ፈልግ

ካርዲናል ፓሮሊን፣ መንግሥታት የስደተኞችን ጉዳይ ለመመልከት መልካም ፍላጎትን እንዲያሳዩ አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ሮም በሚገኘው በግረጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ትናንት ህዳር 17 ቀን 2011 ዓ. ም. በተደረገው የስደተኞች የብዙሃን መገናኛዎችና የመንግሥት ባለስልጣናት ስደተኞችን የሚያገል አመለካከትን በመተው፣ ስደተኞች በክብር የሚስተናገዱበትንና ከማሕበረሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ. ም. በሜክስኮ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉባኤ የላኩትን መልዕክት ያስታወሱት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ስደተኞች ለሄዱበት አገር ሸክም ይሆናሉ ብሎ ከማሰብ ይልቅ ወደ ማሕበረሰባችን ይዘው የሚመጡትን የሕይወት ልምዳቸውን፣ ሐይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በማካፈል ትልቅ አስተዋጽዖን ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።    

የስደትን መልካም ጎን መናቅ ተገቢ አይደለም፣

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመግቢያ ንግግራቸው ስደትን በተመለከተ የብዙሃን መገናኛዎችና የፖለቲካ መሪዎች ያለባቸውን ሃላፊነት መዘንጋት የለባቸውም ብለው፣ ስደተኞች በሚኖሩበት አገር ውስጥ ክብር እንዲኖራቸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየጊዜው እንዳሳስሰቡት ሁሉ ስደተኞች በማሕበረሰቡ መካከል መገለልና መናቅ እንደሌለባቸው ገልጸዋል። የብዙሃን መገናኛዎች የስደተኞችንና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ አስመልክተው ይፋ የሚያደርጉት አሳዛኝ መረጃዎች መኖራቸው ቢታወቅም፣ ለስደተኞችና ለጥገኝነት ጠያቂዎች ሊደረግላቸው የሚያስፈልጉ እርዳታዎች፣ ከእነዚህም መካከል መልካም አቀባበልና መስተንግዶ፣ በማሕበረሰብ መካከል ገብተው ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ የበጎ ሥራ አገልግሎት መናቅ የለበትም ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከዚህም ጋር አያይዘው መንግሥታት በስደተኞችና በጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከቶች በማስወገድ፣ ፍትህን የተከተሉና የጊዜውን ሁኔታ ያገናዘቡና ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሰዎች ፍልሰት የሚያሰጋ መሆን የለበትም፣

በሮም ከተማ የሚገኘው የግረጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የእምነትና ባሕል ጥናት ማዕከል በሜክሲኮ አገር ከሚገኝ የሲንደረሲ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር በመተባበር አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ በመጽሐፍ መልክ ይፋ ማድረጉን ብጹዕ አቡነ ሳሙኤለ ሳንጋሊ ገልጸዋል። የተማሪዎቹ ጥናታዊ ጽሑፍ አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤለ ሳንጋሊ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ በየዓመቱ ከ60 በላይ ተማሪዎች፣ በተለያዩ ማሕበራዊ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያደርጉትን ጥናታዊ ምርምር ለማከሄድ በሮም በሚገኘው የግረጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው በሁርታዶ ማዕከል ውስጥ ለአንድ አመት ያህል እንደሚቆዩ ገልጸዋል። ተማሪዎቹ ዘንድሮ ያካሄዱት ጥናታዊ ጽሑፍም የወቅቱን የስደተኞች ጉዳይ የተመለከተ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤለ፣ ተማሪዎቹ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ከመጀመራቸው በፊት የሕዝቦችን ፍልሰት እንደ አስደናጋጭ ማሕበርዊ ክስተት ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ጠቅሰው፣ ከድንጋጤ የተነሳ መንግሥታት ድንበሮቻቸውን መዝጋት እንደሌለባቸው፣ ነገር ግን ዓለም አቀፋዊ ለውጥ መሆኑን በመገንዘብ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሳስሰቡት ሁሉ ስደተኞች ተቀብሎ ማስተናገድ፣ በማሕበራዊ ኑሮ ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ እንጂ መገለልና መናቅ እንደሌለባቸው ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ክብር ለእኛም ለተፈናቃዮችም ሊኖር ይገባል፣

ማስከበር ካለብን ዋና ዋና እሴቶች መካከል የሰብዓዊ ክብርና መብት እንደሚገኙ የጠቀሱት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤለ ሳንጋሊ፣ የእነዚህ ሰብዓዊ መብቶች መከበር ለአውሮጳዊያን እጅግ አንገብጋቢ ከሆኑ፣ በጦርነትና በአመጽ ምክንያት ለሚሰደዱት፣ ለሕይወት አስጊ የሆኑ መንገዶችን አቋርጠው ወደ አውሮጳ ለሚደርሱት ስደተኞች ክብራቸውንና መብታቸውን ማስከበር እንዴት ተገቢ አይሆንም ብለዋል። ነጻነት፣ እኩልነታና ወንድማማችነት የሚለውን የፈረንሳዊያን አባባል ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤለ ሳንጋሊ፣ አውሮጳውያኑ በነጻነትና በእኩልነት ይበልጥ እንደሚያተኩሩ ነገር ግን ወንድማማችነትን የዘነጉ ይመስላል ብለው፣ የወቅቱ የስደተኞች ሁኔታ ወንድማማችነት የሚለውንም እንድንመለከት ያስገድደናል ብለዋል።    

27 November 2018, 16:22