ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሎረንሶ ባልዳሳሪ የወጣቶች ጉዳይ የቤተክርስቲያን አንገብጋቢ ርዕስ መሆኑን ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ባልዳሳሪ፣ ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚቆየውን የብጹዓን ጳጳሳት 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን አስመልክተው መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል። የብጹዓ ጳጳሳት ጉባኤም በቀዳሚነት የሚወያየው በወጣቶች፣ እምነታቸውና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን እንዲገነዘቡ የሚል እንደሆነም ታውቋል።

ቤተክርስቲያን የወጣቶችን ጉዳይ በማስቀደም፣ ድምጻቸውን ለማዳመጥ፣ እምነታቸውንም ሆነ ጥርጣሬያቸውን፣ የሚያቀርቡትን ወቀሳቸውንም ሆነ አስተያየታቸውን ለመስማት መዘጋጀቷን ብጹዕ ካርዲናል ሎረንዞ ባልዳሳሪ በመግለጫቸው ገልጸዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሎረንዞ ባልዳሳሪ በመግለጫቸው እንደገለጹት የጳጳሳት ሲኖዶስ ትኩረትን ሰጥተውበት የሚወያዩባቸው ርዕሦችም ወጣቶች፣ እምነታቸውና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን እንዲገነዘቡ የሚሉ እንደሆኑ አስረድተው የሲኖዶሱ አባላትም ከመላው ዓለም ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተወጣጡ 267 ጳጳሳትና የመላው ዓለም ወጣቶችን የሚወክሉና ዕድሜአቸው ከ18 እስከ 29 የሆናቸው 34 ወጣቶችም ጽሑፋቸውን እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል።

ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል ስመተ ጵጵስናን በማስመልከት ለመጀመሪያ ጊዜ ስምምነት ማግስት የቻይና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል በጳጳሳት ሲኖዶስ የሚሳተፉ ሁለት ብጹዓን ጳጵእሳት ከቻይና መምጣታቸውን ካርዲናል ባልዳሰሪ ገልጸዋል። 

ካርዲናል ባልዳሳሪ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳስገነዘቡት የብጹዓን ጳጳሳት 15ኛው አጠቃላይ መደበኛ ሲኖዶስ ወጣቶች በተያያዙት ክርስቲያናዊ ጉዞ ከእግዚ አብሔር አምላካቸው ጋር እንዲገንኙ መንገድ ያመቻቻል ብለው፣ ምንም እንኳን ቤተክርስቲያን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ፈተናዎችና ችግሮች ውስጥ ብትገኝም ወጣቶች ማየት ያለባቸው ይህንን ፈተና እንዴት ማለፍ እንደሚቻል ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር በጋራ መወያየትና መነጋገር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። 

01 October 2018, 18:25