ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ሰሜን ኮርያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸው ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በሮም በተደረገው በአንድ የመጽሐፍ ማስመረቂያ ዝግጅት ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሰሜን ኮርያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ፍላጎት እንዳደረባቸው አሳይተዋል ብለዋል። ከዚህ በፊት ይፋ በሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ የተገለጸውን ዋቢ በማድረግ የተናገሩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እንዳሉት፣ ትናንት ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ. ም. የደቡብ ኮርያው ፕሬዚደንት በቫቲካን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተገኛኙበት ጊዜ፣ የሰሜን ኮርያው ፕሬዚደንት፣ ቅዱስነታቸው ፒዮንግ ያንግን እንዲጎብኙ መመኘታቸውን እንደገለጹ ጠቅሰው፣ ግብዣቸውንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደስታ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ዝግጅት ተጀምሮ እንደሆነ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ካርዲናል ፓሮሊን ሲመልሱ፣ በሁለቱም በኩል ያለውን መልካም ምኞት በቃል ተገላለጹበት የመጀመሪያ ደረጃ እንጂ የተጀመረ ነገር የለም ብለዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም አስቀድሞ መከናወን ያለባቸው ቅድመ ዝግጅቶች እንዳሉ ገልጸው ከእነዚህም መካከል ለሰላም ሂደት ድጋፍን በመስጠት፣ የኮርያ ባሕረ ሰላጤን ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ስጋት ነጻ ማድረግ ይገኝበታል ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገለጻቸውን በመቀጠል ስለ ሐዋርያዊ ግብኝታቸው ሁኔታ በዝርዝር ማቀድ ስንጀምር፣ ከጉብኝታቸው አስቀድሞ ተግባራዊ መሆን ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰሜን ኮርያን እንዲጎበኙ የሚል ምኞት ከሰሜን ኮርያ በኩል ቢገለጽም፣ ወደ ዚህች አገር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሰፊ ቅድመ ዝግጅትን እንደሚጠይቅ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስረድተዋል።                 

19 October 2018, 17:13