ፈልግ

Pope Francis in Palermo Pope Francis in Palermo  

በሮም የሚካሄደው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በሙሉ ልብ እንደሚከናወን ተገለጸ።

ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚቆየው ይህ የብጹዓን ጳጳሳት 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን በቀዳሚነት የሚወያይባቸው ርዕሠ ጉዳዮች በወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ ሲሆን ይህም ወጣቶች፣ እምነታቸውና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን እንዲገነዘቡ የሚል እንደሆነም ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለረጅም ወራት በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሀገረስብከቶች ዝግጅት ሲደረግበት የሰነበተው 15ኛው የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ነገ በሮም በይፋ እንደሚከፍት ከቅድስት መንበር የሕትመት ክፍል የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት እንደሚከፍቱት ታውቋል።   

ከነገ መስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚቆየው ይህ የብጹዓን ጳጳሳት 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን በቀዳሚነት የሚወያይባቸው ርዕሠ ጉዳዮች በወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ ሲሆን ይህም ወጣቶች፣ እምነታቸውና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን እንዲገነዘቡ የሚል እንደሆነም ታውቋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሎረንዞ ባልዳሳሪ ትናንት በመግለጫቸው የጳጳሳቱ አጠቃላይ መደበኛ ሲኖዶስ የሚካሄድበት ይህ ጊዜ በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጥበት፣ አሁን የምትገኝበትን ሁኔታ በማጤን የወደፊት ጉዞዋን እንዴት መጓዝ እንዳለባት ሃሳብ የምታሰባስብበት እንደሆነ በመግለጫቸው አስረድተዋል። አክለውም ለአንድ ወር ያህል የሚዘልቀው የጳጳሳት 15ኛው አጠቃላይ መደበኛ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያን ዋና ተዋናይ ከሆኑት ከወጣቶች ጋር በሕብረት እንደሆነ ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንሶ ባልዳሳሪ በመግለጫቸው እንደገለጹት ከሁለት ሳምንታት በፊት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተፈርሞ የጸደቀው አዲስ ሐዋርያዊ ድንጋጌ መላውን የእግዚአብሔር ሕዝብ በማሳተፍ፣ በመካከላቸው የውይይት አድማስን በማስፋት፣ የጳጳሳት ሲኖዶስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቅርብ ሆነው በመተባበር እንድሰሩ ያሳስባል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንሶ ባልዳሳሪ በማከልም የሲኖዶሱ አባቶች ለጉባኤው ያወጡትን የመጨረሻ ሰነድ በስፋት እንዲመለከቱት ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

ነገ በሮም የሚከፈተውን 15ኛ መደበኛ የጳጳሳት ሲኖዶስን የሚካፈሉት፣ ብጹዓን ካርዲናሎችን፣ ብጹዓን ጳጳሳትን፣ ክቡራን ካህናትን፣ ገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ ከምዕመናን ወገን የመጡ ምሑራንን ጨምሮ ባጠቃላይ 300 አባላት እንደሆኑ ብጹዕ ካርዲናል ሎረንሶ ባልዲሰሪ ገልጸው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረው በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ ስድስተኛ እ. አ. አ. በ1965 ዓ. ም. እንዳቋቋሙት ገልጸው በዚህ የጳጳሳት ሲኖዶስ ተካፋይ የሚሆኑና በቅርቡ ከቅድስት መንበር ሙሉ ዕውቅናን የገኙ ሁለት የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት እንደሚገኙ ገልጸዋል።  

በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውይይት የሚደረግባቸው ጉዳዮች፣ የሚቀርቡትም ሪፖርቶች በቅድስት መንበር የመገናኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አማካይነት በብዙሃን መገናኛ ማሕበራዊ ድረ ገጽ በኩል በመላው ዓለም ለሚገኙትና ጉባኤውን በቅርብ ለሚከታተሉት በሙሉ፣ ሲኖድ 2018 በሚለው የድረ ገጽ አድራሻ ዕለታዊ መረጃዎች እንደሚደርሳቸው የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሎረንዞ ባልዳሳሪ ገልጸዋል።

ያለፈው ዓመት የአምስቱም አህጉራት የጳጳሳት ጉባኤዎችን የሚወክሉ ወጣቶች፣ ከተለያዩ መንፈሳዊና ማሕበርዊ እንቅስቃሴዎች፣ ከገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተወካዮች የተወጣጡ 300 ወጣቶች ወጣቶች በሮም ተገኝተው “ወጣቶች፣ እምነትና፣ ጥሪያቸውን በሚገባ ለይቶ ማወቅ” በሚሉ የውይይት ነጥቦች ላይ ተነጋግረው የሚታወስ ነው።

02 October 2018, 17:50