋፍን፣ ሁለት ራስ ገዝ መንግሥታት የሚል ሃሳብም ብቸኛ የመፍትሄ መንገድ መሆኑን እንደምትደግፍ አስታውቃ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ተበታትነው በስደት ላይ ለሚገኙት የፍልስጤም ዜጎች በቂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተማጽናለች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢና እንደራሴ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ትናንት በኒዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ጠቅላላ ስብሰባ እንዳስገነዘቡት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን የዕርዳታና የሥራ አቅርቦት አስተባባሪ ክፍል ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው አስታውቀዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፍልስጤም ተፈናቃዮች ዕርዳታ አቅርቦት፣

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ ባቀረቡት መረጃ መሠረት ባሁኑ ወቅት በጋዛ ብቻ 5.6 ሚሊዮን ተፈናቃዮች እንደሚገኙና የሥራ አጥ ቁጥርም 43 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ በገለጻቸው እንዳስገነዘቡት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን የዕርዳታና የሥራ ዕድል አቅርቦት አስተባባሪ ክፍል ከ13,000 በላይ የፍልስጤም ተፈናቃዮች የሥራ ዕድል እንደሚከፍት ገልጸው አስተባባሪ ክፍሉ የፍልስጤም ተፈናቃዮች የከፋ ችግር እንዳይገጥማቸው የቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢና እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን የዕርዳታና የሥራ አቅርቦት አስተባባሪ ክፍልን ያጋጠመውን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ይህም ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ገልጸው የዓለም አቀፉ ዕርዳታ ለጋሽ አገሮች ችግሮችን ለማቃለል የሚያድረጉትን ጥረት በተግባር እንዲያሳዩ አሳስበውል። የፍልስጤም ስደተኞችና ተፈናቃዮች በብዛት በሚገኙባቸው አገሮች እነርሱም በዌስት ባንክ፣ በጋዛ፣ በዮርዳኖስ፣ በሊባኖስና በሶርያ ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን አስቸኳይ እርዳታን እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።

ለፍልስጤም ስደተኞች ዝቅተኛ ትርጉም መሰጠት የለበትም፣

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በ1940 ዓ. ም. ለተሰደዱት ፍልስጤማዊያን ብቻ የሚሰጥ የስደተኛ መብት እውቅና እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሱ በተለያዩ ዕመታት የፍልስጤም ሕዝብ ሲሰደድና ሲፈናቀል የቆየ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ሕዝብ የስደተኛ መብት እውቅናን መንፈግ ከተባበሩት መንግሥታት ሊያገኙ የሚችሉትን ድጋፍ ማሳጣት ይሆናል ብለዋል። በመሆኑም አለም አቀፉ ማሕበረሰብ አስቸኳይ የችግሩ መፍትሄን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሁለት ራስ ገዝ መንግሥታ እንዲሆኑ የሚል የመፍትሄ ሃሳብ፣

ቅድስት መንበር ፍልስጤምና እስራኤል ሁለት ራስ ገዝ መንግሥታ ይሁኑ የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ከረጅም ጊዜ በኋላም ቢሆን ሰላምንና ዕርቅን በሁለቱ አገሮች መካከል እንደሚያመጣ ከታመነበት የተጀመረው ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው ጥያቄ ማቅረቧ ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ እነዚህ ሁለት ተደራዳሪዎች ወደ ስምምነት ደረጃ ላይ እስከሚደርሱ ጊዜን ስለሚወስድና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን የዕርዳታና የሥራ አቅርቦት የዚያኑ ያህል ስለሚቀጥል በ2012 ዓ. ም. ሊወድቅ የተቃረበው የአገልግሎት ዘመኑም ከወዲሁ መታደስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በንግግራቸው መጨረሻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች 70 ኛ አመት ሊከበር መቃረቡን አስታውሰው የፍልስጤም ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ጨምሮ መላው የዓለም ሕዝብ የሰብዓዊ መብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በማለት ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።                                   

14 November 2018, 15:02