ፈልግ

Intervista Gabriella Gambino Intervista Gabriella Gambino 

ፍቅር በቂ ጊዜ መስጠትንና ታማኝነትን የሚጠይቅ መሆኑ ተገለጸ።

የጋብቻ እሴቶችን ልጆች በወላጆቻቸው መካከል በግልጽ ሲንጸባረቁ መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል። በአንዳንድ ቤተሰብ መካከል ፍቅር እየቀዘቀዘ መምጣቱን ያልሸሸጉት ወይዘሮ ገብርኤላ ቤተሰብን መመስረትና በጋብቻ መካከል ታማኝነትን ተጋባራዊ ማድረግ መስዋዕትነትን ይጠይቃል ብለው በልጆቻችንም መካከል እውነተኛ ፍቅርና ታማኝነት እንዲያድግ ማስተማር ይጠበቅብናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማደግ ላይ ያለ ቤተሰብ ማንነቱን ጠብቆ፣ ከሌሎችም ጋር በፍቅር ለመኖር የሚያስችል መንገድ መሆኑን በቤልጄም ዋና ከተማ በብራስልስ የተቀመጠው የአውሮጳ ካቶሊካዊ ቤተሰብ ማሕበራት ፌደሬሽን አስታወቀ። የአውሮጳ ፓርላማ ጽሕፈት ቤት መቀመጭ በሆነችው በብራስልስ ከተማ ጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ. ም. በተካሄደው ጉባኤ ላይ የአውሮጳ ካቶሊካዊ ቤተሰብ ማሕበራት ተወካዮች እንደገለጹት በዛሬው ጊዜ የቤተሰብን ጽንሰ ሐሳብ ወይም ትርጉም አቅልሎ ማየት አይቻልም ብለው ቤተሰብ የሕብረተሰቡ ውድ ሐፍት እንደሆነ ገልጸዋል። ቤተሰብ የጋር ጥቅም መሠረት፣ ከማሕበራዊ ኑሮ በመነሳት የእያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ ክብርና ማንነት የሚረጋገጥበት መሆኑን ጉባኤው እንደተወያየበት በቅድስት መንበር የምዕመናን ቤተስብና የሕይወት ተንከባካቢ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ ገልጸዋል።

ቤተሰብ የሚኖረው በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ እንደሆነ ነው፣

ቤተሰብ ለማሕበራዊ እድገት መሠረት ነው ያሉት ወይዘሮ ገብርኤላ ቤተሰብ የሰው ልጅ አስፈላው እገዛ ተደርጎለት የሚያድግበት ስፍራ እንደሆነ ገልጸው፣ በቤተሰብ መካከል ከሚደረገው ግንኙነት በመነሳት ወደ ዓለም ሁሉ ሊደርስ ይችላል ብለዋል። በቤተሰብ ውስጥ የምንገኝ እያንዳንዳችን በየዕለቱ በምናሳየው ወይም በመካከላችን በምናደርገው ግንኙነት የተነሳ የበለጠ ስብዕናችንን እናሳድጋለን ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ቤተሰብ ለሰው ልጅ መኖር የጀርባ አጥንት ነው ማለታቸውን አስታውሰዋል። በቅድስት መንበር የምዕመናን ቤተስብና የሕይወት ተንከባካቢ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ በማከልም ከፊታችን የሚገኝ ትልቁ የሥራ ድራሻ ቢኖር ቤተሰብ በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ፣ ሊለያይ ወይም ሊበታተን የማይችል፣ ለእውነት የቆመ ማሕበረሰብን ለመገንባት ብቸኛ መንገድ መሆኑን ለልጆቻችን ማስረዳት መቻል አለብን ብለዋል።  

በምክንያት ላይ የተመሠረተ ነጻነት ይኑር፣

አሁን የደረሰንበት የዓለማዊነት አስተሳሰብ ጋብቻ በሕብረተሰብ ዘንድ ሊኖረው የሚገባውን ክብርና ትርጉም በማሳነስ መልኩን ቀይሮ እንዲገኝ አድርጎታል ያሉት ወይዘሮ ገብር ኤላ ጋምቢኖ ቤተሰብ በምንም መልኩ ማደግ መስፋፋት ያስፈልጋል ብለው ይህም ማንነቱን ለማስከበር፣ የሕብረተሰቡንም እድገት ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል። በሕብረተሰብ መካከል ሰዎች ሊያበረክቱ የሚችሉት የዕውቀት ዘርፍ የሚመነጨው ከቤተሰብ ነው ያሉት ወይዘሮ ገብርኤላ ይህም እያንዳንዱ ሰው ማንነቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅ ያግዛል ብለዋል። አሁን ያለንበትን ዓለም ለቤተስብ ያለውን አስተሳሰብ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዝ ማድረግ የሚቻለው በግልጽ የሚታዩ እውነታዎችን በመለወጥ ሳይሆን የቤተሰብን ትርጉምና ከወዴት እንደመጣ በሚገባ ማወቅ ስንችል ነው ብለዋል። ወጣቱ ትውልድ ስለ ቤተሰብ ትርጉም በትክክል ለማወቅ እንደሚቸገሩ የገለጹት ወይዘሮ ገብርኤላ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ያለው የወጣቱ ትውልድ እንዴት እርግጠኛ ሊሆን ይችላል? ምን ተስፋ ይኖረዋል? የኑሮ ዋስትናንስ እንዴት ሊያገኝ ይችላል? ብለዋል። ነጻነት ሕግ ወይም ደንብ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው በሚገባ የተገነዘበው ከሆነ ለሚያደርጋቸው ሥራዎች በሙሉ ትክክለኛና በቂ ምክንያት ሊኖረው የሚገባ የሕይወት አካሄድ ነው ብለዋል። ይህም እውነትንና ማሕበራዊ ጥቅምን ያገናዘበ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ለቤተሰብ ሕጋዊ መብትና ጥበቃ እንዲኖረው ያስፈልጋል፣

ቤተሰብ ሊኖረው የሚገባውን ሕጋዊ መብትና ጥበቃን በማስመልከት ወይዘሮ ገብርኤላ ባቀረቡት ሃሳባቸው፣ በርካታ ስነ ሞራላዊ ደንቦች እየታዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ቤተሰብን የሚመለከቱ ሕጎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንም ጠቅሰው እነዚህን ሕጎችንና ስነ ሞራላዊ ደንቦችን የሰው ልጅ ራሱንና የሚኖርበትን ሕብረተሰብ በሚጠቅም መልኩ በተግባር በመተርጎም የቤተሰብ ዘላቂ ሕይወትንና ደህንነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

መልካም በራሱ እና ለግል ሲሆን፣

የቤተሰብን መልካም ጎን በተጨባጭ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል ያሉት በቅድስት መንበር የምዕመናን ቤተስብና የሕይወት ተንከባካቢ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ ንግግራቸውን በመቀጠል እንዳስረዱት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአውሮጳ የጋብቻንና የቤተሰብ ሕይወትን  በተመለከተ እየተወሰደ የመጣው ደንብ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተምሩት አካሄድ፣ ይህም ለእኔ ብቻ መልካም የሆነ እንደሆነ መልካም ነው፣ የሚል አስተሳሰብ እንደሆነ ተናግረው ሁላችንም ልንገነዘበው የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ለልጆቻችን የሚናስተምረው ትምህርት በእውነት ለውደፊት ሕይወታቸው ዋስትናን ታማኝነትንና ፍቅርን በመካከላቸው ሊያሳድግ ይችላል ወይ ብለን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በጋብቻ መካከል ታማኝነት ኣንዲኖር፣

ወይዘሮ ገብርኤላ በመጨረሻም የጋብቻ ትክክለኛ ትርጉም የሚገለጸው ለጋብቻ ምስጢር መሰረት የሆነው ታማኝነት እውነተኛ ፍቅር ሲኖር ነው ብለው ታማኝነት ሁለቱ ባለትዳሮች የሚለዋወጡት የእምነት ምልክት ነው ብለዋል። እነዚህን ሁለቱን የጋብቻ እሴቶችን ልጆች በወላጆቻቸው መካከል በግልጽ ሲንጸባረቁ መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል። በአንዳንድ ቤተሰብ መካከል ፍቅር እየቀዘቀዘ መምጣቱን ያልሸሸጉት ወይዘሮ ገብርኤላ ቤተሰብን መመስረትና በጋብቻ መካከል ታማኝነትን ተጋባራዊ ማድረግ መስዋዕትነትን ይጠይቃል ብለው በልጆቻችንም መካከል እውነተኛ ፍቅርና ታማኝነት እንዲያድግ ማስተማር ይጠበቅብናል ብለዋል።  

09 November 2018, 15:27