ፈልግ

2018.10.05 Briefing Sinodo 2018.10.05 Briefing Sinodo 

ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች ጋር ሆና ማለም እንደምትፈልግ ተገለጸ።

“ቤተክርስቲያን እስካሁን በብቃት ላላከናወኗቸው ሐዋርያዊ ግዴታዎች እና ለፈጸመቻቸውም ስህተቶች ይቅርታን ጠይቃለች”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በተጀመረው 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ላይ፣ ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች ጋር ሆና የወደፊት ጉዞዋን ማለም እንደምትፈልግ ተገለጸ። በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ “ወጣቶች፣ እምነትና፣ ጥሪያቸውን በሚገባ ለይቶ ማወቅ” በሚሉ የመወያያ ነጥቦች ላይ ትኩረት ያደረገ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ጉባኤውን በይፋ ከጀመረበት ዕለት ወዲህ የመጀመሪያ በሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት ቤተክርስቲያን ወደ ፊት እንድትጓዝ ከተፈለገ ወጣቶችን በሙላት በማሳተፍ ከወጣቶች ጋር ለማለምና ለመስራት ጽኑ ፍላጎት አላት ብለዋል። ከተለያዩ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲዎችና ጳጳሳዊ ጉባኤዎች የመጡና በማሕበረ ሰብ ጥናት ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ምሑራን፣ ትናንት ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል። 

በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ በዘመናችን ወጣቶችን በተመለከተ በስፋት ከሚነሱ ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ለምሳሌ ወጣቶች ከሕብረተሰባቸው መካከል ስለመገለልና ተደማጭነትን ስለ ማጣት፣ ስደትና ስነ ጾታን እንዲሁም የወደፊት ሕይወታቸው ጥሪን በተመለከት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ጊዜ በአንክሮ ካስረዱት ጉዳዮች መካከል አንዱ የወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወትና ወጣቶች ከእግዚአብሔር ጋር ስላላቸው ግንኙነት በማስመልከት ተናግረው ቤተክርስቲያን በወጣቶች ዘንድ ስላላት ተዓማኒነትም ተናግረዋል። አቶ ፓውሎ ሩፊኒ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳስገነዘቡት ቤተክርስቲያን እስካሁን በብቃት ላላከናወናቸው ሐዋርያዊ ግዴታዎች እና ለፈጸመቻቸውም ስህተቶች ይቅርታን እንደጠየቀች ተናግረዋል።

ይህ አጋጣሚ ቤተክርስቲያን የወጣቶችን አቤቱታ ለማዳመጥ ምቹ ጊዜን እንደፈጠረላት የገለጹት የአርጀንቲናው ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ካርሎስ ሆሴ ቲሰራ፣ ቤተክርስቲያን ከወጣቶች ጋር መጓዝ ይኖርባታል ብለዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ፓርላማ አይደለም ያሉት የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባልና የ“Civiltà Cattolica” ወይም ካቶሊካዊ ስልጣነ የሚል መጽሄት ዳይረክተር የሆኑት ክቡር አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ በበኩላቸው፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በጥበብ ማስተዋል ያለበት፣ መንፈሳዊነትን የተላበሰ እንጂ የሃሳብ ክርክር የሚደረግበት መድረክ መሆን የለበትም ብለዋል።

በአርጀንቲና የኪልመስ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ካርሎስ ሆሴ ቲሰራ በማከል ወጣቶች ለቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር በረከት በመሆናቸው፣ ቤተክስቲያን የጣቶችን ድምጽ በማዳመጥ፣ ፍላጎታቸውን በመረዳት ጥያቄዎቻቸውን በመመለስ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገናኙበትን መንገድ ማሳየት አለባት ብለዋል።  ጳጳሳትና ካህናት፣ ወጣቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለሚያደርጉት ወዳጅነት ወይም ግንኙነት ድልድይ በመሆን፣ ወጣቶች በሕይወት ጉዞአቸው ብቻቸውን እንዳልሆኑ በተግባር ማሳየት አለባቸው ብለዋል።

በሚላኖ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ የማሕበረሰብ ጥናት ረዳት ፕሮፈሰርና የባሕሎች ግንኙነት ጠበብት የሆኑት ወይዘሮ ኪያራ ጃካርዲ በበኩላቸው ለቫቲካን የሕትመት ክፍል በሰጡት መግለጫ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ የቀረበውን ምስክርነት በማጠናከር እንደተናገሩት ቤተክርስቲያን ወጣቶችን ለማዳመጠ ያላትን ፍላጎት በተግባር ማሳየት አለባት ብለዋል። የጉባኤው ተሳታፊ የሆነው የቬትናም ተወላጅ በመዝሙሩ በኩል ባስተላለፈው መልዕክቱ ቤተክርስቲያን በተለያዩ መጠነ ሰፊ ችግሮች መካከል የሚገኙ ወጣቶች ትክክለኛ የሕይወት ጥሪያቸውን እንዲያውቁ እገዛን ማድረግ አለባት ብሏል።             

ያለፈው ዓመት የአምስቱም አህጉራት የጳጳሳት ጉባኤዎችን የሚወክሉ ወጣቶች፣ ከተለያዩ መንፈሳዊና ማሕበርዊ እንቅስቃሴዎች፣ ከገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተወካዮች የተወጣጡ 300 ወጣቶች ወጣቶች በሮም ተገኝተው “ወጣቶች፣ እምነትና፣ ጥሪያቸውን በሚገባ ለይቶ ማወቅ” በሚሉ የውይይት ነጥቦች ላይ ተነጋግረው የሚታወስ ነው።

05 October 2018, 18:19