ፈልግ

2018.10.03 Apertura lavori Sinodo 2018.10.03 Apertura lavori Sinodo 

የጳጳሳት ሲኖዶስ “ቤተክርስቲያን የወጣቶች መኖሪያ ቦታ እንድትሆን ያስፈልጋል”።

ወጣቶች የወንጌልን መልካም ዜና የሚያዳምጡ ብቻ ሳይሆን የሚመሰክሩም ሊሆን ይገባል። ይህም ወጣቶች በመንፈስዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት ላይ ያላቸውን ሚና በማደስ የበለጠ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወጣቶች፣ እምነታቸውና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት እንዲገነዘቡት በሚል የመወያያ ርዕስ 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የመላው ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሐሙስ ዕለት ባደረገው ውይይቱ ወጣቶችን ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።

ወጣቶች የወንጌልን መልካም ዜና የሚያዳምጡ ብቻ ሳይሆን የሚመሰክሩም ሊሆን ይገባል። ይህም ወጣቶች በመንፈስዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት ላይ ያላቸውን ሚና በማደስ የበለጠ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል ተብሏል። በተጨማሪም በአዲሱ ትውልድ መካከል የዓለም ብርሃን፣ የሰላምና የፍቅር መሣሪያ እንዲሆኑ ያደረጋቸዋል ተብሏል።

ቤተክርስቲያን የወጣቶች መኖሪያ ሥፍራ ልትሆን ይገባል፣

ቤተክርስቲያን ለወጣቶች እናትም፣ መኖሪያ ቤታቸውምና ድምጻቸውም እንደሆነች የጳጳሳት ሲኖዶስ ገልጾ በተለይም በተለያዩ ማሕበራው ችግሮች ውስጥ የሚገኙት ወጣቶችም ቢሆኑ የወንጌልን መልካም ዜና የማወጅ ዕድል ቢሰጣቸው የተሻለ ዓለምን ለመገንባት እንደሚችሉ ሲኖዶሱ አምኖበታል። በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች የተጠቁ ወጣቶች ለምሳሌ በለጋ ዕድሜአቸው በውትድርና አገልግሎት ተሰማርተው የነበሩ፣ በጎጂ ልማድ በተጠቁ ቤተሰቦች መካከል የተወለዱ ልጆች፣ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ በሙስና የተዘፈቁ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ የተሰማሩት፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወጥተው ሥራ በማጣት ለስደት የተዳረጉ፣ በዚህ የተነሳ ከወላጅ ቤተሰብና ከእምነት የራቁ በርካታ ወጣቶች መኖራቸው ተስተውሏል።  

የወጣቶችን ቅንዓት መንከባከብ፣

የምርት ፍጆታን ያማከለ የምዕራቡ ዓለም የወጣቶችን አስተስሰብና አቋም እየተጠናወተ እንዳለ ያስታወሰው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወጣቶችን ወደ አዳዲስ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ በማስገባት ያለ እምነት እንዲቀሩ ማድረጉን ተገንዝቧል። ሲኖዶሱ በግልጽ መወያየት ያስፈልጋል በማለት ካነሷቸው የውይይት ርዕሶች መካከል አንዱ በወጣቶች መካከል፣ ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም ጾታዊ ግንኙነት በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን የእጮኛነት ጊዜን ታማኝነትን እንደሚጎዳ ገልጿል። ወጣቶች በቁምስናቸው ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ብዙ ወጣቶች ምስጢረ ሜሮንን ከተቀበሉ በኋላ ከቤተክርስቲያን እንደሚርቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ እንዳይከሰት ለወጣቶች የሚሰጠው አገልግሎትና እንክብካቤን ባዲስ መልክ እንዲዋቀር፣ ለወጣቶች የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት በእውነተኛ ፍቅር የታገዘ እንዲሆን፣ የወጣቶች ዘመናዊ ባሕልን መረዳትና ድምጻቸውን ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

ወጣቶች በቤተክርስቲያን እምነት ይኑራቸው፣

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ወጣቶች በቤተክርሲያን ውስጥ በዕድሜ የሚበልጧቸውን የምዕመናን ወገን በመደገፍ፣ ቤተክርስቲያን በተግባር የምታበረክተውን የወንጌል ምስክርነትንና የአንድነት መንፈስን በገሃድ መመልከት እንደሚፈልጉ ተገንዝቧል። ወጣቶች ይህን አገልግሎት ለቤተክርስቲያናቸው፣ ለቁምስናዎቻቸው በማበርከት የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን በመገንዘብ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቅድስት መንበር የወጣቶችን ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤት እንዲቋቋም ሃሳቡን አቅርቧል። የጉባኤው አባቶች ባዘጋጁት ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት በወጣቶች ሕይወት ውስጥ መንፈሳዊ ተሃድሶ እንዲታይ ጠይቀው ቤተክርስቲያን አሁን በምትገኝበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ ወጣቶች ፊታቸውን ወደ ቤተክርስቲያን በማዞር፣ ከጎኗ መሆን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ወጣቶች ማሳየት ካለባቸው መንፈሳዊ ተሃድሶ በተጨማሪ በካህናት ላይ እምነት እንዲኖራቸው ጠይቀው በመካሄድ ላይ ያለው  የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለወጣቶች በሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት መልካም ውጤትን የሚያስገኙ አዳዲስ መንገዶችን እንደሚያመቻች ተስፋስፋቸውን ገልጸዋል።

ቅዱሳንን የሚያስታውሱ የአምልኮ ስርዓትንና ጸሎሎቶችን ማዘጋጀት፣

በቤተክርስቲያን የሚሰጡ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እና ስርዓተ አምልኮ ከምዕመናኑ የውዳሴ ጸሎት ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆን እንዳለበት የሲኖዶሱ አባቶች አስረድተው የምዕመናን ጸሎት ቤተክርስቲያን በስደት ላይ በምትገኝበት ጊዜ ሁሉ ከብዙ መከራ ሊከላከላት እንደቻለ አስታውሰዋል። ወጣቶች ወደ አንዳንድ ፈታኝ ወደ ሆኑት ማሕበራዊ ስሜቶች ውስጥ እንዳይገቡ በርትተው መጸለይ እንዳለባቸው ማስረዳት ያስፈልጋል ብለው ቤተክርስቲያንም በበኩሏ ወጣቶች ትክክለኛ ጥሪያቸውን እንዲገነዘቡ ዘወትር እንደምታስታውሳቸው አስረድተዋል። የሲኖዶሱ አባቶች በተጨማሪም እውነተኛ ደስታን የሚያስገኙ ዘለዓለማዊ ሃብቶችን ለወጣቶች በማዳረስ እገዛን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው ለዚህም ብዙ መንፈሳዊ በረከቶችና ጥበብ የሚገኝበት የቅዱሳን የሕይወት ገድል ለወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት ማደግ እጅግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።   

06 October 2018, 19:30