ፈልግ

TOPSHOT-CAFRICA-CONFLICT-UN TOPSHOT-CAFRICA-CONFLICT-UN 

ቅድስት መንበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ተልዕኮን ለመገምገም መጋበዟ ተገለጸ።

ቅድስት መንበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላምን ለማስከበር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች፣ እንዲሁም የሰላም አስከባሪዎች ለሚፈጽሟቸው የሰላም ተልዕኮዎች ያላትን አድናቆት ገልጻ በበኩሏም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር ግጭቶችንና ጦርነቶችን ለማስወገድ በሚደረጉ ጥረቶች፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማፈላለግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩትመንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ እድገት ያለ ሰላም፣ ሰላምም ያለ እድገት ሊመጣ አይችልም ማለታቸው ተገለጸ። ብጹዕነታቸው ይህን የተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ዙሪያ ሰላምን ለማስከበር የሚያደርገው ተልዕኮን ለመገምገም በጋበዘው ስብሰባ ላይ እንደሆነ ታውቋል።

ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ እንደገለጹት ሰላምን ለማምጣት የሚደረጉት ጥረቶች አመጾች ወይም ጦርነቶች በሚቀሰቀሱበት ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች ብቻ ሳይሆኑ ጦርነቶች ከመቀስቀሳቸው በፊት ለሚፈጠሩት ቅራኔዎች መፍትሄዎችን የሚያፈላልግ፣ አመጾች ወይም ጦርነቶች እንዲቆሙ የሚያደርጉ ስምምነቶችም መከበራቸውንና ተግባር ላይ መዋላቸውን የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው ብለዋል።

እውነተኛ የሆነ ሁሉ አቀፍ እድገት ለማምጣት ከተፈለገ ጦርነቶች መወገድ አለባቸው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2007 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግራቸው “ጦርነት የሚከሰተው በጠቅላላ የሰብዓዊ መብቶች ላይ በሚደርሱ ጥሰቶች ምክንያት ነው” ያሉትን ያስታወሱት፣ በተባበሩት መስንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በሕዝቦችና በመንግሥታት መካከል ጦርነቶች እንዳይከሰቱ ሳንሰለች ጠንክረን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ በማከልም የሰብዓዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለው በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ላይ እንደተጠቀሰው፣ ወደ ጦርነት የሚያመሩ ቅራኔዎች የተፈጠሩባቸው መንግሥታት ወይም አገሮች መካከል የሚደረጉ ድርድሮች ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ አደራዳሪ አገሮችም ሳይሰለቹ የማስታረቅ ሥራቸውን ማከናወን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በሰላም ስምምነቶች የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው፣

ሰላምንና ጸጥታን ለማስከበር በሚደረጉ ጥረቶችና ድርድሮች መካከል የሴቶች ተሳትፎ ውስን እንደሆነ ያስረዱት ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲኖ ቢሆንም አመጾችን ለማስወገድና ሰላምን ለማስፈን የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ሰፊ እንደሆነ ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲቶ በማከልም ሴቶች አመጾችና ጦርነቶች በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ቀጥተኛ የሰላም መልዕክተኞች እንደሆኑ በጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እንክብካቤን፣ ርህራሄንና ምህረት ማድረግን በማስተማር ተወዳዳሪ እንደሌላቸው አስረድተው እርቅን ለማውረድ በሚደረጉ የመጀመሪያ ወቅት ሂደቶችም የሚቻወቱት ሚና ሰፊ እንደሆነ አስረድተዋል። እድገት ያለ ሰላም፣ ሰላምም ያለ እድገት ሊመጣ አይችልም ያሉት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ፣ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ቅድስት መንበር በዓለም ዙሪያ ለሚከሰቱት ግጭቶች መፍትሄን ለማግኘት የምታደርገው ጥረት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። እድገት፣ ጸጥታና ሰብዓዊ መብቶችን ማስጠበቅ የተገናኙ እንደሆነ ያስረዱት ብጹዕነታቸው፣ እድገት ያለ ሰላም፣ ሰላምም ያለ እድገት ሊመጣ አይችልም ብለዋል። አቡነ ቤርናዲቶ ገለጻቸውን በመቀጠል የጸጥታ ማነስ፣ የፍትህ መጓደል፣ ሙስናን ጨምሮ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር እነዚህ በሙሉ የጦርነትና የአመጽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል። ግጭቶችና ጦርነቶች የሚከሰቱባቸው አገሮች እድገትን ሊያመጡ ወይም ሊበለጽጉ አይችሉም ብለዋል። በግጭቶችና በጦርነቶች መካከል የሚኖር፣ የሕይወት ዋስትናን ያላገኘ ዜጋ እድገትን ለማምጣት የሚያስችለውን አቅምና እውቀት በተግባር ላይ ሊያውሉ አይችልም ብለው ሁሉን የሚያካትትና ዘላቂነት ያለው እድገት የማሕበረሰብን ሕይወት ከመለወጥ ባሻገር ግጭቶችን ለማስቆም የተሻለ መከላከያ መንገድ ነው ብለዋል።

ጦርነት ሰዎችን በግዴታ እንዲፈናቀሉ ያደርጋቸዋል፣

ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ሰዎች በጦርነት ምክንያት በግዴታ እንዲፈናቀሉ መደረጋቸው ቅድስት መንበርን እጅግ እንዳሳሰባት ገልጸው ሰዎችን በግድ እንዲፈናቀሉ ማድረግ ለመንግሥታትና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ጦርነትና ግጭት የበለጠ እንድስፋፋ ለማድረግ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በእነዚህ ጦርነቶች ምክንያት የከፋ አደጋና ጥፋት የሚደርስባቸውም በቁጥር ዝቅተኛ በሆኑት ማሕበረሰብ ወይም የእምነት ተከታዮች መካከል እንደሆነ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አስረድተዋል። በግጭቶችና በሚደርስባቸው መከራ ምክንያት ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ለሚደረጉት ሰዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ውስጥ የተጠቀሱ ሰብዓዊ መብቶች፣ ለሰው ልጅ ሊሰጥ የሚገባው ክብር በተግባር እንዲገለጽ ማድረግ የቅድስት መንበር ቀዳሚ ተልዕኮ እንደሆነ አቡነ ቤርናርዲቶ ገልጸዋል። በሚደርስባቸው ችግሮች ምክንያት ለሚፈናቀሉት ወይም ለሚሰደዱት ሰዎች በመራራት በደረሱበት ስፍራ ወይም አገር በክብር ተቀብሏቸው ማስተናገድ፣ መንከባከብ፣ የሚኖሩበት ሕብረተሰብም ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግና ስደተኞች ወይም ተፈናቃዮች ከሚኖሩበት ሕብረተሰብ መካከል የሥራ ዕድል ተሰጥቷቸው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማሳሰባቸውን ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲቶ ገልጸዋል።

ቅድስት መንበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ተልዕኮዎችን አወደሰች፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ቅድስት መንበር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላምን ለማስከበር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች፣ እንዲሁም የሰላም አስከባሪዎች ለሚፈጽሟቸው የሰላም ተልዕኮዎች ያላትን አድናቆት ገልጸው፣ ቅድስት መንበርም በበኩሏ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር ግጭቶችንና ጦርነቶችን ለማስወገድ በሚደረጉ ጥረቶች፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማፈላለጉ ጥረት ላይ ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

05 November 2018, 15:23