ፈልግ

2018.10.18 Briefing 18 ottobre 2018.10.18 Briefing 18 ottobre 

ካርዲናል ብርሃነየሱስ “ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው”።

አንዳንድ የአውሮጳ አገሮች ስደተኞች እንዳይገቡ ብለው ድንበሮቻቸውን ሲዘጉ ማየት ወይም መስማት እጅግ ያሳዝናል ብለዋል። ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከእነዚህ ተፈናቃዮች ወይም ስደተኛ ወጣቶች ጋር መሆኗን አስገንዝበው በዓለማችን 40 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የባርነት ሕይወት እንደሚኖሩ፣ ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤን በመካፈል ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ፕሬዚደንትና የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤዎች ሕብረት አገሮች የበላይ ጠባቂ፣ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱ ሱራፌል፣ የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት የተወያዩባቸውን ርዕሠ ጉዳዮች አስመልክተው በቫቲካን የዜና ማሰራጫ በኩል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት የአውሮጳ ትልቁ ክርስትያናዊ ስልጣኔ መሠረቱ መስተንግዶ እንደሆነ አስረድተው አውሮጳ ይህን ክርስቲያናዊ እሴት መዘንጋት የለባትም ብለዋል።

በርካታ የዜና ማሰራጫዎች ስደትን አስመልክተው የሚሰጡት መረጃ የአፍሪቃ ወጣቶች ወደ አውሮጳ ለመድረስ የሚያደርጉትን የባሕር ላይ ጉዞ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ነገር ግን ከመቶ 80 እጅ የሚሆን የአፍሪቃ ወጣት የሚሰደደው ወይም የሚፈናቀለው በሚኖርበት አገር ወይም በአፍሪቃ አህጉር ውስጥ እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል በሌላ ቃለ ምልልስ እንደገለጹት የአፍሪቃ ወጣቶች ሐይማኖተኞች እንደሆኑ፣ ቤተክርስቲያንም ከጎናቸው ሆና እንደምታዳምጣቸው፣ ነገር ግን ወጣቶች ራሳቸውን ከቤተክርስቲያን በሚያርቁበት ጊዜ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ይወድቃሉ ብለዋል። የኤች አይ ቪ ኤይድስ እና የሥራ እጦት ከፍተኛ የወጣቶች ችግር እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱ ሱራፌል፣ የወጣቶችን መሰደድ ለመቀንስ፣ የውጭ አገር እርዳታ ሰጭ ድረጅቶች ከቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር፣ በትላልቅ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የሚያገኙትን የሥራና የትምሕርት ዕድል በገጠራማው አካባቢ ያሉት ወጣቶችም እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

አንዳንድ አገሮች ድንበሮቻቸውን መዘጋታቸው ያሳዝናል፣

መጠነ ሰፊ ችግሮች ያለባት አፍሪቃ በሙስና፣ በእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ምክንያት ተጨማሪ ችግሮች ይደርሱባታል ብለዋል። በተለይም በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ምክንያት በርካታ ወጣቶች ይሞታሉ ብለዋል። ስደተኛ መሆን በከባድ ችግር ላይ ይጥላል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው፣  ከወላጅ ቤተሰብ ተለይተው ወደ ባዕድ አገር ለሚሰደዱት ወጣቶች ክርስቲያናዊ ተግባር መሆን ያለበት በር መዝጋት ሳይሆን በእንግድነት ተቀብሎ ማስተናገድ ነው ብለዋል። አንዳንድ የአውሮጳ አገሮች ስደተኞች እንዳይገቡ ብለው ድንበሮቻቸውን ሲዘጉ ማየት ወይም መስማት እጅግ ያሳዝናል ብለዋል። ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከእነዚህ ተፈናቃዮች ወይም ስደተኞ ወጣቶች ጋር መሆኗን አስገንዝበው በዓለማችን 40 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የባርነት ሕይወት እንደሚኖሩ፣ ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ እንደሆነ ገልጸዋል።           

ቤተክርስቲያን ከሚሰቃዩት ጋር ናት፣

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ከቫቲካን የዜና ማሰራጫ ተቋም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የአውሮጳ ትልቁ ክርስትያናዊ ስልጣኔ መሠረቱ መስተንግዶ እንደሆነ አስረድተው አውሮጳ ይህን ክርስቲያናዊ እሴት ማጣት የለባትም ብለዋል። በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች፣ በሰዎች ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለምሳሌ ፓክስታንን በመሳሰሉት፣ በተጨማሪም በሕንድና በአፍሪቃ በርካታ ሰዎች ስቃይና መከራ እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የኮሚንስት ስርዓት በነበረበት ጊዜ በሰዎች ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው አስታውሰው በክህነት አገልግሎት ወቅት በእርሳቸው ላይ የእስር ቅጣት ተበይኖባቸው እንደነበር አስታውሰው እምነት ግን ሁሉንም ያሸንፋል ብለዋል።    

የወጣቶችን ጩሄት ማዳመጥ ያስፈልጋል፣

በጳጳሳዊ ፋክልቲ፣ የስነ ትምሕርት ክፍል ውስጥ የምጣኔ ሃፍት መምህር የሆኑት እህት አሌሳንዳራ ስመሪሊ፣ የምጣኔ ሃፍትና ስነ ምህዳር ተመሳሳይነት እንዳላቸው በማስረዳት፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማስታወስ፣ የምንኖርባት ምድርና የወጣቶቻችንን ጩሄት ከማዳመጥ ወደ ኋላ ማለት አንችልም ብለዋል። የኢጣሊያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጎ አድራጊ ድርጅት ዓመታዊ ሪፖርት በማስታወስ በኢጣሊያ፣ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝ የወጣት ቁጥር ከአዛውንት በልጦ ተገኝቷል ብለዋል እህት አሌሳንድራ። በኢጣሊያ ውስጥ፣ በድህነት ከተመዘገቡት መካከል ከሁለቱ አንዱ ወጣት ወይም ገና በልጅነት የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል ዘላቂነት መፍትሄ ካላገኙ በስተቀር መቀየር እንደማይቻል አስረድተዋል።       

የጳጳሳት ሲኖዶስ የጋራ ልምዳችን ነው፣

ትናንት ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ. ም. የወጣቶችን እውነታ ለማዳመጥ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ቀርበው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት፣ በኢጣሊያ የቦሎኛ ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ ማርያ ዙፒ በበኩላቸው፣ በመካሄድ ላይ ያለው የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፣ በአካል ተገናኝተን ሃሳብን ለመለዋወጥና ለመደማመጥ ዕድልን የከፈተ የጋራ ልምድ እንደሆነ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ ዙፒ አክለውም የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ስለ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ ውይይት፣ ስለ ስደት፣ ስለ ጥገኝነት ጠያቂዎች በስፋት መወያየቱን አስረድተው፣ እነዚህ ርዕሶች ከሚመለከቷቸው አብዛኛዎቹ ወጣቶች እንደሆኑ ገልጸዋል። በቅድስት መንበር የምእመናን ጉዳይ ተንከባካቢ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ አሌስንደር አዊ ሜሎ በበኩላቸው፣ የጳጳሳቱ ሲኖዶስ በቫቲካን ለመሰብሰብ መብቃቱ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ብለው በጋራ ሆነን ተስፋን የሚሰጥ የጋራ ውይይት  ለማድረአግ ችለናል ብለዋል።

ፖለቲካ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ ይሁን፣

በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት የመገናኛ ክፍል አስተባባሪ፣ ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ በበኩላቸው በሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት የተካሄዱት የመጨረሻዎቹ ጉባኤዎች፣ ፖለቲካ ሕዝብን ለማገልገል የቆመ እንደሆነ መገለጹን ተናግረው በሌላ ወገን በፖለቲካ ዘርፍ የሚንጸባረቀው ምግባረ ብልሹ አመራር ወጣቶችን እያሳሰበ መምጣቱን አስረድተዋል። ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ የጳጳሳቱ ሲኖዶስ የተወያየባቸው ሌላው ርዕስ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በርካታ ሰዎች አስከፊ በሆነው የባርነት ሕይወት ውስጥ በመውደቃቸው ብዝበዛና ወንጀል እንደሚፈጸምባቸው መግለጻቸን ተናግረው፣ ቤተክርስቲያን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መቃወም እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።             

19 October 2018, 10:43