ፈልግ

cardinale Fernando Filoni cardinale Fernando Filoni 

ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ የወጣቶች ጥንካሬ የቤተክርስቲያን ሀብት እንደሆነ ገለጹ።

በዓለማችን ወጣቶቻችን የሚገኙበትን ችግርና እላያቸው ላይ የተቻነባቸውን ሸክም መመልከት ያለባት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳትሆን ሌሎች ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ተቋማትም ጭምር ተኩረት ሰጥተውበት ቢመለከቱት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም በመካሄድ ላይ የሚገኘውን 15ኛ አጠቃላይ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ አስተያየታቸውን ያካፈሉትና በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ስርጭት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወጣቶች ለሚያሳዩት ብርታትና ግልጽነት ትልቅ ዋጋን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ካርዲናል ፊሎን እንዳስረዱት ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸው ዕጣ ፈንታ ምን ሊመስል እንደሚችል ለማወቅ የሚያደርጉትን ጥረት፣ መንፈሳዊ፣ ስነ ልቦናዊና ሞራላዊ ግልጽነታቸውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል። በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ስርጭት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት ለእነዚህ አዲስ እውነታዎች ራሳቸውን ክፍት ያደረጉት ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድመው የሚያውቁ፣ ሃላፊነትንም ለመቀበል የተዘጋጁ ይሆናሉ ብለዋል።

የወጣቶች ጥንካሬና ግልጽነት ውድ ሀብታቸው ነው፣

ብጹዕ ካርዲናል ፊርናንዶ ፊሎኒ ካቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት በዛሬው ዓለማችን ወጣቶችን የሚገኙበትን ችግርና እላያቸው ላይ የተቻነባቸውን ሸክም መመልከት ያለባት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ማሕበራዊ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ተቋማትም ጭምር ተኩረት ሰጥተውበት ቢመለከቱት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል። የርዕሠ ሊቅነ ጳጳሳትን ሃሳብ በመጋራት አስተያየታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ ወጣቶች ስለ ጥሪያቸው፣ ወደ ፊት የሚጠብቃቸው ሕይወት ምን ይመስል እንደሆነ ለማወቅ በሚያድረጉት ጥረት መካከል ሊኖራቸው የሚገባውን ነጻነት መገፈፍ የለባቸውም ብለዋል። ወጣቶች ሁል ጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ እንጂ በአንድ ቦታ ብቻ የተረጋጉ አይደሉም ያሉት ካርዲናል ፊሎኒ በማከልም ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላም ከዚህ በፊት ያካበቱትን ጥበብና እውቀት በተግባር ላይ ሊያውሉ ይችላሉ ብለዋል። በመሆኑም ይህን የወጣቶች ጥረትና ያካበቱትን ዕውቀት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በትክክል ተገንዝቦ ዋጋን ከሰጠበት የጉባኤው ትልቅ ፍሬን ሊያስገኝ ይችላል ብለዋል።

ስለ የትኛው ወጣት እናወራለን?

ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ ከተጨባጭ እውነታ ለመረዳት እንደሚቻለው የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት እንድታጤን ለቤተክርስቲያን በርካታ ጥያቄዎች ቢቀርቡላትም በቂና ትክክለኛ ምላሽ የምታገኝበት መንገድ ገና እንዳልተረዳች አስረድተዋል። ስለዚህም ከሁሉ በፊት ስለ የትኛው ወጣት እንደምንናገር ለይተን ማወቅ ይኖርብናል ብለዋል። እድሜአቸው ከ14-16 ዓመት ድረስ ያላቸው ወጣቶች ዕድሜአቸው ከ25-28 ዓመት ድረስ ካላቸው ወጣቶች በእጅጉ የተለየ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል ብለው በዚህ መልኩ ካልተለየ በአገልግሎት አቅርቦት ላይ እክል በመፍጠት ውጤታማነቱን ሊቀን ይችላል ብለዋል። በሁለት ዓይነት የዕድሜ ክልል ያሉትን ወጣቶች ወስደው ያወዳደሩት ካርዲናል ፊሎኒ፣ የ29 ዓመት ዕድሜ ወጣት በልምድና ካካበተው የዕውቀት ደረጃ ከ16 ዓመት ዕድሜ ወጣት የተለየ እንደሆነ አስረድተው የ16 ዓመት ዕድሜ ወጣት ገና ልምድንና እውቀትን በማሳደግ ላይ እንዳለ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ ባቀረቡት ሌላ ምሳሌ ወጣቶች የሚገኙበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥም ተጽዕኖን ሊያደርግ ይችላል ብለው የአፍሪቃ፣ የእስያና የአውሮፓ ወጣቶች የሚለያዩበት የባሕል፣ የኤኮኖሚና የኤኮኖሚ ደረጃን ማስተዋል ይኖርብናል ብለዋል። ስለ ወጣቶች ስናወራ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን በቁጥር ወደ ሁለት ሚሊያርድ የሚጠጉትን ወጣቶች እንደሆነ አስረድተዋል። በመላው የዓለም ክፍሎች ከሚገኙት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የመጡት ጳጳሳት የተለያዩ ወጣቶች ልምድ ይዘው ነው የመጡት ያሉት ካርዲናል ፊሎኒ ለምሳሌ የአፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት በቤተክርስቲያን ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶች ልምድ ይዘው መጥተዋል ብለዋል።

ወጣቶች የራቁት ከቤተክርስቲያን ብቻ አይደለም፣

የወጣቱ ትውልድ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚያደረገው ተሳትፎ ሁል ጊዜ ፈተና እንደሚያጋጥመው ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ ከቤተክርስቲያን ውጭ ቢሆንም ፍላጎቱ የተሟላለት ሊሆን አይችልም ብለዋል። በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ስርጭት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ በንግግራቸው የወጣቱ ትውልድ ሁል ጊዜ ራሱን ከሌላው ዓለም የሚያገልበት ሁኔታ አለ ብለው፣ ወጣቶች ከወላጆቻቸው፣ ወጣቶች ከአካባቢያቸው ባሕል ራሳቸውን እንደሚያገልሉ ሁሉ ከቤተክርስቲያንም ራሳቸውን የገልላሉ ብለዋል። ወጣቶች ከቤተክርስቲያን ብቻ ራሳቸውን በድንገት ያርቃሉ ብሎ ማሰብ ስሕተት ነው ያሉት ካርዲናል ፊሎኒ ወጣቶች በቤተክርስቲያን ሆነውም የተረጋጉ ሳይሆኑ ሌላ አዲስ ነገርን ለማግኘት ፍላጎትና ምኞት ያድርባቸዋል ብለዋል። ይህም ከዕድሜአቸው ጋር የሚመጣ ስሜት በሆኑን በመገንዘብ፣ አዳዲስ ልምዶችንና እውቀት ይዘው የሚመለሱበትን ጊዜ በተስፋ መጠበቁ መልካም ይሆናል ብለዋል።                           

09 October 2018, 18:03