ፈልግ

Arcivescovo Bernadito Auza, Osservatore Permanente della Santa Sede presso le Nazioni Unite a New York, ad un evento a ONU il 4 giugno 2018 Arcivescovo Bernadito Auza, Osservatore Permanente della Santa Sede presso le Nazioni Unite a New York, ad un evento a ONU il 4 giugno 2018 

ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በኒዮርክ የአፍሪቃ የሰላምና የጸጥታ ጉባኤን መካፈላቸው ተገለጸ።

ለአፍሪቃ አገሮች እድገት፣ ለአፍሪቃ አህጉር ሰላምና ጸጥታ ልዩ ሚናን የሚጫወት የሰላም አስከባሪ ሃይል ሊኖር ይገባል። ይህም ለአካባቢው ወይም ለአሕጉሩ ሕዝቦች ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ሌሎችንም አካባቢዎችን ሊጠቅም ይችላል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢና እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በኒዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስለ አፍሪቃ ሰላምና ጸጥታን አስመልክቶ ትናንት ማክሰኞ ህዳር 11 ቀን 2011 ዓ. ም. ባዘጋጀው ነጻ የውይይት መድረክ ላይ መገኘታቸው ታውቋል። የነጻ ውይይቱ ርዕስ በአፍሪቃ ውስጥ ሰላምንና ጸጥታን የማስጠበቅ ተግባር ማጠናከር የሚል እንደነበር ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ለውይይት መድረኩ ያቀረቡት ንግግር ሙሉ ይዘት ትርጉም እንደሚከተለው ቀርቧል።

“ክቡር ፕሬዚደንት፣

በአፍሪቃ ውስጥ ሰላምንና ጸጥታን የማስጠበቅ ተግባር በሚል ርዕስ፣ መላውን የዓለም ማሕበረሰብን እያስጨነቀ የሚገኘውንና ባሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ በሰባት አገሮች የሰላምና የጸጥታ ማስከበር ተልዕኮውን በማበርከት ላይ ስለሚገኝ የሰላምና የጸጥታ ሃይል በማስመልከት ስላዘጋጀችው ነጻ የውይይት መድረክ የቻይናን ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት፣ ቅድስት መንበር ምስጋናዋን ታቀርባለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላምና የጸጥታ አስከባሪ ሃይል በዓለም ዙሪያ ተሰማርቶ እንደሚገኝ በግልጽ የሚታወቅ ነው። እጅግ በተከፋፈል ዓለም ውስጥ ሰላም የማስከበር ተግባር የዓለሙ ማሕበረሰብ ከምን ጊዜም በበለጠ በዲፕሎማሲ ሥራዎች፣ በኤኮኖሚና በባለሞያ አቅርቦትና በሰላምና ጸጥታ አስከባሪ ሃይል ምደባ ለመተባበር የሚያስችል ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል። ባሁኑ ወቅት ሰላምን መልሶ መገንባት፣ ንጹሃን ዜጎችን ከሞት አድጋ መከላከል፣ በአገሮች የዘላቂ ሰላምና ፍትህ መሠረቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ፖለቲካዊ ሂደቶችን ማመቻቸት መጠነ ሰፊ ሥራን ይጠይቃል።

 

አንዳንድ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ስር ሆነው መንግሥታትንና ሕዝቦችን ለማገናኘት የሚሰሩ ወንድና ሴት ሰራተኞች ለሰላም ጠንቅ በሆኑት ታጥቁ አሸባሪዎች ሲገደሉ እናያለን።  መሣሪያ ታጣቂ አሸባሪ ቡድኖች በአፍሪቃ አህጉር ውስጥ በአንድ አገር ውስጥ ወይም ከአገር ወደ አገር እየተንቀሳቀሱ የአገሮችን ጸጥታ እያናጉ ይገኛል። ሰላምን የማስጠበቁ ተግባር አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ትርጉም ይሰጠውና ሰላም በሁሉም ስፍራ የሚገኝ፣ ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ ብቻ እንደሚያስፈልግ ተደርጎ ይታሰባል። ሁላችንም እንደምናውቀውና እንደምንመለከተው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ለሕይወታቸው እጅግ አስጊ በሆኑ አካባቢዎች ሆነው፣ በጦርነትና በእርስ በእርስ ግጭቶች ለተጎዱ እርዳታ ፈላጊዎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማበርከት ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ የሰላም አስከባሪዎች መካከል ብዙዎቹ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። የሰላም አስከባሪዎች ለከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነትና ዛሬም ቢሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማበርከት ላይ ያለው ተልዕኮ ሳይጋነን ወይም በሕዝቦች መካከል የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ጾታዊ ጥቃቶች በገሃድ እየወጡ መሆናቸው ይታወቃል።

 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለአፍሪቃ ልማት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚታወቅ ሲሆን ለሰላም አስከባር ሃይል የሚመደብ የገንዘብ መጠን ለዓለማችን ጦር ሠራዊት ከሚመደብ የገንዘብ መጠን ጋር ሲስተካከል እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ይስተዋላል። ግጭቶችንና ጦርነቶችን ለማስወገድ ከሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጎን ለጎን ለሰላም ማስከበር አገልግሎት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ መጠን ሊያድግ ይገባል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጉተሬዝ እንዳስገነዘቡ “መልካም ውጤቶችን ለማስገንዘብ ከተፈለገ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች፣ ጫንቃችን ላይ ያሉትን ከባድ ሸክሞችና ሃላፊነቶች በጋራ መወጣት አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

 

ክቡር ፕሬዚደንት፣

እውነተኛ ውጤትን ለማስመዝገብ፣ የአፍሪቃ ወጣት ትውልድን በማስተባበር፣ የሚኖርበትን አገር ለማሳደግና የአገር መሪም እንዲሆን የሚያዘጋጅ፣ ጥራትን የጠበቀ የትምህርት ዕድል፣ በተወለደበት አገር የራሱን ሕይወት በትክክል መምራት እንዲችል የሚረዳ የሥራ ዕድል እንዲኖር ያስፈልጋል። ይህ ከመሆኑ ይልቅ፣ በቁጥር በርካታ የአፍሪቃ ወጣቶች በሚያሳዝን መልኩ ምንም ዓይነት የትምህርትና የስልጠና ዕድል ሳያገኙ የቀሩ መኖራቸው ይታያል። ምንም ዓይነት የወደ ፊት ተስፋ ከሌላቸው ለብዝበዛና ለአመጽ ይጋለጣሉ። ይህን ችግር ለመከላከል ወይም ለመቀንስ እንዲቻል የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ልኡካን ጋር በመተባበር፣ አፍሪቃ ለብዙ ዘመናት የተነፈገችውን የወጣቶች ጉልበትንና የተፈጥሮ ሃብቷን ጥቅም ላይ ለማዋል ከሕዝቡ ጋር አብሮ የመስራት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል። ሕዝቡ ከብዝበዛና ከድህነት የማይወጣ ከሆነ፣ አንዳንድ ጊዜ እያወቁ የሚቀሰቅሷቸው ግጭቶችና ጦርነቶች እየተባባሱ የሚመጡ ከሆነ ውድ የሆነ የአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ለሕዝቡ እድገት ሳይውል በከንቱ ባክኖ ይቀራል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በህዳር ወር 2008 ዓ. ም. በመከከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ ባደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ የዚያችን አገር አገር የተፈጥሮ ሃብት ለመቀራመት የተቀመጡ፣ ነገር ግን ለዚያች ደሃ አገር ብልጽግናና እድገት ምንም ደንታ የሌላቸው ሃይላት መኖራቸውን ተመልክተዋል።

ክቡር ፕሬዚደንት፣

ለአፍሪቃ አገሮች እድገት፣ ለአፍሪቃ አህጉር ሰላምና ጸጥታ ልዩ ሚናን የሚጫወት የሰላም አስከባሪ ሃይል ሊኖር ይገባል። ይህም ለአካባቢው ወይም ለአሕጉሩ ሕዝቦች ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ሌሎችንም አካባቢዎችን ሊጠቅም ይችላል። አመሰግናለሁ”።

በማለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢና እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ትናንት ማክሰኞ ህዳር 11 ቀን 2011 ዓ. ም. በኒዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስለ አፍሪቃ ሰላምና ጸጥታን አስመልክቶ  ባዘጋጀው ነጻ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ያደረጉትን ንግግር አጥቃልለዋል።     

21 November 2018, 15:54