ፈልግ

2018.10.09 Sinodo dei giovani 2018.10.09 Sinodo dei giovani 

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ “ጥሪ በቤተ ሙከራ ወስጥ ገብቶ የሚታወቅ አይደለም”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ ግርማቸው ተስፋዬ - ቫቲካን

በትናንትናው ዕለት ማለትም ዕለተ ረቡዕ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. እ.አ.አ. በዚህ በወጣቶች ሲኖዶስ ላይ የተደረገዉን ውይይት ኢሳቤላ ፒሮ እንደሚከተለው ተከታትላዋለች። ይህ በትናንትናው ዕለት ማለትም ዕለተ ረቡዕ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. የተደረገው ውይይት ስምንተኛው ኣጠቃላይ የብጹኣን ጳጳሳት ስብሰባ ሲሆን በስብሰባው ላይ የተገኙት ኣባቶች 255 ናቸው። በዚሁም ውይይት በይበልጥ የተንሸራሸረው ሓሳብ እምነትና ጥሪ ላይ ውሳኔ ስለመስጠት በተመለከተ ነው።

በዕለቱ ወጣቶችና ቤተክርስቲያን በሚል በተነሳው ሓሳብ ላይ ወጣቱ የነገው የቤተክርስቲያን ተስፋ ብቻ ሳይሆን በኣሁኑም ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው እስከ ፊታችን ጥቅምት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. እ.አ.አ. የሚካሄደው ስምንተኛው ዙር አጠቃላይ የብጹኣን ጳጳሳት ሲኖዶስ ኣስምሮበታል።

በዚሁ ዙሪያ እየተካሄደ ያለው ሲኖዶስ ወጣቱ ትውልድ በቂ የሆነ እገዛ እንደሚያስፈልገውና እውነተኛ ጥሪዉንም በሚገባ እንዲረዳ ብሎም በወደፊት ሕይወቱ ትክክለኛ ምርጫ እንዲያደርግ ምክር መለገስ ያስፈልጋል ተብሏል። እንደ ሲኖዶሱ ኣባቶች አመለካከት የወጣቶች ሓዋርያዊ እንክብካቤን በተመለከተ ወጣቱ በእርግጥም በውስጡ ያለዉን ፊላጎቱን በሚገባ እንዲረዳና በዛም ላይ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንዲችል ማገዙ ተገቢ ነው ሲሉ ብዙዎች ኣስተያየቶቻቸውን መለገሳቸው ተብራርቷል።

በዕድሜ የገፉ ሰዎች እና ወጣቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች

ሲኖዶሱ አሁንም ጥሪን በተመለከተ በጥልቀት እንዳስረዳው ጥሪ በቤተ ሙከራ ውስጥ ገብቶ የሚታወቅ ነገር ሳይሆን ከህብረተሰቡ ውስጥ የሚወጣ ወይም የሚመነጭ ነገር ነው። ይህንንም ለማጎልበት ደግሞ ቤተክርስቲያን በዚህ ረገድ ወጣቶችን ለመርዳት እንደ የመስክ ሆስፒታል በመሆን ከወጣቶቹ ጋር እውነተኛና ቀጥተኛ ግንኙነት መመሥረት ይጠብቅባታል የመገናኛ መድረኮችን መክፈትና ለነገሩ የበለጠ ትኩረት ሰጥታ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባት ተብራርቷል።

በዚህ መልኩ ቤተክርስቲያን ወጣቶች ለሚያደርጉት ትክክለኛ ምርጫ ላይ በመሳተፍ ትክክለኛ ምርጫ እንዲያደርጉ በመርዳት ያለባትን ኃላፊነት ትወጣለች በዚህ መልኩ ከወጣቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረጓን ተቀጥላለች ይህ ደግሞ ቤተክርስቲያን ስለ ወጣቶች ማውራት ብቻ ሳይሆን ከወጣቶቹ ጋር የመወያየትንም ባህል እንድታዳብር ያግዛታል። በዚህ መልኩ የአረጋዉያን ሕልምና የወጣቶች የወደፊት ዕቅድ ተግባራዊ ሊሆንና በሁሉ መልኩ የታነፀ ማኅበረሰብ ሊፈጠር ይችላል። በትንቢተ ኢዩኤል ላይም ተጠቅሶ እንደምናገኘው በዚህ መልኩ ቤተክርስቲያን ራሷንና ጉልበቷን በወጣቶች ውስጥ ታገኘዋለች ይህ ደግሞ ወጣቱ ከጌታችን እየሱስ ጋር እንዲገናኝ በር ይከፍትለታል።

ወጣቶችን ኃላፊነት እንዲሰማቸውና ኃላፊነት እንዲወስዱ ስለማረግ

ወጣቶች ወይም አዲሱ ትውልድ በማያሻማ እና ማራኪ በሆነ መንገድ በእውነታዊ ማስተዋል እና በመደማመጥ ላይ በማተኮር እውነተኛ ውሳኔዎችን እንዲወስድና ተግባራዊ እንዲያደርገው ጥሪ ማድረግ ያስፈልጋል ምክንያቱም በዚህ መልኩ የደኅንነት መልዕክት በተገቢና ቀልብን በሚስብ መልኩ ለወጣቱ ሊደርስ ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ወጣቶች ወይም አዳጊዎች ልክ እንደ ወላጆች በብዙ ዉጣ ውረዶች ላይ የተከበቡ ባይሆኑም በብዙ ነገሮች ላይ ግን ኃላፊነት የሚወስዱና በቤተክርስቲያን ህይወት ውስጥም ተሳታፊ መሆን አለባቸው በዚህ መልኩ ካደጉ ለወደፊቱ ትልቅ ህልም ይኖራቸዋል።

ለድሆች ፍቅርን ማዳበር

ሌላው የጥሪ ትኩረት ማዕከል ወጣቱ ትውልድ ድሆችን እንዲቀርብና እንዲያግዝ ማድረግ ነው። እንደ ሲኖዶሱ ኣባቶች ኣገላለጽ ደሃ ሰው ከሌለ ክርስቲያናዊ ጥሪ አይኖርም ምክንያቱም ደሃ ሰው ዓለምን የበለጠ እንድንረዳትና እንድንገነዘባት ብዙ ነገሮችን ያስተምረናል በዚህም የተነሳ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙትን እርዳታና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን ወጣቶች መመልከት ይኖርባታል ምክንያቱም እነርሱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ለመከተል የተጠሩ ናቸውና። ከዚህ ኣንፃር ሲኖዶሱ ሰብአዊ አመለካከትን በማዳበር በማህበራዊ ፍትህ ዙሪያ በሰብአዊ መብቶች ኣከባበር እንዲሁም የህይወት ባህልን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት ተነጋግረዋል።

ቤተሰብ ትንሿ ቤተክርስቲያን መሆንዋ ተገለጸ

ቤተሰብ ትንሿ ቤተክርስቲያን መሆንዋ በሲኖዶሱ የተጠቆመ ሲሆን ቤተሰብ ትንሿ ቤተክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን ሕይወትና ጥሪም የመጀመሪያ መስመራቸዉን የሚያሰምሩት በዚሁ ደረጃ ነው። ቤተክርስቲያንም ይህንን ጥሪ በእምነት በተስፋና በተልዕኮ የማሳደጉ ኃላፊነቱ ቢኖራትም መነሻው ግን ሁሌም ከቤተሰብ መሆኑ ተብራርቷል። በተለምዶ የመጀመሪያ ጥሪ በሕፃናት ጨዋታ መሓል የሚንፀባረቅ ሲሆን ወላጆችም ከልጆቻቸው ጋር በመጫወትና ለእነርሱ ጊዜ በመስጠት የልጆቻቸውን ጥሪ እንዲረዱና ያንንም ጥሪ ከቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክሩ ዉጤቱ መልካም ነው ትብሏል።

የኢየሱስን ምሳሌነት ከኤማሁስ ተጓዦች ጋር

ኣንዳንድ ጊዜ የዚህን ዓለም ሁኔታ ስንቃኝ የወንጌልን ዋጋ ያሳንሰዋል እንደ ሲኖዶሱ ኣባቶችም አመለካከት ወጣቶቹ በኣብዛኛው በተሳሳተ ነገር ላይ እምነታቸውንና ተስፋቸዉን በማሳደር ከቤተክርስቲያን ይሸሻሉ። ይህንን ነገር ለማሻሻል ደግሞ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከኤማሁስ ተጓዦች ጋር ተገናኝቶ ኣብሮኣቸው ይጓዝ እንደነበረ ኣሁንም ከወጣቶቹ ጋር ለመጓዝ ፈቃደኛ ነውና በተቻላቸው መጠን ወጣቶች ከእርሱ ጋር ለመገናኘትና ኣብረው እንዲጓዙ መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው ትብሏል።

የአቻ ለአቻ ጓደኝነት

ከወጣቶች ወይም ከኣዳጊዎች ጋር ያለምንም የእነርሱን ሓሳብና ምቾት ሳንነሳ ከጎናቸው በመቀመጥ ልባቸው በነፃነት የፈለገዉን እንዲጠይቅ ማድረግ ይህ እውነተኛ ሓዋርያዊ ጓደኝነት ወይም ደግሞ ሓዋርያዊ እንክብካቤ ነው። ወጣቶች ወይም ደግሞ ኣዳጊዎች ሁሌ ቢሆን እኮዮቻቸውን ይሻሉ በነፃነትም ሃሳባቸውን እርስ በርሳቸው ያንሸራሽራሉ። በዚህ በወጣቶች ሲኖዶስ ተካፋይ የሆኑት ወጣቶች በሲኖዶሱ በተዘጋጀ መንፈሳዊ የጉብኝት ቦታ እድሜያቸው ገፋ ካሉ ኣባቶች ጋር ወዲህና ወዲያ ሲል መስተዋሉም እንደ ምሳሌ መወሰዱን በውይይቱ ተብራርቷል።

እውነተኛ ነፃነት በኢየሱስ ልብ ውስጥ ራስን ማግኝት ነው

የሲኖዶሱ ሓሳብ ይህን የዲጂታል ዓለም የበለጠ መረዳት ነው። አንድ የሞባይል ስልክ ምናልባት ለህፃናት ወይም ለወጣቶችህ ክርስቶስን የሚያገኙበት መንገድ ኣሊያም ደግሞ የሕይወታቸዉን ኣቅጣቻ የሚመለከቱበት ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ኣብዛኛውን ጊዜ ልጆች በውስጣቸው ለሚመላለሱ ሓሳቦች ወይም ጥያቄዎች መልስ ማግኘትን ይመኛሉ ነገር ግን የሚያገኙት ነገር ቴክኒካዊ ወይንም ሳይንሳዊ መረጃ እንጂ እንደ ፍቅር መቻቻል ኣብሮነት የመሳሰሉትን ነገር በቀላሉ ኣያገኙም። ሲኖዶሱ በዚህ ዙሪያ ሓሳቡን ሲያስቀምጥ እንዲህ ይላል ወጣቶች እውነተኛ ነፃነትን ይሻሉ ወይንም በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ እራሳቸውን ማግኘት ይፈልጋሉ እንዱሁም የተወደዱና ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሚሹ ተጠቁሟል።

በሳልና ኃላፊነት በሚሰማው ፍቅር መጎልመስ ያስፈልጋል

በመጨረሻም የስብሰባው ተሳታፊዎች በሳልና ኃላፊነት የሚሰማው ፍቅር ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ይህም ብስለት በሰው ልጆች ውስጥ ያለውን ፍቅር ማእከልና መሠረት ያደረገ ነው። በተጨማሪም ሲኖዶሱ በጾታ ትምህርት ላይ ከጋብቻ በፊት በሚደረግ ኣላስፈላጊና የተሳሳተ ጾታዊ ግንኙነቶች ላይ አጽንዖት ሰቶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል። በመጨረሻ የሲኖዶሱ አባቶች በስደት ውስጥ ላሉ ወጣት ክርስቲያኖች እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እነርሱን ለመርዳት ለሞቱት አያሌ ቄሶች ቁሳዊ እርዳታ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ የእኛን ቅርብነትና መንፈሳዊ ድጋፍ ይሻሉ ብለዋል።

11 October 2018, 17:58