ፈልግ

2018.11.24 Corali 2018.11.24 Corali 

ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ መዘምራን በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ወደ ዓለም እንዲያዳርሱ ጠየቁ።

ከእግዚአብሔር የተሰጠንን የእምነታችንን የድነት ስጦታን እንዘምራለን፣ በእምነት ጎዳና የሚመራንን የተስፋ ሃይል በመጠባበቅ ላይ ሆነን እንዘምራለን፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ፍቅር በማድነቅ እንዘምራለን፣ በዓለማችን በርካታ ሰዎች የሚጠብቁትን የእግዚአብሔር ፍቅር እንዘምራ፣ እንጋራለንም፣ በመዝሙር ሐሴትንም እናደርጋለን፣ በመዝሙር ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ለእኛ የሚያደርግልንን ጥበቃ እንገልጻለን፣ በመዝሙር አማካይነት እግዚአብሔር በሚፈልገው አኳኋንና ስፍራ አገልግሎታችንን እናቀርባለን፣ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን አውቀን፣ እንደ እርሱ ፈቃድ በሕይወታችን ዘመን በሙሉ የትንሳኤው አምላክ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዘምራለን

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሶስተኛ ዙር ዓለም አቀፍ የመዝሙር አገልግሎት ጉባኤ መዝጊያን ምክንያት በማድረግ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተደረገው  የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ፣ በቅድስት መንበር አዲስ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ጉባኤውን ለተካፈሉት መዘምራን በሙሉ ውብና ማራኪ በሆኑ የዝማሬ አገልግሎታቸው አማካይነት  የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ወደ ዓለም ሁሉ ማዳረስ እንዳለባቸው አስታውሰዋል። ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ወቅትም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከላቸውን የሰላምታ መልዕክት ጉባኤውን ለተካፈሉት መዘምራን በሙሉ አድርሰዋል።

በቫቲካን ከተማ ለሶስት ቀናት በተካሄደውና ለሶስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የመዝሙር አገልግሎት ጉባኤ ላይ ከዓለም ዙሪያ የመጡ ከ8 ሺህ በላይ አባልት መካፈላቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ቅዳሜ ማታ ህዳር 15 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ላገኟቸው የጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግራቸው ልባዊ ሰላምታቸዋን አቅርበውላቸው፣ ለቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት ስምረት በመዝሙራቸው አማካይነት ለሚያበረክቱት የከበረ አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በቅድስት መንበር አዲስ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ በበኩላቸው በዕለቱ የወንጌል ምልዕክት በመታገዝ ባሰሙት ንግግር የኢየሱስ ክርስቶስ ነጉሥነት የዓለምን ስልጣንና ሃይል አስወግዶ፣ በስቃይና በሞት ላይ የመላይነትን በመጎናጸፍ በኋላም የትንሳኤ ክብር የተገለጸበት እንደሆነ አስገንዝበዋል። ለክርስቲያኖች እውነት ማለት ጽንሰ ሐሳብ ወይም ትዎሪ ሳይሆን በአካል የሚታይ እንደሆነ ገልጸው ለዚህ እውነትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክር እንደሆነ፣ ይህ እውነትም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በሙሉ ካለው መልካም ፍላጎትና ምኞት ፈጽሞ ሊለያይ እንደማይችል አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በውል እንድንገነዘብ የሚፈልገው እውነት፣ እግዚአብሔር ለዓለም በሙሉ የገለጠው ፍቅር፣ ለእያንዳንዳችን በግል በቃሉ አማካይነት፣ በድንቅ ሥራው፣ በተለይም በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ አማካይነት የገለጠልን ግልጽ ፍቅር እንደሆነ አስረድተዋል።

የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚመሰክሩ፣

የእግዚአብሔር እውነተኛ ፍቅር መላው ዓለም የሚጠብቀውና ዓለምንም ለመለወጥ አቅም ያለው በመሆኑ በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ በተለይም በውዳሴና በምስጋና መዝሙር መነገር አለበት ያሉት በቅድስት መንበር አዲስ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ በማካልም፣ እኛ በሃጢአታችን ብዛት ተጨንቀን ብንገኝም፣ በየዕለቱ በሃጢአት ወድቀን ብንገኝም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አያጎድልብንም ብለዋል። ከአርባ አገሮች ለመጡት የጉባኤው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግራቸው እንዳስገነዘቡት በውዳሴና በምስጋና መዝሙራቸው አማካይነት የእግዚአብሔርን ፍቅር ወደ ዓለም ሁሉ እንዲያዳርሱና፣ ቅዱስ አጎስጢኖስ እንዳለው መዘመር ማለት የአፍቃሪውን ማንነት በመዝሙር መግለጽ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ለእርሱ እንድንዘምር ያስገድደናል ያሉት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ደካማ እምነታችንን ለማሳደግ ብዙን ጊዜ በቂ ቃላት እንደማይገኙ አስታውሰው በዝማሬ የሚቀርብ የምስጋና የውዳሴ ጸሎት እምነታችን እንዲጎለብት ትልቅ እገዛ እንዳለው አስረድተዋል። ብጹዕ ፊዚኬላ በማከልም፣ ሕዝቦች በሙሉ፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችም በሙሉ ያገለግሉታል የሚለውን የነብዩ ዳንኤል ትንቢት ጠቅሰዋል።

መዝሙር የቤተክርስቲያን አገልግሎት ነው፣

በቅድስት መንበር አዲስ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ በንግግራቸው ማጠቃለያ በቤተክርስቲያን ስለሚቀርብ የመዝሙር አገልግሎት አስፈላጊነት ሲያስረዱ፣ በአምልኮ ስነ ስርዓት ወቅት የሚቀርቡ የምስጋናና የውዳሴ መዝሙሮች የእግዚአብሔር የፍቅር ምስጢር የሚገለጥበት እንደመሆኑ በሕይወት አካሄዳችን ውስጥ በተግባር በመታየት፣ ለሌሎችም መመስከር ያስፈልጋል ብለዋል። ከእግዚአብሔር የተሰጠንን የእምነታችንን ድነት ስጦታን እንዘምራለን፣ በእምነት ጎዳና የሚመራንን የተስፋ ሃይል በመጠባበቅ ላይ ሆነን እንዘምራለን፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ፍቅር በማድነቅ እንዘምራለን፣ በዓለማችን በርካታ ሰዎች የሚጠብቁትን የእግዚአብሔር ፍቅር እንዘምራ፣ እንጋራለንም፣  በመዝሙር ሐሴትንም እናደርጋለን፣ በመዝሙር ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ለእኛ የሚያደርግልንን ጥበቃ እንገልጻለን፣ በመዝሙር አማካይነት እግዚአብሔር በሚፈልገው አኳኋንና ስፍራ አገልግሎታችንን እናቀርባለን፣ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን አውቀን፣ እንደ እርሱ ፈቃድ በሕይወታችን ዘመን በሙሉ የትንሳኤው አምላክ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዘምራለን በማለት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ሶስተኛ ዙር በተካሄደው ዓለም አቀፍ የመዝሙር አገልግሎት ጉባኤ ለተካፈሉት ያደረጉትን ንግግር አጠቃልለዋል።                 

26 November 2018, 16:09