ፈልግ

2018.10.23 Incontro Giovani e Anziani 2018.10.23 Incontro Giovani e Anziani 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለወጣቶች ስጦታን ማበርከታቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጽሐፉን ለወጣቶቹ በስጦታ መልክ ያበረከቱት በተለይም ክርስቲያን ወጣቶች የማሕበራዊ ሕይወት አቅጣጫቸውን ለይተው በማወቅ የሚጠበቅባቸውን ማሕበራዊ ጥረት እንዲያሳድጉ ለማበረታታት ብለው ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ 15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ለተካፈሉት ወጣቶች ስጦታን ማበርከታቸው ተገለጸ። በቫቲካን ከተማ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ፣ ወጣቶች፣ እምነትና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት ሁኔታ እንዲገነዘቡ ለማድረግ በሚል የመወያያ ርዕስ፣ 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ. ም. 254 የሲኖዶሱ አባቶች በተገኙበት 19ኛ ዙር የሙሉ ቀን ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የዚህ ሲኖዶስ ጠቅላላ ሃሳብን በያዘ ሰነድ ላይ መወያየታችው ታውቋል። ጉባኤውን የተካፈሉት የሲኖዶሱ አባቶች፣ ወጣት ተወካዮችና የገዳማዊያንና ገዳማዊያት ተወካዮች ያቀረቡት ረቂቀ ሃሳብ የተቀመጠበት ሰነድ ወደ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት መቅረቡ ታውቋል። የተካፋዮቹ ሃሳብና አስተያየ በዋናው ሰነድ ውስጥ በመካተት፣ ይህን ሰነድ እንዲመለከቱት በጳጳሳቱ ሲኖዶስ ለተመረጡ ዋና ኮሚቴዎች፣ ለብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ፣ ዋና ጸሐፊዎች ለሆኑት ለክቡር አባ ጃኮሞ ኮስታ እና ለክቡር አባ ሮዛኖ ሳላ እንደሚቀርብ ታውቋል።

ትናንት በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው፣ 15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን በመካፈል ላይ ለሚገኙት ወጣት ተወካዮች፣ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮችን የያዘ ሰነድ በስጦታ መልክ ማበርከታቸው ታውቋል። ለወጣቶቹ የተበረከተው መጽሐፍ የከዚህ በፊት የነበሩት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ካወጧቸው ሰነዶች መካከል፣ በግንቦት 8 ቀን 1883 ዓ. ም. ይፋ የሆነው “Rerum novarum” የተሰኘና በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ ስርዓት በማገናዘብ በተለይም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎችን መሠረት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 13ኛ ይፋ ያደረጉት ሰነድ፣ ውዳሴ ላንተ ይሁን ከሚለው እስከ ከፍቅር የሚገኝ ደስታ የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቃለ ምዕዳኖችን የያዘ እንደሆነ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መጽሐፍ ለወጣቶቹ ሲያበረክቱ በተለይም ክርስቲያን ወጣቶች የማሕበራዊ ሕይወት አቅጣጫቸውን ለይተው በማወቅ የሚጠበቅባቸውን ማሕበራዊ ጥረት እንዲያደርጉ ለማበረታታት እንደሆነ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንደገለጹት በቅዱስ ወንጌል በመታገዝ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ራሳችንን እንድንድለውጥ፣ ቀጥሎም የምንኖርባትን ምድር እንድንንከባከባት፣ በመጨረሻም ዓለማችንን እንድንለውጥ የሚል መልዕክት መጻፋቸው ታውቋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ፣ 20ኛ ዙር ጠቅላላ ጉባኤውን ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ጉባኤ አስቀድሞ ጠዋት በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ፣ የ15ኛ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚያወጣውን የመጨረሻ ሰነድ የሚገመግም ወይም የሚመረምር የጳጳሳት ምክር ቤት ምርጫ መካሄዱ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አባላትና በድምሩ 300 የጉባኤው ተካፋዮች ከሮማ ቁምስናዎች ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር በመሆን ከሮም በ6 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘውን የቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ወደነበረበት ስፍራ መንፈሳዊ ጉዞን ማድረጋቸ ታውቋል። ይህን መንፈሳዊ ጉዞ ያዘጋጀው በጳጳሳዊ ምክር ቤት አዲስ የወንጌል ስርጭት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት እንደሆነ የታወቀ ሲሆን የንግደቱ ተካፋዮች በሙሉ ከስፍራው በመነሳት በቫቲካን ከተማ ወደሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ከደረሱ በኋላ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንሶ ባልዲሰሪ በሚመሩትና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተገኙበትን መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው ታውቋል። በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ 192 የሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች፣ ከእነዚህም መካከል 101 ብጹዓን ጳጳሳት፣ 9 ብጹዓን ካርዲናሎች፣ የሲኖዶሱን ጉባኤ የተሳተፉት 82 ወጣቶችና የተለዩ ባለሙያዎች እንደዚሁም ከሮም ሀገረ ስብከት የመጡ 100 ምእመናን መካፈላቸውን፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ አዲስ የወንጌል አገልግሎት ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ገልጸዋል።

25 October 2018, 17:11