ፈልግ

የቅዱስ ቁርባን ተዓምራት በጥናታዊ ፊልም ተዘጋጅቶ መቅረቡ ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የቅዱስ ቁርባን ተዓምራቶችን የሚያሳይ ጥናታዊ ፊልም ተዘጋጅት ለእይታ መቅረቡን የቫቲካን የፊልም ዝግጅትና መዝገብ ቤት አስታወቀ። ብጹዕ አቡነ ዳሪዮ ኤዷርዶ ቪጋኖ፣ በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት አማካሪ፣ የቅዱስ ቁርባን ተዓምራቶችን የሚያሳይ ጥናታዊ ፊልም ተሰርቶ መውጣቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ጥናታዊ ፊልሙ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለብጽዕና የሚበቃበት ጊዜ እየተጠበቀ ስለሚገኝ ወጣት ካርሎ አኩቲስ የሕይወት ታሪክ እንደሚተርክ ገልጸዋል። አቡነ ቪጋኖ እንደገለጹት ወጣቱ ኮምፒዩተርንና በኮምፒዩተ በኩል የሚቀርቡ የቪዲዮ ጨዋታዎችን እንደሚወድ ተናግረው ከሁሉ አስቀድሞ ግን ይህ ወጣት ለቅዱስ ቁርባን ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር እንዳለው ፊልሙ በግልጽ እንደሚያሳይ አስረድተዋል። ወጣት ካርሎ በ15 ዓመት ዕድሜው፣ በ1998 ዓ. ም. ከመሞቱ በፊት በቤተክርቲያን እውቅናን ያገኙ 136 የቅዱስ ቁርባን ተዓምራትን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፍ ምስሎችን በሰሜን አሜርካ ውስጥ በሚገኙት 10,000 ቁምስናዎች ለእይታ ማቅረቡን ብጹዕ አቡነ ቪጋኖ አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ቪጋኖ በማከልም ወጣት ካርሎ አኩቲስ ለጓደኞቹ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮች ለመሆን ከፈለጋችሁ የቅዱስ ቁርባን ፍቅር ሊኖራችሁ ይገባል ይል እንደነበር ገልጸው በተጨማሪም ወጣቱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፊት ለፊት የምንገናኝበትን አጋጣሚ ነው ማለቱንም አስታውሰዋል።

ቅዱስ ቁርባን ወደ ልብ ጡንቻነት መለወጡ፣

በጣሊያንኛ ቋንቁ “Segni” ወደ አማርኛው ሲተረጎም ደግሞ “ምልክቶች” የሚል ስም የተሰጠው ባለ 50 ደቂቃ ጥናታዊ ፊልም በሁለት ዋና ርዕሶች ላይ እንደሚተርክ ያስታወሱት የፊልሙ አዘጋጅ አቶ ማቴዎ ቸካሬሊ እንደገለጹት ባለፉት ቅርብ ዓመታት ውስጥ በአርጀንቲናና በፖላንድ ውስጥ ቅዱስ ቁርባን ወደ ልብ ጡንቻዎች የመለወጡን ተዓምር አስታውሰው፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በኢጣሊያ ውስጥ ላንቻኖ በተባለ ስፍራም ተመሳሳይ ተዓምር መታየቱን በቦታው የነበሩ ምዕመናን መናገራቸውን አስታውሰዋል። በአካባቢው ምዕመናን በኩል በቀረቡት ምስክርነቶች መሠረት ቅዱስ ቁርባን በድንገት መሬት ላይ ቢወድቅ ወይም ውሃ ቢነካው፣ ውሃው ሲደርቅ ወደ ጠንካራ የልብ ጡንቻነት እንደሚለወጥ ተናግረው ይህ ተዓምር ለበርካታ ምዕመናን የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር ታላቅነት እንዲረዱና ለሌሎችም እንዲመሰክሩ ማድረጋቸው ታውቋል። በቅዱስ ቁርባን ላይ የተደረገውን ጥናታዊ ፊልም የመሩት አቶ ማቴዎ ቸካሬሊ እንደገለጹት የጥናታዊ ፊልሙ ዋና ዓላማ የቅዱስ ቁርባንን ተዓምራት የተመለከቱ ምዕመናን ምስክርነትና ሳይንሳዊ ጥናት ባካሄዱት ተመራማሪዎች መካከል ውይይትን ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል። በቅዱስ ቁርባን ላይ የተደረገውን ሳይንስዊ ጥናት ልዩና አስገራሚ የሚያደርገው፣ ነፍስ ከስጋ ስትለይ ነጭ የደም ሴሎች ወዲያ እንደሚጠፉ የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የተገኘው ነጭ የደም ሴሎች እንዴት ሊቆዩ እንደቻሉ ተመራማሪዎችን እንዳስገረማቸው የጥናታዊ ፊልሙ አዘጋጅ አቶ ማቴዎ ቸካሬሊ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፋዊ ርዕሠ ጉዳይና ጥቂት ጥናት የተደረገበት፣

በቅድስት መንበር የመገናኛ ክፍል ሰራተኛ የሆኑት ክቡር አቶ ኒኮላ ሳልቪ፣ ወጣት ካርሎ አኩስቲ በ15 ዓመት ዕድሜው የቅዱስ ቁርባንን ተዓምራት የሚገልጹ ልዩ የፎቶግራፍ ትዕይንቶችን ማቅረቡ እንዳስገረማቸው ገልጸዋል። የቅዱስ ቁርባን ተዓምር ዓለም አቀፋዊ ይዘት ቢኖረውም በፊልም የተደገፈ ማብራሪያ ወይም መግለጫ እንዳልተዘጋጀ ገልጸው አሁን ተዘጋጅቶ በወጣው ፊልም ውስጥ የሚታዩ ምዕመናን በተለያዩ ቋንቋዎች ምስክርነታቸውን በመስጠታቸው ለዓለም ሕዝብና ምዕመናን በሙሉ መንፈሳዊ ግንዛቤን እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 

የካርሎ እናትና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስለመገናኘቷ፣

በፊልሙ ውስጥ ምስክርነታቸውን ከሰጡት ግለ ሰቦች መካከል የወጣት ካርሎ እናት፣ ኣንቶኒያ ሳልዛኖ እንደሚገኙበትና ልጃቸው ካርሎ በሰባት ዓመት ዕድሜው የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር እንደተቀበለና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ሳያቁርጥ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚሳተፍና ከመስዋዕተ ቅዳሴ በፊት ወይም በኋላ ለቅዱስ ቁርባን ክብር አጭር ጸሎት ያደርግ እንደነበር ተናግረዋል። ልጃቸው ካርሎ ከሌሎች ጓደኞቹ የተለየ ባሕርይ የማይታይበት ነገር ግን ለቅዱስ ቁርባን ያለውን ልዩ አክብሮትና ፍቅር ይናገር እንደነበር፣ በቅዱስ ቁርባን የሚገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘወትር ታማኝ ጓደኛው እንደሆነ ይናገር እንደነበር ተናግረዋል። እናቱ የሆኑት ወይዘሮ አንቶኒያ በማከልም ልጃቸው ካርሎ፣ ቤተክርስቲያን በአቅራቢያቸው በመገኘቱ ዕድለኞች መሆናቸውን ይናገር እንደነበር፣ በዚህም ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ኢየሱስ በሚኖርበት ኢየሩሳሌም አካባቢ ከኖሩት ሰዎች ይልቅ የበለጠ ዕድለኞች መሆናቸውና ሕያው ኢየሱስ ክርስቶስን በቅዱስ ቁርባን ውስጥ እናገኘዋለን ማለቱን አስታውሰዋል። በማከልም ካርሎ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገር እንደነበር፣ በቅዱስ ቁርባን በኩል ስለምንቀበለው ደስታ ሌሎችን ማስተማርና ለሌሎች መመስከር ያስፈልጋል ይል እንደነበር አስታውሰዋል።

ኢየሱስን የጎበኘ የልብ ሐኪም፣

በቅዱስ ቁርባን ላይ በተደረገው ጥናታዊ ፊልም ውስጥ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል በኢጣሊያ ውስጥ በቦሎኛ ከተማ የልብ ቅድዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት አቶ ፍራንኮ ሴራፊኒ “ኢየሱስን ያከመ የልብ ቀድዶ ሕክምና ባለሞያ፣ የቅዱስ ቁርባን ተዓምራቶች በሳይንሳዊ ምርምር” የሚል መጽሐፍ ማሳተማቸው ታውቋል። አቶ ፍራንኮ፣ የልብ ቀዶ ሕክምናን መስጠት ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ፣ ባለፉት 10, 20 እና 30 ዓመታት መካከል በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተረጋገጡና ሳይንሳዊ ምርምር የተደረገባቸውን አምስት የቅዱስ ቁርባን ተዓምራቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ተዓምር የየዕለት ሕይወት ገጠመኝ ነው፣

የፊልሙ አዘጋጅ ክቡር አቶ ቸካሬሊ በመግለጫቸው እንዳስገነዘቡት፣ በጥናታዊ ፊልሙ የተገለጹ እውነታዎችን መገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው፣ እውነተኛ ተዓምራት በየዕለት ሕይወት መካከል ሊገለጥ የሚችል መሆኑን በፊልሙ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች ወይም ምዕመናን መረዳት እንደተቻለ፣ እነዚህ ምዕመናን በክርስትና ሕይወታቸው ውስጥ የቅዱስ ቁርባንን ታላቅነት ተገንዝበው በሚኖሩበት አካባቢዎችን ቁምስናዎች ውስጥ ምስክርነትን መስጠት መቻላቸውን አስረድተዋል። የቅዱስ ቁርባን ተዓምር የሚገለጽበት ጥናታዊ ፊልም በሚቀጥሉት ጊዜያት በተለያዩ የማሕበራዊ መገናኛዎች በቪዲዮ፣ በቴሌቪዢን፣ በኢንተርኔት በኩል እንደሚሰራጭና ወጣት ካርሎ አኩቲስ በርካታ በፎቶግራፍ የታገዙ ትዕይንቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማቅረብ ለማሳየት ያደረጋቸውን ጥረቶች በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ የተቻለበት አጋጣሚ መመቻቸቱን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
31 October 2018, 15:45