ፈልግ

2018.10.23 Sinodo briefing 2018.10.23 Sinodo briefing 

የአባቶች ጥበብ፣ የወጣቶችን ኃይል መምራት እንደሚችል ተገለጸ።

ሽማግሌዎች ሕልምን የማያልሙ ከሆነ ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸውን መመልከት አይችሉም ብለዋል። አባ አንቶኒኣዮ ስፓዳሮ በመግለጫቸው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስም ቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎቷን የምታበረክትበት መንገድ እንደሆነ ገልጸው ሕዝበ እግዚአብሔር ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ የወንጌል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ የሚተባበሩ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የቤተክርስቲያን አካል እንደሆኑ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የሕትመት ክፍል ቀርበው ጋዜጣዊ መግለጫቸውን የሰጡትና 15ኛን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤን በመከታተል ላይ የሚገኙት አባቶች በመግለጫቸው፣ ወጣቶች ከአባቶች በሚያገኙት ጥበብ መታገዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቤተክርስቲያን ሁሉንም የምታስተናግድ የጋራ ቤት እንደሆነችም ያስረዱት ብጹዓን አባቶች፣ ከጉባኤው ብዙ ትምህርቶችን የቀሰሙ መሆናቸውን ገልጸው በጉባኤው ላይም በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ሰጥተውባቸዋል። የብጹዓን አባቶች በጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ የወጣቶችን መንፈሳዊም ሆነ ማሕበራዊ የሕይወት ጉዞን ከአባቶች ሕይወት ነጥሎ መመልከት አይቻልም ብለው በሁሉም አቅጣጫ ቢሆን የብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስም ሆነ የቤተክርስቲያን ጉዞ የሚያመላክተን ይህን ነው ብለዋል።

የሃላፊነት ባሕል ይኑር፣

በኦሸኒያ የዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት አባልና፣ 15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን በመካፈል ላይ የሚገኝ ወጣት ዮሴፍ ሳፓቲ፣ ከብዙ ሺህ ዓመታት ወዲህ የአገሩ ሕዝብ ውቅያኖስ ላይ በመጓዝ የፈለጉበት ስፍራ ለመድረስ ኮኮብን መከተል የአባቶች ምክር እንደሆነ አስታውሷል። ይህ የአባቶች ጥበባና ምክር ቤተክርስቲያንንም ለመምራት ትልቅ እገዛ እንዳለው ገልጾ  ወጣቶችም በበኩላቸው ጉልበታቸውን በመጠቀም የወንጌል አገልግሎትን ማበርከት ይችላሉ ብሏል።

አብሮ መኖር፣ አብሮ መጓዝ፣

በኮንጎ ሪፓብሊክ፣ የዶሊሴ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤንቨኑ ማናሚካ፣ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳስገነዘቡት፣ 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ፣ በሕብረት ተወያይተን፣ በሕብረት እንድንጓዝ የሚያደርግ ስሜት የታየበት እንደሆነ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በጉባኤው መካከል በመገኘት ሃሳባችንን በነጻነት እንድንገልጽ በማድረግ ብርታትን ሰጥተውናል ብለው በጉባኤው መካከል የተገኙት ወጣቶችም በሚያቀርቡት ሃሳብ፣ አስተያየትና ጥያቄዎች፣ ወጣቶች እንድንሆን አድረገውናል ብለዋል።

ህልሞች እና ራዕዮች፣

ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ከሰጡት መካከል “ካቶሊካዊ ስልጣኔ” የተባለ መጽሄት ዳይረክተር የሆኑት ክቡር አባ አንቶኒኣዮ ስፓዳሮ በበኩላቸው የአባቶች ራዕይ የወጣቶችን የወደፊት ዕድል ይከፍታል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ነቢዩ ኢዩኤል በትንቢቱ ላይ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፣ ጎልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ (ትንቢተ ኢዩኤል በምዕ. 2. 28.) የተጻፈውን አስታውሰው እንደነበር ገልጸው፣ ሽማግሌዎች ሕልምን የማያልሙ ከሆነ ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸውን መመልከት አይችሉም ብለዋል። አባ አንቶኒኣዮ ስፓዳሮ በመግለጫቸው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስም ቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎቷን የምታበረክትበት መንገድ እንደሆነ ገልጸው ሕዝበ እግዚአብሔር ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ የወንጌል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ የሚተባበሩ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የቤተክርስቲያን አካል እንደሆኑ አስረድተዋል።

የጊዜውን ጥበብ መከተል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ጥቅምት 13 ቀ 2011 ዓ. ም. በሮም ከተለያዩ አገሮች ከመጡት ወጣቶችና አዛውንት ጋር ለመገናኘት እቅድ እንዳላቸው ያስታወሱት ክቡር አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ፣ የግኑኝነታቸው ዓላማ፣ “ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የዘመኑ ጠቢብ፣ በዘመናችን በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ውይይት የሚያደርጉ” በሚል ርዕሥ የተጻፈው መጽሐፍ ለአንባቢያን ይፋ የሚደረግበትን አጋጣሚ ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ መጽሐፍ ከ30 አገሮች በላይ ለተሰበብሰቡ 250 ጥያቄዎች መልስና ትናታኔዎችን ለመስጠት የተሞከረበት እነደሆነ ገልጸው መጽሐፉ እንዲታተም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ ፈቃድ እንደነበር የገልጹት ክቡር አባ ስፓዳሮ፣ ሕልምን የሚያልሙና ጥበባቸውን የሚጋሩ ሽማግሌዎች ያስፈልጉናል ያሉትን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን ንግግር አስታውሰዋል።

ቤተክርስቲያን ሁሉን ተቀብላ የምታስተናግድ ትሁን፣

ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ከሰጡት መካከል የማኒላ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በበኩላቸው ቤተክርስቲያን በማንኛውም ጊዜ ሰዎችን ተቀብላ የምታስተናግድ መሆን አለባት ብለዋል። የሰዎችን ስብዕና በሚገባ ያገናዘበ ማሕበር ሁል ጊዜ ከሕዝብ ጋር ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ቤተክርስቲያን የሰዎችን ጾታዊ አስተዳደግ ሁኔታን በመልከት ምንም ዓይነት ልዩነት ሳታደርግባቸው በእኩል ዓይን መመልከቱ በጉባኤው መካከል በሚገባ ውይይት እንደተደረገበት ገልጸው ይህን በተመለከተ ወደፊት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ይፋ በሚያደርገው የጉባኤው ሰነድ ላይ በዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጥበት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ብዙ ነገሮችን የተማሩበትና ወጣቶችም ሃሳቦቻቸውን ያካፈሉበት አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸው አሁንም ቢሆን ከወጣቶች በሚመነጩ ተጨባጭ ልምዶች ተውስደው ጥናቶች መደረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሴቶች ድምጽ ይሰማ፣

በ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ላይ ስለ ሴቶች ጉዳይ ተነስቶ ኣንደሆነ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጡት የማኒላ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ከሴቶች በኩል የሚቀርቡ ሃስቦችና አስተያየቶች ተደማጭነት ሊኖራቸው እንደሚገባ እራሳቸው በተገኙበት ቡድን ውስጥ ውይይት ከመደረጉም በላይ፣ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ የተጠቀሱ ሴቶች ሕይወት ለዘመናችን ወጣቶች እንደ ምሳሌ እንዲሆን የሚል ሃሳብ መቅረቡን አስታውሰዋል።

የመነሻ ምንጭ

ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ከሰጡት መካከል በሚያንማር የያንጎን  ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ቻርልስ ማውንግ ቦ በበኩላቸው፣ 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ብዙዎቻችን ለወጣቶቻችን ምን ማድረግ አለብን ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ አድርጎናል እያንዳንዱ ሃገረ ስብከት የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን ምክሮችን በመከተል ለወጣቶችና ለመላው ቤተክርስቲያን እድገት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ከጉባኤው እንደሚገኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻ ሰነድ፣

በቫቲካን የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ እና የብጹዓ ጳጳሳት ሲኖዶስ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውይይቶች የሰፍፈረበት የመጨረሻው ሰነድ ረቂቅ ለሲኖዶስ መቅረቡን ገልጸው ቀጥሎም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚቀርብ አስረድተዋል።

24 October 2018, 15:45