ፈልግ

2018.10.22 sala stampa Briefing sinodo giovani 2018 2018.10.22 sala stampa Briefing sinodo giovani 2018 

ብጹዕ አቡነ ቢዜቲ ለወጣቶች ተስፋን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ፣ ወጣቶች እምነትና ጥሪያቸውን በጥበብ እንዲረዱ ማድረግ በሚል የመወያያ ርዕስ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤን በመካፈል ላይ የሚገኙት፣ በቱርክ የአናቶሊያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪና እና የታቤ ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ቢዜቲ፣ ትናንት ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ. ም. በቫቲካን የዜና ማሰራጫ በኩል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት ለወጣቶች ተስፋን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የብጹዕ ቢዜቲን ጋዜጣዊ መግለጫ የተከታተሉት፣ በቫቲካን የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ እና በጳጳሳት ሲኖዶስ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ ብጹዓን ጳጳሳት የተወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች የመጨረሻው ሰነድ ረቂቅ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስና ለመላው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

ለወጣቶች የሚሰጡ እድሎች ጥቂት ብቻ  ናቸው፣

የአናቶሊያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ፣ ብጹዕ አቡነ ቢዜቲ በመግለጫቸው እንዳስገነዘቡት ቤተ ክርስቲያን ለወጣቶች በቂ ዕድሎችን ባለመስጠቷ ይቅርታን መጠየቅ ያስፈልጋል ብለው፣ ወጣቶች በማሕበርዊ ሕይወት በብቃት እንዳይሳተፉ እድል ካለመሰጠቱ የተነሳ ዓለማችን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ መውደቋን አስረድተዋል። አቡነ ቢዜቲ በማያያዝም፣ 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ የዓለም ወጣቶች የሚገኙበትን ሁኔታ፣ ችግሮቻቸውንና ስኬቶቻቸውን በዝርዝር እንድንመለከት በመደረጉ፣ ከጉባኤው ያገኙት ልምድ እንዳረካቸው ገልጸዋል። በማከልም በጉባኤው ወቅት ከወጣቶች የሚመነጩ ሃሳቦች ተጨባጭነት ያላቸው በመሆናቸው፣ የብጹዓን ጳጳሳትና የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ሃብት በመሆን ከወጣቶች ጋር ለመጓዝ፣ ድምጻቸውን ለማዳመጥ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሯል ብለው እምነት ተደፍኖ የሚቆይ እንዳልሆነ ገልጸው፣  የቤተክርስቲያን ውድ ሃብት የሆኑትን ወጣቶች ከጎናቸው በመሆን መርዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዲጂታሉ ዓለም የወንጌል ተልዕኮ ዋናው መንገድ ነው፣

በቫቲካን የዜና ማሰራጫ በኩል ጋዜጣዊ መግለጫቸውን የሰጡት፣ በሰሜን አሜርካ የብሪጅ ፖርት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፍራንክ ካጃኖ፣ ወጣቶች ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት እጅግ እንደማረካቸው ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ፍራንክ፣ ወጣቶች የቤተክርስቲያን አካል እንደመሆናቸው በቤትክርስቲያን ውስጥ ለውጥን ማምጣት እንደሚፈልጉ አስረድተው በማከልም ወጣቶች በቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት ላይ ሊያበረክቱ የሚችሉት ብዙ አስተዋጽዖ እንዳላቸው አስረድተዋል። የዲጂታል ማሕበራዊ መገናኛ መንገድ በተስፋፋበት ዓለማችኝ ወጣቶች በመካከላቸው የወንጌል አገልግሎትን ማዳረስ ይችላሉ ብለዋል። ሁላችንም ለቅድስና ተጠርተናል ያሉት አቡነ ፍራንክ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተካፈልን በሙሉ፣ ከጉባኤው የቀሰምናቸውን ሃሳቦች ወደ የአገረ ስብከቶቻችን የማዳረስ ተልዕኮ አለብን ብለዋል።

ምስክርነትን ለመስጠት መነሳሳት፣

የቅዱስ ጆቫኒ ቦስኮ ሳሌዢያን ምሕበር ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ አንገል ፌርናንደዝ አርቲመ፣ በበኩላቸው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን ትረትና ሁሉ አቀፍነትን ሲገልጹ፣ የጳጳሳቱ ሲኖድስ በተወሰኑ ወጣቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚገኙ ወጣቶችን፣ መብታቸው የተነፈገባቸውን ወጣቶች፣ የመላው ዓለም ወጣቶችን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል። በምስክርነታችን እንድንበረታ፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም የምንገልጽ እንድንሆን ወጣቶች ጠይቀውናል ብለዋል። በወጣቶች መካከል ለጋብቻ ሕይወት ያላቸው ፍላጎት እየቀሰ መምጣቱ ወጣቶችን እያሳሰበ መምጣቱን ገልጸው ቤተክርስቲያን ለዚህ ችግር መልስ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ወጣቶች ለዓለም ድምቀትን ይሰጣሉ፣

በካሬቢያን አገሮች መካከል፣ በፎርተ ዲ ፍራንስ፣ የማርቲኒክ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዳቪድ ማካይሬ በመግለጫቸው ወጣቶች የቤተክርስቲያን ተስፋና፣ የዓለማችን ደማቅ ብርሃን በመሆን የወንድማማችነት መንፈስ እንዲያድግ ያደርጋሉ ብለው መግለጫቸውን ከተከታተሉት መካከል፣ የጊኔያ ተወላጅ፣ ወጣት ሄንሪቴ ካማራን አስታውሰው፣ ወጣቷ ከእስልምና እምነት ወደ ክርስትና የመጣች መሆኗን ከገለጹ በኋላ መላውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በመጥራት፣ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲገልጹ ጊዜንና ቦታን ስላዘጋጁ፣ የጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ በነጻነት የሚወያዩበትን መድረክ በማዘጃጀት፣ አንዱ ከሌላው እንዲማር ዕድል የሰጡትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አመስግነው ወደ መጡበት ሀገረ ስብከት ሲመለሱ ከጉባኤው የቀሰሙትን ሃሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች እንደሚያካፍሏቸው ገልጸዋል።             

23 October 2018, 16:46